ሕጋዊ የዘር አቅርቦት ለምርታማነት

0
67

የአማራ ክልል ግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ጋር በመተባበር የተሻሻለውን የዘር አዋጅ 1288/2015 ለባለድርሻ አካላት አስተዋውቋል። በሕገ ወጥ ዘር ቁጥጥር ላይም በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አድርጓል። በመድረኩ በክልሉ የሚገኙ የፍትሕ አካላት፣ ግብርና ቢሮ፣ የሕገ ወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረ ኃይል፣ ንግድ ቢሮ፣ የመንግሥት እና የግል ዘር አምራች ድርጅቶች ተወካዮች፣ የአማራ የግብርና ጥራትና ደኅንነት ባለስልጣን የጥራት ቁጥጥር አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

 

ሕገ ወጥ የዘር ዝውውር ቁጥጥር በአማራ ክልል ያለበት ሁኔታ፣ ችግሩን ለመከላከል ስለሚደረግ ጥረት እና ተግዳሮቶችን በተመለከተ በውይይቱ ተነስቷል። ሕገ ወጥ አካላት ጥራቱን ያልጠበቀ ዘር በማሰራጨት እና በማከፋፈል አርሶ አደሩን እየጎዱ በመሆናቸው ሁሉም አካል በባለቤትነት ሕገ ወጥ ድርጊትን መከላከል እንደሚጠበቅበት ተመላክቷል።

በውይይቱ እንደተብራራው ሕገ ወጥ ዘር፣ ዝውውር እና አቅርቦት የሚባለው ትክክለኛ ያልሆነ ዘርን ጨምሮ ፈቃድ ሳይኖር ማምረት እና ማዘዋወር፣ ባልተገባ ሥፍራ ማከማቸት እና ማቅረብ እንዲሁም ባልተፈቀዱ ቦታዎች መገበያየት ነው።

በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው የምክክር መድረኩ አንዱ ዓላማ መደበኛ የዘር አቅርቦት የሚመራበትን ሥርዓት ማሳለጥ መሆኑን ተናግረዋል። የአማራ ክልል ምጣኔ ሀብት የተመሠረተው በግብርናው ዘርፍ በመሆኑ ግብርናውን መደገፍ እና ማዘመን ይጠበቅብናል ብለዋል።

 

እንደ አቶ አጀበ ማብራሪያ ክልሉ ከሚሠራባቸው የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ የተሻሻለ ዘር በማቅረብ ምርታማነትን ማሳደግ እና የምርጥ ዘር አጠቃቀም ሽፋንን ማሳደግ ነው። አርሶ አደርን በአግባቡ ማገልገል ካልተቻለ ደግሞ ምጣኔ ሀብትን ማሳደግ አይቻልም። በመሆኑም አርሶ አደሩን በሚገባው ልክ ማገልገል እንደሚገባ በመጠቆም የተሻሻለ የሰብል ዘር ማቅረብ አንዱ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

በአማራ ክልል የዘር አቅርቦት በሁለት መንገድ ነው እየቀረበ የሚገኘው፤ እነዚህም መደበኛ እና ኢመደበኛ የዘር አቅርቦት ናቸው። ለአማራ ክልል በመደበኛ የዘር አቅርቦት ሥርዓት የሚቀርበው ምርጥ ዘር ከ10 በመቶ አይበልጥም ሲሉም አቶ አጀበ ይናገራሉ። በአርሶ አደሮች ባሕላዊ ሥርዓት የሚቀርበው መደበኛ ያልሆነ የዘር አቅርቦት ያለበትን ውስንነት በማሻሻል ወደ መደበኛ ሥርዓቱ መለወጥ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው እንዳሉት የመደበኛ የዘር አቅርቦቱ በቂ አለመሆን እና የሕገ ወጥ ዘር እንቅስቃሴ የአርሶ አደሩን ልማት እያደናቀፈው ነው፤ ለምርት ዕድገትም ማነቆ ሆኗል።

 

ዘርን ለምግብነት ማዋል፣ በሕገ ወጥ መንገድ ማዘዋወር እና ቀለም በመቀባት ዘር ያልሆነን ዘር ነው ብሎ ለአርሶ አደሩ መሸጥ በምርታማነቱ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ ነው። ችግሩን በመፍታት ምርትን ለማሳደግ ታዲያ የልማት እና የሕግ አካላት ተቀናጅተው መሥራት ይገባቸዋል ሲሉ ነው አቶ አጀበ ያሳሰቡት። ከዚህ ጋር በተገናኘ ሕገ ወጥ የዘር ዝውውርን እና አቅርቦትን ለመከላከል በአዋጅ ሕጋዊ ድጋፍ ማግኘቱ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን በውይይቱ ተስተጋብቷል። ሕጉን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ ቁርጠኛ ሆኖ መሥራት እንደሚገባ አቶ አጀበ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊ ዘላለም ልየው እንደተናገሩት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ከተሰጠው ተግባር እና ኃላፊነት አንዱ ከምርምር የሚወጡ ዘሮችን ጥራት እና ደኅንነት ተጠብቆ ለአርሶ አደሮች ማድረስ ነው፡፡ አዋጁ ደግሞ ሕገ ወጥ አምራች፣ አከፋፋይ እና ቸርቻሪዎችን ለመቆጣጠር ይረዳል። ጥራቱን የጠበቀ ዘር እንዲመረት እና ተጠያቂነትን በማስፈን አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆንም ያደርጋል።

 

አጋር አካላት (ግብርና፣ ማኅበራት፣ ንግድ፣ ፖሊስ፣ ፍትሕ፣ ፍርድ ቤት እና ሌሎችም ተቋማት) የሕገ ወጥ ዘር ዝውውርን እና አቅርቦትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የመተባበር ኃላፊነት እንዳለባቸው አቶ ዘላለም አስገንዝበዋል። በመጋዝን ላይ የሚገኙትን ዘሮች ከፍተኛ ቁጥጥር ተደርጎባቸው ጥቅም ላይ እንደሚውሉ በማንሳትም በክልሉ በሚመረቱ ምርጥ ዘሮች ላይ ከመጀመሪያው ለዘር እስኪዘጋጁ ድረስ ከፍተኛ የጥራት ቁጥጥር እየተደረገ ስለመሆኑ ነው ያብራሩት፡፡ ለማሳያም በዚህ ዓመት የዘር ጥራት ቁጥጥር የተወሰኑ ጉድለቶች ቢኖሩም ከባለፉት ዓመታት የተሻለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

 

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሚመረትን ዘር በየደረጃው ቁጥጥር እንደሚያደርግ የተናገሩት አቶ ዘላለም በተሠሩ ሥራዎችም እስከ አምስት ሺህ ኩንታል ጥራት የሌለው ምርጥ ዘር ውድቅ መደረጉን ተናግረዋል። ጥራት የሌለው ዘርን የሚያመርቱ እና የሚያከፋፍሉ ቢገኙ እስከ ፈቃድ መንጠቅ የሚደርስ ሥራ እንደሚሠራም ነው ያስረዱት። የእርምት እርጃ የተወሰደባቸው አምራቾች መኖራቸውንም ገልፀዋል። በመሆኑም ጥራት ያለው የሰብል እና የእጽዋት ዘር ለማቅረብ በትኩረት እየተሠራ ስለመሆኑም ነው ያብራሩት።

ዘር የሚያመርቱ፣ የሚያከፋፍሉ እና የሚቸረችሩ አካላት ሕጋዊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ዘርን ከባዕድ ነገር ከመቀላቀል፣ መጠኑን ከመቀነስ እና አመሳስሎ ከማቅረብ መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስበዋል። ጥራቱን ያልጠበቀ ዘር ለአርሶ አደሩ ማሠራጨት “ምርትን ማምከን ነው” ብለውታል።

 

“ዘር መድኃኒት ነው” ያሉት አቶ ዘላለም ተባብሮ በመሥራት ሕገ ወጥ የዘር ዝውውርን እና ግብይትን በመከላከል “አርሶ አደሩን ከጉዳት የማዳን ኃላፊነት አለብን” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደመቀ ወንዶች በበኩላቸው እንዳብራሩት የፖሊስ ዋና ተግባሩ ወንጀልን (ሕገ ወጥ ድርጊትን) ቀድሞ መከላከል፣ መከታተል፣ ማጣራት፣ መቆጣጠር፣ ሕግን ማስከበር እና አጥፍተው ሲገኙም በምርመራ አጣርቶ ለሕግ በማቅረብ ሌላውም እንዲማርበት ማድረግ ነው። ተቋሙ በምርጥ ዘር ላይ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን የመከላከል ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ያነሱት ኮማንደር ደመቀ “ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል። ኮማንደር ደመቀ እንዳሉት በዚህ ዓመት በተሠራው ጠንካራ የቁጥጥር ሥራ ጥፋተኞች ከጥፋታቸው እንዲማሩ እና ሕጋዊ መስመር እንዲይዙ ተደርጓል። ወንጀልን መከላከል የጋራ ተግባር  በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

 

በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር ሙሉጌታ አሻግሬ እንዳሉት ጥራቱ የተጠበቀ ዘር ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ በየደረጃው የሚገኘው የፍትሕ ተቋም መከላከልን ጨምሮ ሕገ ወጥ የዘር ዝውውር ተፈጽሞ ሲገኝ ለሕግ በማቅረብ አጥፊዎችን ተጠያቂ ያደርጋል። ዘርን ከማምረት ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው ድረስ የሚኖረውን ግብይት እና ዝውውር ሕጋዊ ለማድረግ እና ወንጀሎችን ለመከላከል የጋራ ግንዛቤም ተፈጥሯል።

ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት በቀጣይም በክልል ደረጃ የተጀመሩ መልካም ሥራዎችን እስከ ወረዳ ድረስ ወጥነት ባለው መልኩ በመተግበር እና ክፍተቶችን በማስተካከል ሕገ ወጥ የዘር ዝውውርን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው።

 

በኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የዕጽዋት ዝርያ እና ዘር ተቆጣጣሪ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ፍስሃ ተሾመ ውይይቱ ሕገ ወጥ የዘር ዝውውርን የሚመለከተው አዋጅ፣ የማስፈፀሚያ ደንብ እና መመሪያ ላይ በመወያየት ግልጽነትን ለመፍጠር መሆኑን ተናግረዋል። ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት የግንዛቤ ፈጠራ እና የቁጥጥር ስልቶችን በመቀየስ ለመሥራት ዝግጅት መደረጉንም አስረድተዋል።

አቶ ፍስሃ እንዳሉት በሕገ ወጥ የዘር አቅርቦት ላይ ጥናት ተደርጓል፤ በዚህም በበቆሎ እና አትክልት ዘሮች ላይ ሕገ ወጥ የዘር አቅርቦት የሰፋ መሆኑ ታይቷል።

 

ያልተገቡ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ጉዳቱ በርካታ ስለሆነ በመድረኮች እና በሁሉም አማራጮች የማሳወቅ ሥራም እየተሠራ መሆኑን አቶ ፍስሃ ገልጸዋል። ያልተገቡ ዝርያዎችን አርሶ አደሩ ከተጠቀመ ለበሽታ ከመጋለጥ ጀምሮ ምርታማነታቸው በእጅጉ ይቀንሳልም ብለዋል። በመሆኑም የሕገ ወጥ ዘር ዝውውርን የቁጥጥር ስልቱን በማዘመን መሥራት እንደሚጠይቅ አመላክተዋል።

ዘርን ከባዕድ ነገር ጋር መቀላቀል፣ መንከር እንዲሁም ማሸጊያዎችን በመጠቀም አስመስሎ ማቅረብ በሕገ ወጥ የዘር አቅርቦት የተፈረጁ ናቸው። ሕገ ወጥ የዘር ዝውውር እና አቅርቦት በኅብረተሰቡ ዘንድ ግልጽነት ተፈጥሮበት ወንጀሉን መከላከል ይቻል ዘንድ የሚዲያ አካላትም ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ተጠይቀዋል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here