ወራሪዎች
ብሪታኒያ በአውሮፓ ትልቁ ደሴት ነው። በ94 ሺ ስኩዌር ኪሎሜትር መሬት ላይ ያረፈ ደሴት ሲሆን ለረጅም ዘመናት ያህል ከአውሮፓ ጋር በየብስ የተገናኘ የአህጉሩ አካል ሲሆን ምናልባትም ከ6500 ቅ.ዓ በኋላ መሬቱ በውሃ ተውጦ ከእናት ምድሩ ተለይቶ በውሃ የተከበበ ደሴት ሆኖ እንደቀረ ታሪኳ ያስረዳል። ኢንግላንድ፣ ዌልስ እና ስኮትላንድ የተባሉ የተለያዩ ሀገረ መንግሥታትን አዋህዶ ታላቋ ብሪታኒያ የተባለ ምድር ነው። የመጀመሪያዎቹ ሰፋሪዎች ከሰሜን አውሮፓ የተሰደዱ የሴልቲክ ነገዶች ነበሩ። እነዚህ ነገዶች ጥበብ አዋቂ እና በቴክኒክ የተካኑ ነበሩ። በብሪቴይን ለረጅም ዘመናት ጎበዝ ገበሬ፣ ጎበዝ ነጋዴዎች እና አንጥረኞች ሆነው አካባቢያቸውን አልምተዋል። እናም ብሪቴንን ለወጧት።
የብሪታኒያ ምድር ተስማሚ የአየር ንብረት እና የዘመናት ሰላም ውጤት የሆነ ባለፀጋ የሆኑበት ዘመን ቢኖር አራተኛው ክፍለ ዘመን ነበር። ይህ ብዙዎችን በማማለል በየጊዜው እንድትወረር አድርጓት ቆይቷል። ከአራት ክፍለዘመን በላይ በቅኝ ግዛት ስር አድርጎ ያቆያት የሮማውያን አስተዳደር ከምድሪቱ መወገዱን ተከትሎ በአምስተኛው ክፍለ ዘመን ላይ ከሰሜናዊ ጀርመን የተነሱ አንገል፣ ሳክሶን እና ጁት የተሰኙ ነገዶች ብሪቴንን በተለያዩ አቅጣጫዎች ወረሯት።
ጁቱዎች በምስራቅ በዋናነት በኬንት እና በደቡቡ ዳርቻ ይዘው ሰፈሩ። አንገሎች በምስራቅ በኩል በሰሜን መሃል ምድሮች ላይ ሲሰፍሩ ሳክሰኖች ደግሞ በጁቶች እና በአንገሎች መካከል ያለውን ምድር ይዘው ወደ ምእራብ አቅጣጫ ሰፈሩ። የአንግሎ ሳክሰኖች ስደት የብርቴንን ሰፊውን ክፍል ኢንግላንድ የሚል ስም አስገኝቶለታል፣ ኢንግላንድ የአንገሎች ምድር እንደማለት ነው።
የብሪታኒያ ሴሷልቲክ ሕዝቦች የጀርመን ጎሳዎችን እና ሰፈራዎችን በቻሉት አቅም ተዋግተዋል። ይሁን እንጂ አዲስ መጤዎቹ ነገዶች ጦረኞች እና ያልተማሩ ስለነበሩ በቀጣይ መቶ ዓመታት ውስጥ እስከ 562 ዓ.ም ድረስ ቀስ በቀስ ከመሀል ወደ ምእራብ አቅጣጫ እየተገፉ ሄዱ። በመጨረሻም አብዛኞቹ ሴልቲኮች፣ ሳክሰኖች የዉጭ ሰዎች ምድር እንደማለት “ዌልስ” ብለው ወደሚጠሩት በምእራብ ጫፍ ውስጥ ወዳሉት ተራሮች ተገፍተው ወጥተዋል።
አንዳንድ ሴልቶች ወደ ኮርን ዌል ተሰደዱ። በሰሜን በኩል ደግሞ ሌሏሎች ሴልቲኮች በኋላ ላይ ስኮትላንድ ወደተባለችው ሀገር ደጋማ ክፍል እንዲሰደዱ ተደርገው ነበር። ከ442 እስከ 750 ዓ.ም ድረስ ብሪታኒያን በአንግሎ ሳክሰን ስደተኞች ወደ ሰባት ኪንግደሞች ተከፈለች። ኖርዙምብራ፣ መርሲያ፣ ዌሴክስ፣ ኢሴክስ፣ ሱሴክስ እና ኬንት ይባሉ ነበር። በእንግሊዝ ውስጥ የእነዚህ ነገዶች ተጽእኖ እስከ አሁን ድረስ በእንግሊዝ ከተሞች ስም ላይ ይታያል::
ለአብነት የእንግሊዝ ከተሞችን ብናነሳ መጨረሻው ላይ ኤይ ኤን ጂ ያለባቸው ከተሞች አሉ፤ ሪዲንግ እና ሃስቲንግ ይጠቀሳሉ:: ሪዲንግ ማለት የራዳ ቤተሰብ ርስት እንደማለት ነው:: ሃስቲንግ ደግሞ የስታ ቤተሰብ ርስት እንደማለት ነው:: በመጨረሻቸው ሃም የሚል ቃል የሚያስከትሉ ስሞች የእርሻ ቦታን ለመግለጽ አንግሎ ሳክሰኖች የሰጧቸው ስሞች ሲሆኑ ዌስትሃም፡ ቢርሚንግሃም፤ ፉልሃም የተባሉት ከተሞች ምስክር ናቸው።
ብሪታኒያ ውስጥ የእንግሊዝን ጠንካራ ኪንግደም የመሰረቱት አንግሎ ሳክሰኖች ወደ ዌልስ እና ስኮትላንድ ሰፍረው የራሳቸውን መንግሥታት የመሰረቱትን ኪንግደሞች በማስገበር እና ታላቋን ብሪታኒያ ለመገንባት በየጊዜው የእርስ በእርስ ጦርነት ያደርጉ ነበር። የኢንግላንድ ነገሥታት ዌልስን እና ስኮትላንድን በማካተት ታላቋን ብሪታኒያ መመስረት የሚለው እቅድ ግን ከፍተኛ ሂደት ማለፍ ግድ ነበር። ብሪታኒያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስራዎችን የከወኑ ነገሥታትን እና ስራዎቻቸውን እንቃኝ።
አልፍሬድ
አንግሎ ሳክሰኖች በኢንግላንድ ምድር ላይ ብዙ ትናንሽ ነገዶችን መስርተው ነበር:: ከዚያም ከዴንማርክ የተነሱ ወራሪዎች በ9ኛው ክፍል ዘመን ማብቂያ ላይ ኢንግላንድን ይወራሉ። ይሁን እንጂ በወቅቱ የሳክሰኖች ንጉሥ ታላቁ አልፍሬድ ወራሪውን ሀይል በጀግንነት መክቶ አስቆመው:: ከዚያ ወዲያም ነው ከአልፍሬድ የዘር ሀረጋቸው በሚመዘዝ ነገሥታት አማካኝነት ኢንግላንድ ወደ አንድ ሀገርነት የተዋሃደችው።
ዊሊያም ቀዳማዊ
በ1058 ዓ.ም ደግሞ ከወደ ሰሜን አቅጣጫ በሰሜናዊት ፈረንሳይ የኖርማንዲ መስፍን በነበረው ዊሊያም የተመሩት ኖርማኖች በሀስቲንግ ጦርነት ላይ አንግሎ ሳክሰኖችን ድል ነስተው ኢንግላንድን ወርረው ነበር:: ‘ዊሊያም ወራሪው’ በሚል ቅፅል የሚጠራው የጦር መሪ የኢንግላንድ ንጉስ ተብሎ ዘውድ ጫነ:: በጊዜ ሂደትም ኖርማኖች እና አንግሎ ሳክሰኖች የተዋሃዱ አንድ ሕዝብ ሆነዋል:: ኖርማኖች መጀመሪያ ላይ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ቢሆኑም በመጨረሻም ከአንግሎ ሳክሰኖቹ ቋንቋ ጋር በማዳቀል የዛሬው የእንግሊዝኛ ቋንቋ እንዲጀመር አድርገዋል::
ዊሊያም አንደኛ በእንግሊዝ ታሪክ ውስጥ ጠንካራ አህዳዊ መንግሥት እንዲመሰረት መሰረቱን የጣለ ሰው ነበር:: የሀገሪቱን መስራች የአንግሎ ሳክሰኖቹን መሬት በመቀማት ለተከታዮቹ ለኖርማንዴዎች አከፋፍሎ እስከመስጠት ደርሷል:: በመጨረሻ በመላ ኢንግላንድ ሰፊ ጠንካራ ዘውዳዊ ስልጣን መገንባት ችሎ ነበር የሞተው::
ዳግማዊ ሔነሪ
ከቀዳማዊ ዊሊያም አንድ መቶ ዘመን በኋላ ኢንግላንድ በሌላ ወሳኝ መሪ ተገዝታለች፤ በዳግማዊ ሔነሪ:: ይህ የአንግሊዝ ታላቅ ንጉሥ የእንግሊዝ መንግሥትን እና ሕግ ገንቢ በመሆኑ ይታወቃል:: የዳኝነት ሥርዓት ያደገው በዳግማዊ ሔነሪ ሥር ነበር:: በጊዜው በወንጀል የተከሰሱ ግለሰቦች በፍርድ ችሎት የሚዳኝበት ስርዓት በኢንግላንድ ጥቅም ላይ ውሎ ነበር::
ንጉሥ ዮሐንስ
በኢንግላንድ አስጨናቂ ጊዜያትን ያመጣ መሆኑ የሚነገርለት ንጉሥ ዮሐንስ የሔነሪ ታናሹ ልጅ ነበር:: ሴረኛና ጨካኝ ነበር:: ንጉሥ ዮሐንስ አባቱን ከሥልጣን ለማውረድ የሞከረ እና ሪቻርድ ልበ አንበሳው እየተባለ በሚታወቀው ታላቅ ወንድሙ ላይም ሴራ ሲጎነጉን ነበር::
ዮሐንስ ንጉሥ የሆነው በ1191 ዓ.ም ላይ ንጉሥ ሪቻርድ ከሞተ በኋላ ነበር:: በእርሱ የስልጣን ዘመን ወቅት ዮሐንስ ከባሮች እና ከሀይማኖት መሪዎች ዘንድ ጠላቶች አፍርቷል:: ኢንግላንድ ፈረንሳይ ውሰጥ ይዛው ከነበረው አብዛኛውን መሬት አጥቷል፤ እንዲሁም ከአቡነ ኢኖሰንት ሳልሳዊ ጋር ተጣልቷል:: የዮሐንስን ስልጣን ለማሣነሥ በተደረገ ሙከራ ከባሮች እና የቤተክርስቲያን መሪዎች የተውጣጣ አንድ ቡድን የተሃድሶ ጥያቄ ያነሡበት እና ከዚያም ያምጹበታል:: በ1207 ዓ.ም ማግና ካርታ እየተባለ በሚታወቀው ሰነድ ላይ እንዲስማማ አስገድደውት ነበር:: ቻርተሩ ንጉሡን ከሕግ በታች ያስቀመጠ እና ስልጣኑን የወሰነ ነበር::
ኤድዋርድ እና ፓርላማ
የተወካዮች ም/ቤት ወሳኝ ሆኖ የታየው በ13ኛው ክ/ ዘመን ማብቂያ ላይ በዮሐንስ የልጅ ልጅ በቀዳማዊ ኤድዋርድ የስልጣን ዘመን ነበር:: ም/ቤቱ ሁለት ቅርንጫፎች ነበሩት:: የጌቶች ምክር ቤት የሚባለው መሪ ባላባቶች እና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚሳተፉበት እና ሁለተኛው የሕዝብ ተወካዮች የሚባለው ሲሆን የጦር አበጋዞች፣ አነስተኛ የመሬት ከበርቴዎች የቤተክርስቲያን መሪዎች እና የከተሞች ተወካዮች የሚካተቱበት በሚል በ1289 ዓ.ም ኤደዋርድ ያለፓርላማው ፈቃድ የተወሠነ ግብሮችን ላለመሠብሠብ ተስማምቷለ:: ፓርላማውም ቀስ በቀስ በኢንግላንድ መንግሥት የሕግ አውጪው አካል ወደ መሆን አድጓል::
የዌልስ በኢንግላንድ ሥር መሆን
በ1275 ዓ.ም ቀዳማዊ ኤድዋርድ ዌልስን እና ስኮትላንድን ለመያዝ ተደጋጋሚ ጦርነቶችን አካሂዷል:: እናም በ1275 ዓ.ም ዌልስን በኢንግላንድ ሥር በማድረግ ልጁን የዌልስ ልዑል ብሎ ሾመው:: በኋላ ላይ ዳግማዊ ኤድዋርድ የተባለውን ማለት ነው። ቀዳማዊ ኤድዋርድ በተጨማሪም ስኮትላንድን ለመውረር ሞከሮ ነገር ግን ስኮቶች የኤድዋርድን ኃይል ታግለው በማሸነፍ ለ300 ዓመታት ያህል ነፃነታቸውን አስከብረዋል::
የቱዶር ቤተሠብ
የኖርማንዲው ዊሊያም በሀስቲንግ ጦርነት ላይ አንግሎ ሳክሰኖችን ድል ባደረገበት በ1058 ዓ.ም እና የቱደር ቤተሠብ ስልጣን በያዙበት በ1477 ዓ.ም መካከል ባሉት 400 ዓመታት ውስጥ ኢንግላንድ ይበልጥ የተዋሃደች ሀገር የሆነችበት እና ንጉሣዊ ሥልጣን የጨመረበት ታላቅ ወቅት ነበር::
ከ1477 -1595 ዓ.ም ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ የቱዶር ቤተሠብ ኢንግላንድን በመምራት እና ንጉሣዊ ሥልጣንን በማጠናከር ቆይቷል::
ንጉሥ ሔነሪ 7ኛ
በመጀመሪያ የቱዳሩ ሔነሪ በ1477 ዓ.ም ቦስ ወርዝ ላይ የተደረገውን ጦርነት በማሸነፍ ዘውድ ደፋ እና ንጉሥ ሔነሪ 7ኛ ተባለ:: ሔነሪ ይቃወሙት የነበሩትን የፊውዳል ባላባቶች እየጠራረገ አስወገደ::
ንጉሥ ሔነሪ 8ኛ
ከሔንሪ 7ኛ ቀጥሎ ልጅ ሔነሪ 8ኛ በ1501 ዓ.ም የኢንግላንድ ንጉሥ ሆነ:: ሦስት ልጆች ነበሩት፣ ኤድዋርድ፣ ሜሪ እና ኤልዛቤጥ:: በ1524 ዓ.ም በኢንግላንድ የቤተክርስቲያን ከፍተኛ ባለሥልጣን ንጉሡ እንጂ ጳጳሱ አለመሆናቸውን የሚደነግግ ሕግ ፓርላማው እንዲወሰን አድርጓለ:: ይህን ተከትሎም የእንግሊከን ቤተክርስቲያን ተቋቁሟል:: በአርሱ ዘመን ዌልስና ኢነግላንድ በመጨረሻ ውህደት የፈጠሩበት ነበር:: ሔንሪ 8ኛ ኢንግላንድን ኅያል አድርጓታል::
ኤድዋርድ 5ኛ
በ1539 ዓ.ም አርባ ዓመታት ከሚጠጋ የሥልጣን ቆይታው በኋላ ሔነሪ 8ኛ ሞተ:: በቦታውም በሕመም የሚቸገረው ልጁ ኤድዋርድ 5ኛ ነገሰ:: ነገር ግን ጥቂት ዓመታት ብቻ ነበር የገዛው::
ንግሥት ሜሪ
ቀጥሎ የመጣው ንጉስ ሳይሆን ከሔነሪ ሴት ልጆች አንዷ ሜሪ ንግሥት ሆና በእንግሊዝ ዙፋን ላይ ተቀመጠች:: ለኤድዋርድ 5ኛ በግማሽ እህቱ ናት:: ሀቀኛ የካቶሊክ አማኝ ነበረች:: በመሆኑም ካቶሊክ የሀገሪቱ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን እስከማድረግ ደርሳለች:: ለአምስት ዓመታት ብቻ ነበር ኢንግላንድን የመራችው:: ንግሥት ሜሪ ከሔነሪ የመጀመሪያ ሚስቱ ንግሥት ካትሪን የተወለደች ልጁ ናት::
ቀዳማዊት ኤልሳቤት
በመቀጠል በእንግሊዝ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ ያላት ቀዳማዊት ኤልሳቤት ናት:: ቀጣይ የኢንግላንድ መሪ ንግሥት ቀዳማዊት ኤልዛቤት ዘውድ ደፋች:: በ1550 ዓ.ም የኤልዛቤት የስልጣን ዘመን የሚባልለት ነበር::
ቀዳማዊት ኤልዛቤት ጠንካራ እና ጠላቶቿን አንድ በአንድ ያጠፋች ጥንቁቅ መሪ ነበረች:: ከመጀመሪያ ስራዎቿ መካከል አንዱ የኢንግላንድን ቤተ ክርስቲያን እንደገና ማቋቋም ነበር:: ኢንግላንድ በቀዳማዊት ኤልዛቤት ዘመን በተለያዩ መስኮች እመርታ አሳይታለች:: ነጋዴዎች ኢስት ኢንዲያ ካምፓኒ የተሰኘ ታላቅ የንግድ ኩባንያ በ1592 ዓ.ም የተመሰረበውም በእርሷ ዘመን ነው።
በቀዳማዊት ኢልዛቤት ዘመን ኢንግላንድ ወቂያኖሱን መቆጣጠር የቻለ የባህር ኃይል የገነባችበት ነበር:: የታላቋ እንግሊዝ መርከቦች ሩቅ የሚባሉ አህጉራትን እያሰሱ አግኝተዋል::
(መሠረት ቸኮል)
በኲር የግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም