የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮንደር ሊየን እ.አ.አ በ2005 እና 2019 መካከል በጀርመን ፌዴራል መንግሥት ውስጥ አገልግለዋል፡፡ በአንጌላ ሜርክል ካቢኔ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ የነበራቸው ቮንደር ሊየን የፌዴራል የመከላከያ ሚኒሥትር ሆነውም አገልግለዋል። አሁን ደግሞ ከ2019 ጀምሮ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ ።
ከጀርመናዊ ወላጆቻቸው በብራስልስ ቤልጂየም ተወልደው ያደጉት ኡርሱላ ቮንደር ሊየን አባታቸው ኤርነስት አልብሬክት ከመጀመሪያዎቹ የአውሮፓ የመንግሥት ሠራተኛ (ሲቪል ሰርቫንቶች) አንዱ ነበሩ። ጀርመንኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑት ኡርሱላ ቮንደር ሊየን በ1971 አባታቸው በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ ወደ ጀርመን ሲያቀኑ እርሳቸውም ከቤተሰቦቻቸው ጋር አብረው ሄዱ። በ1978 ከለንደን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት ተመረቁ፡፡
እ.አ.አ በ1980 ደግሞ በሃኖቨር የህክምና ትምህርት ቤት በመግባት በ1987 የህክምና ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በሴቶች ጤና ላይ ለመስራት የሚያስችል የሙያ ፍቃዳቸውን አግኝተዋል። ከ1988 እስከ 1992 በሃኖቨር ሜዲካል ትምህርት ቤት የሴቶች ክሊኒክ ረዳት ሐኪም ሆነው ሠርተዋል።
ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮንደር ሊየን ትዳር መስርተው መንታ ልጆች ከወለዱ በኋላ በስታንፎርድ ካሊፎርኒያ ከ1992 እስከ 1996 ከሥራ ውጪ ሆነው ቆይተዋል፡፡
ባለቤታቸው ኡርሱላ ቮንደር ሊየን የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፋኩልቲ አባል ሆነው በመመደባቸው በ1996 ወደ ጀርመን ተመለሱ። ከ1998 እስከ 2002 በሃኖቨር ሜዲካል ትምህርት ቤት በኤፒዲሚዮሎጂ፣ በማህበራዊ ህክምና እና የጤና ሥርዓት ጥናት ክፍል አስተምረዋል።
ወደ ጀርመን ከተመለሱ በኋላ በ1990ዎቹ መጨረሻ በሃኖቨር ክልል በአካባቢ ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ ጀመሩ፤ ከ2003 እስከ 2005 በታችኛው ሳክሶኒ ግዛት የመንግሥት ካቢኔ ሆነው አገልግለዋል።
ቮንደር ሊየን የፌዴራል ካቢኔ አባል ከሆኑ ከ2005 እስከ 2009 የቤተሰብ ጉዳይ እና ወጣቶች ሚኒሥትር፣ ከ2009 እስከ 2013 የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒሥትር፤ በመጨረሻም ከ2013 እስከ 2019 የመጀመሪያዋ ሴት የመከላከያ ሚኒሥትር ሆነው አገልግለዋል፡፡
እ.አ.አ በ2015 በአውሮፓ፣ በኔቶ፣ በሩሲያ በተከሰተ ውጥረት ምክንያት ሰራዊቱን ሙሉ በሙሉ ለማዘመን የጀርመን የመከላከያ ወጪ እንዲጨምርም አድርገዋል፡፡ ይህን ተከትሎም በግንቦት 2015 የጀርመን መንግሥት የመከላከያ ወጪን በአንድ ነጥብ ሦስት ከመቶ፣ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ በስድስት ነጥብ ሁለት ከመቶ እንዲጨምር አድርገዋል፡፡ በዚህም የታንክ መርከቦችን ቁጥር ወደ 328 ለማስፋፋት፣ 131 ተጨማሪ መሳሪያ (ቦክሰሮች) የታጠቀ የሰው ኀይል አጓጓዦችን ለማዘዝ፣ የባህር ሰርጓጅ መርከቦችን ለመጨመር እና ቶርናዶን የተሰኘውን የሚተካ አዲስ ተዋጊ ጄት ለማዘጋጀት ተችሏል። በዚህም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ የመከላከያ ሚኒሥቴር ሰራዊቱን ሙሉ በሙሉ ማዘመን ችለዋል፡፡
ኡርሱላ ቮንደር ሊየን ሥራቸውን ለቀው ሲወጡ ሜርክል ቻንስለር ከሆኑ በኋላ በሜርክል ካቢኔ ውስጥ ያለማቋረጥ ያገለገሉ ብቸኛ ሚኒሥትርም ነበሩ። እ.ኤ.አ ከ2010 እስከ 2019 የሲዲዩ ምክትል መሪ ሆነው ያገለገሉት ሲሆን ሜርክልን በመተካት የጀርመን ቻንስለር ሆነው ለመሾም እንደ መሪ ተፎካካሪ እና ከጄንስ ስቶልተንበርግ በኋላ የኔቶ ዋና ፀሀፊ ለመሆን ተመራጭ ተደርገው ይታዩ ነበር።
የማዕከላዊ ቀኝ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ህብረት (ሲዲዩ) እና ተባባሪው የአውሮፓ የፖለቲካ ፓርቲ የአውሮፓ ሕዝቦች ፓርቲ (ኢ.ፒ.ፒ.) አባልም ናቸው። ኡርሱላ ቮንደር ሊን በታህሳስ 1 /2019 ለአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የተመረጡ የመጀመሪያዋ ሴት ሆነዋል።
እ.አ.አ በኖቬምበር 2022 ኮሚሽነሯ ለሩሲያ ፌዴሬሽን ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለማቋቋም እንደሚሠራም አስታውቀዋል። እ.አ.አ ማርች 7 ቀን 2024 የአውሮፓ ፓርላማ ምርጫ ዘመቻውን እንዲመሩ ኢፒፒ እንደ እጩ አድርጎ መረጣቸው። በጁላይ 2024 ደግሞ ኮሚሽኑን እንዲመሩ በድጋሚ ተመርጠዋል።
ቮንደር ሊን የታቀደውን የአውሮፓ ህብረት የነጻ ንግድ ስምምነትን ደግፈዋል። እሱም ከዓለም ትልቁ የነጻ ንግድ አካባቢዎች አንዱ ሆኗል። ቮንደር ሊየን በሴፕቴምበር 10 ቀን 2019 በርካታ ኮሚሽነሮችን በመሰየም አዲሱን የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን አወቃቀር “ጂኦፖሊቲካል” መደበኛ እና የበለጠ ግብ ላይ ያተኮረ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ በዚህም የአውሮፓ የሕይወት መንገድ ለስደት፣ ለደህንነት፣ ለሥራ እና ለትምህርት ፖሊሲዎች ማስተባበር ኃላፊነት ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቷ የዚህ ተቋም አካል ሆነው በሚቆዩበት ወቅትም የአውሮፓ ሕግን የፖለቲካ አቅጣጫ እና ሎጂስቲክስ አተገባበር ላይ በኃላፊነት ሠርተዋል፡፡ ተጠሪነታቸው ለሁለቱም የአውሮፓ ፓርላማ እና የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት የሆነው ኡርሳላ ቮንደር ሊን የአውሮፓ ኮሚሽነሮችን የመመደብ፣ የማሰናበት ፣ የማዋቀር እና የኮሚሽኑን ሲቪል ሰርቪስ የመምራት ከፍተኛ ኃላፊነታቸውን ፕሬዝዳንቷ በኃላፊነት በመወጣት ላይ መሆናቸውን መረጃው ጠቆሟል፡፡ ለአውሮፓዊያኑ ዓመታዊ የኅብረቱ ውይይትም ሁልጊዜም ንግግር ያደርጋሉ፡፡
እ.አ.አ. ማርች 4/2025 ቮንደር ሊየን የአውሮፓ ህብረት 800 ቢሊየን ዩሮ (840 ቢሊየን ዶላር) ለመከላከያ ኢንቨስትመንት ዕቅድን (“ReArm Europe” ) አስታውቀዋል። የአውሮፓ ኅብረት በአባል ሀገራቱ የመከላከያ ወጪን ለማመቻቸት ብሔራዊ ዕዳን በሚመለከት ሕጎቹን ማስተካከል ሊያስፈልገው እንደሚችልም ጠቁመዋል።
“የዓለማችን ጠንካራ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴት” በማለት ሁለት ጊዜ ታይም መጽሔት ለንባብ አብቅቷታል፡፡ ለአውሮፓ ላደረጉት አስተዋፅኦ እና ለውህደቱም የዘንድሮውን የቻርለማኝ ሽልማት አግኝተዋል። በጀርመን አቼን ከተማ በየዓመቱ የሚካሄደው የቻርለማኝ ሽልማት ለአውሮፓ አንድነት ትልቅ አስተዋፅዖ ያደረጉ ግለሰቦችን ያከብራል። የቮንደር ሊየን አመራር በጂኦፖለቲካል ውዥንብር ፣ በኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት እና በአረንጓዴ ሽግግር ወቅት የተመረጡበት ዋና ምክንያት እንደሆነ ተብራርቷል።
የመረጃ ምንጮቻችን አናዶሉ ፣ ሬውተርስ እና ዊኪፒዲያ ናቸው፡፡፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም