የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2024/25 የውድድር ዘመን በሊቨርፑል አሸናፊነት ተጠናቋል። አርኔ ስሎት የመርሲሳይዱን ክለብ እየመራ በመጀመሪያው ዓመት የአንፊልድ የአሰልጣኝነት ህይወቱ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን አሳክቷል። አርሰናል፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ቸልሲ እና ኒውካስትል ዩናይትድ በቅደም ተከተል ከሁለት እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል። ቶትንሀም ሆትስፐርስም የኢሮፓ ሊግ ዋንጫን በማሳካት በአቋራጭ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ቦታውን አስጠብቋል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ዘንድሮም አጃቢ ሆኖ አጠናቋል። በተከታታይ ሦስት ዓመታት ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል። ይህም በክለቡ ታሪክ አዲስ ክብረወሰን ሆኗል። አርሰናል ከዚህ በፊት በፈረንሳያዊው የቀድሞ አሰልጣኙ አርሰን ቬንገር ዘመን በተከታታይ ሦስት የውድድር ዘመናት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን መረጃዎች አመልክተዋል። በ1998/99፣ በ1999/2000 እና በ2000/2001 እ.አ.አ የውድድር ዘመን በተከታታይ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀበት ወቅት ነው።
መድፈኞቹ እስካሁን በአጠቃላይ ስምንት ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው መጨረሳቸውን የአርሰናል ኢንሳይደር መረጃ አመልክቷል። ዘንድሮም የሊቨርፑል አጃቢ ሆኖ ያጠናቀቁት ወጣት መድፈኞች ዋንጫውን ለማንሳት ሌላ ተጨማሪ የውድድር ዘመን በተስፋ የሚጠብቁ ይሆናል። ወጣት መድፈኞቹ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከውድድሩ አጋማሽ በኋላ ጉልበታቸው እየዛለ በሊቨርፑል እና በማንቸስተር ሲቲ ዋንጫውን ተነጥቀዋል። የዋንጫውን አንደኛውን ጆሮ ከያዙት በኋላ ጉልበት እያጡ ዓመቱን በዋንጫ ሳይሆን በእንባ ታጅበው አጠናቀዋል።
እ.አ.አ በ2019 ታህሳስ ወር ስፔናዊው አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ኤምሬትስ ከደረሰ በኋላ ክለቡ በብዙ መልኩ ተቀይሯል፤ በኤምሬትስ አዲስ የእግር ኳስ አቢዮትም ተፈጥሯል። ተሰፋ ቆርጦ የነበረው ደጋፊም ተነቃቅቷል። ስፔናዊው ታክቲሺያን ቡድኑን እንደገና በወጣት ኮከቦች በመገንባት ዋነኛ ተፎካካሪ ክለብ አድርጎታል። በሜዳው እና ከሜዳው ውጪ የእንግሊዝ እና የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦችን በማሸነፍ ታላቅነቱን አስመስክሯል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ ከዐስር ዓመታት በኋላ ዘንድሮ በታላቁ መድረክ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ድረስ መጓዝ ችሏል። ለረጅም ዓመታት በኦልትራፎርድ፣ በኢትሀድ፣ በስታንፎርድ ብሪጅ እና በቶትንሀም ሆትስፐርስ ሜዳ የነበረባቸውን የፍርሀት ቆፈን ገፈው ከጨዋታ ብልጫ ጋር በማሸነፍ ኃያልነታቸውን አሳይተዋል። ሚኬል አርቴታ አርሰናልን ከተረከበ በኋላ ባለፉት አምስት ዓመታት ትልቅ እና ለዋንጫ ተፎካካሪ ክብረወሰን የሚሰብር እና ግልጽ የራሱ የእግር ኳስ ፍልስፍና እና ባህል ያለው ክለብ ሆኗል።
የሊጉን ዋንጫ ካነሳ 21 ዓመታትን ያስቆጠረው አርሰናል ዘንድሮም ተጨማሪ ዓመት ለመጠበቅ ተገዷል። መድፈኞቹ ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫ ሲያነሱ አብዛኞቹ የክለቡ ተጫዋቾች ነብስ አያውቁም ማለት ይቻላል። ቡካዮ ሳካ፣ ማርቲኔሊ፣ሳሊባ፣ ማጋሌሽ ፣ቲምበር እና ካላፊዮሪ የሁለት ዓመት ህጻናት ነበሩ ሳሊባ ደገሞ የሦስት ዓመት ልጀ የነበረ ሲሆን ሊዊስ ስኬሊ እና ንዋነሪ ደግሞ አርሰናል የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ ገና አልተወለዱም ነበር። እናም እነዚህ ተጫዎቾ ች ምንም አይነት ትዝታ የላቸውም።
የኤምሬትስ የመልበሻ ክፍሉ በፈረንሳያዊው የእግር ኳስ ሊቅ የተገነባ ቢሆንም በሚኬል አርቴታ ቁልፍ መልዕክቶች ማጌጡ ግን የተለየ ትርጉም ይዟል። “እስከ መጨረሻ ሽርፍራሪ ሴኮንድ ታገሉ” የሚለው መልዕክት ሲወጡ እና ሲገቡ እንዲነቃቁ አድርጓቸዋል። በአሰልጣኝ አርቴታ ዘመን ኤምሬትስ ጠንካራው ምሽግ ነው። የትኛውም ተጋጣሚ ቡድን ወደ ኤምሬትስ ዘልቆ ይህንን ጠንካራ ምሽግ በቀላሉ መበታተን አያስችለውም።
ኤምሬትስ ለተጋጣሚ ቡድን የግዞት ምድር መሆኑን ወጣት መድፈኞቹ በተደጋጋሚ አሳይተዋል። የፊት መስመሩ ምንም እንኳ ተጨማሪ ጉልበት እና ኃይል መሰብሰብ ቢኖርበትም አምና እና ካቻምና ተኩሶ ኢላማውን የሚስት እንዳልነበረ ተመልክተናል። አርቴታ በመድፈኞቹ ቤት በታክቲክ ተለዋዋጭ የሆነ፣ አጭር ቅብብል የሚያደርግ፣ በኳስ ቁጥጥር እና ተጭኖ በመጫወት የሚያምን የእግር ኳስ ፍልስፍና እየተከተለ ይገኛል። በዚህ የእግር ኳስ ፍልስፍና እየተመራ ባለፉት ሦስት ዓመታት ማራኪ እግር ኳስ ከሚጫወቱ ጠንካራ የአውሮፓ ክለቦች ውስጥ ተካተዋል።
ወጥ በሆነ የጨዋታ ስልት እና አቋም በታላላቅ ክለቦች ላይ ብርቱ ክንዳቸውን አሳርፈዋል። ባለፉት ሦስት የውድድር ዘመናት ከፍተኛ ነጥብ በመሰብሰብ አጠናቋል። ጥቂት ጨዋታዎችንም የተሸነፉ ሲሆን አነስተኛ ግቦች ከተቆጠሩባቸው ክለቦች መካከልም ከቀዳሚዎች ተርታ ይሰለፋሉ። በሳሊባ እና በጋብሬል ማጋሌሽ የሚመራው የኋላ ክፍል እንደ አለት ጠንካራ እንደሆነ ቁጥሮች ይናገራሉ። ተጋጣሚ ቡድን ከዚህ የሜዳ ክፍል ሲደርስ ጉልበታቸው እንደሚፍረከረክ በየጨዋታዎች ተመልክተናል።
አርሰናል በጠንካራ እና ባለተሰጥኦ ተጫዋቾች የተሞላ ቡድን ቢሆንም የስብስቡ ጥልቀት ግን ደካማ መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው። እንደ ዘ አትሌቲክ መረጃ ባለፉት ዓመታት ተጫዋች ሲጎዳ ውጤቱን ለማስጠበቅ እና የቡድኑን ቅርጽ እና ሚዛን ለመጠበቅ በቂ የተጫዋች ስብስብም የለውም። በማርቲን ኦዲጋርድ፣ ዴክላን ራይስ እና ቶማስ ፓርቴ የሚመራው የአማካይ ክፍል ወደ ኋላ አፈግፍጎ የሚከላከልን ቡድን ለመበታተን የፈጠራ ክህሎት ይጎለዋል።
በተጋጣሚ የግብ ክልል አደጋ የሚፈጥር እና ጨራሽ የሆነ ግብ አነፍናፊም ባለመያዙ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብዙ ዋጋ ከፍሏል። በርካታ ግብ የሆኑ ኳሶችም ሲባክኑ እንደነበር የኤስፒኤን መረጃ አመልክቷል። ለአብነት ዘንድሮ አርሰናል ከኒወካስትል ዩናይትድ በነበረው በካራባዎ ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ መድፈኞቹ ካደረጓቸው 23 ሙከራዎች ሦስቱ ብቻ ኢላማቸውን የጠበቁ እንደነበር አይዘነጋም። ይህም የፊት መስመሩ ምን ያህል ደካማ ስለመሆኑ ማሳያ ነው።
በአንጻሩ የአርሰናል ጥንካሬ ከሚገለጽባቸው ጉዳዮች መካከል የቆሙ ኳሶችን በሚገባ መጠቀም ነው። በአማካይ 32 በመቶ የሚሆኑት የአርሰናል ግቦች ከቆሙ ኳሶች የተገኙ መሆናቸውን ጎል ዶት ኮም አስነብቧል። በተለይ ዘንድሮ አርሰናል በወሳኝ ወቅት በተደጋጋሚ ጉዳት እና ቅጣት የወሳኝ ተጫዋቾችን ግልጋሎት አለማግኘቱ የሚታወስ ነው። ይህም የሊቨርፑል አጃቢ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ ሌላኛው ምክንያት መሆኑን የኤስፒኤን መረጃ አመልክቷል። ታዲያ ክለቡ በዚህ ክረምት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል አንዱ አጥቂ ማስፈረም መሆኑን መረጃው ይጠቁማል።
የተጋጣሚ ቡድንን የሚያሸብር እና ቢያንስ በየዓመቱ ከ20 ግቦች በላይ የሚያስቆጥር ዓለም አቀፍ አጥቂ ማስፈረም ይጠበቅበታል ይላል መረጃው። ባሳለፍነው ዓመት አጥቂ ሳያስፈርም በዋዛ ፈዛዛ ወቅቱን ማሳለፉ የሚታወስ ነው። ዘንድሮ ግን ያምናው ስህተት እንደማይደገም አሰልጣኙ ተናግረዋል። ገና ከወዲሁም በረካታ ተጫዋቾች ከአርሰናል ጋር ስማቸው እየተነሳ ይገኛል። የስፖርቲንግ ሌዝበኑ ቪክተር ጎይከርስ፣ ኒኮ ዊሊያምስ፣ ሮድሪጎ እና አሌክሳንደር አይዛክን የመሳሰሉ በአርሰናል የዝውውር ራዳር ውስጥ ያሉ ተጫዋቾች መሆናቸውን በርካታ የእንግሊዝ ጋዜጦች እየዘገቡት ነው።
የካይ ሀቨርትዝ እና የጋብሬል ጀሱስ መጎዳትን ተከትሎ ሚካኤል መሪኖ ቦታውን ሸፍኖ ሲጫወት እንደነበረ የሚታወስ ነው። አምና የአርሰናል ተጫዋቾች በአጠቃላይ በድምሩ 90 ግቦችን ቢያስቆጥሩም አንድም ተጫዋች ግን ከ25 ግብ ማስቆጠር አልቻለም። እ.አ.አ በ2003/4 ቴሪ ዳንኤል ሄነሪ በአንድ የውድድር ዘመን 25 ግቦችን ካስቆጠረ በኋላ በኤምሬትስ የትኛውም አጥቂ ከዚህ ቁጥር መድረስ አልቻለም። በዚህ ምክንያት ነው ጂሚ ካራገር እና ሌሎች የእግር ኳስ ተንታኞች አርሰናል አስፈሪ የፊት መስመር ሳይኖረው ዋንጫ ለማንሳት ማሰቡ ቅዥት መሆኑን በተደጋጋሚ እየተናገሩ ነው።
በተጨማሪም ፈጣሪ አማካይ የሚያስፈልገው አርሰናል ማርቲን ዙቢሜንዲን ከሪያል ሶሲዳድ ለማስፈረም ቀደም ብሎ እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚታወስ ነው። ከግራኒት ዣካ በኋላ በየጨዋታው በኤምሬትስ ከ70 እስከ 100 የተሳኩ ኳሶችን የሚያቀብል አማካይ አልተገኘም። ታዲያ ዙብሜንዲ ኤምሬትስ የሚደርስ ከሆነ ምን አልባት ስዊዘርላንዳዊውን አማካይ የሚያስታውስ ተጫዋች ሊሆን ይችላል። በግራ መስመሩም ከቡካዮ ሳካ እኩል ብቃት ያለው የክንፍ አጥቂ ማስፈረም እንደሚጠበቅበት መረጃው ይጠቁማል።
በቦታው የሚጫወቱት ማርትኔሊ እና ትሮሳርድ ከእንግሊዛዊው አጥቂ እኩል ተጋጣሚን ሲያሸብሩ አንመለከትም። የአርሰናል ዋነኛው የማጥቂያ መሳሪያ የሆነው ሳካ በተደጋጋሚ ጉዳት የሚያጠቃው ተጫዋች በመሆኑ የሳካን ቦታ በትክክል ሊሸፍን የሚችል የቀኝ ክንፍ ተጫዋች ያስፈልገዋል። አርቴታ እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት በዚህ ቦታ ማርትኔሊን፣ ትሮሳርድን እና ጋብሬል ጀሱስን የመጠቀም እቅድ ቢኖራቸውም የእንግሊዛዊውን ቦታ በትክክል እንደማይሸፍኑ ግን ይገነዘቡታል።
አሁን ላይ አርሰናል በዝውውር ፖሊሲው መጠነኛ መሻሻል ማድረጉ ለክለቡ ለውጥ እንደ ምክንያት ይጠቀሳል። ምንም እንኳ ባለሀብቱ ስታን ክሮንኬ ለተጫዋቾች ዝውውር እጁ ተፍታቷል ባይባልም በቬንገር ዘመን ከነበረው የዝውውር ፖሊሲ ጋር ሲነጻጸር ግን በእጅጉ ለውጥ ይታይበታል። አርቴታ በአርሰናል ቤት ቆይታው ለዝውውር ከ700 ሚሊዪን ዮሮ በላይ ለተጫዋቾች ዝውውር ማውጣቱን የጎል ዶት ኮም መረጃ አስነብቧል። እናም በዚህ ከረምት አርሰናል ሚለዪን ዶላሮችን ፈሰስ አድርጎ ደፍሮ ተጫዋች እንደሚገዛ ብዙዎች ተስፋ አድርገዋል።
በዚህ ዓመት በወርሃ መጋቢት ኢዱ ጋስፐርን ተክቶ ኤምሬትስ የደረሰው አንድሪያ ቤርታ በመጪው የክረምት የዝውውር ወቅት ይሄንን ሁሉ ክፍተት በመሙላት ይበልጥ ክለቡን ጠንካራ ያደርጉታል ተብሎ ይጠበቃል። አርሰናል በፈረንጆች ሚሊኒየም ዋዜማ እና ማግስት ሦስት ተከታታይ ዓመታትን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ካጠናቀቀ በኋላ እአአ በ2003/4 አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ዋንጫውን አሳክቷል።ታዲያ አሁንም በተስፋ ሌላ 38 የጨዋታ ሳምንታትን የሚጠብቁት መድፈኞች በ2025/26 የውድድር ዘመን ይሳካላቸው ይሆን? አብረን የምናየው ይሆናል።።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም