የእብድ ውሻ በሽታ

0
115

የእብድ ውሻ በሽታ ከክርስቶስ ልደት በፊት ማለትም ከ2300 ዓ.ዓ በፊት የነበረ ነው፡፡ ባቢሎን በሚባው ዘመን የውሻ ባለቤቶች ውሻዎቻቸው  የነከሱት ሰው ከሞተ ቅጣት ይጠብቃቸው ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ደግሞ የእብድ ውሻ በሽታ የታወቀው ከጣሊያን ወረራ ጀምሮ   ነበር፡፡ በኢትዮጵያ በፈረንሳይ ድጋፍ ፓስተር የጤና ኢንስቲትዩት በ1944 ሲቋቋም ለእብድ ውሻ በሽታ ክትባት እንዲሰጥ ታስቦ ነበር፡፡ ይህን የነገሩን በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መምህር እና የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት፤ በአዲስ ምዕራፍ ስፔሻሊቲ ክሊኒክ ሀኪም  ዶ/ር ግዛቸው ደምስ ናቸው፡፡

 

ዶ/ር ግዛቸው  እንደገለጹት የእብድ ውሻ በሽታ  ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ እና ገዳይ ነው፡፡ በሽታው እጅግ ጥቃቅን በሆኑ በኤሌክትሮ ማይክሮስኮፕ የሚታዩ ከባክቴሪያዎች ባነሱ ላይሳ (lyssavirus) በሚባሉ ቫይረሶች አማካኝነት ይከሰታል፡፡ ቫይረሶቹ  ከእንስሳት  ወደ  ሰው  ይተላለፋሉ፡፡ በእብድ  ውሻ  በሽታ  የተጠቁ  ሰዎች  ከሟቾች  ቁጥር  ጋር ሲነጻጸር የሞት መጠኑ  ከፍተኛ  ነው፡፡

አጥቢ እና ደመ ሞቃት እንስሳትን የሚያጠቃው የእብድ ውሻ በሽታ  አብዛኛውን ጊዜ በተለይ በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ የሚተላለፈው በውሻ አማካኝነት ነው፡፡ በበሽታው በተጠቁ እንስሳት (ድመትን ጨምሮ በሌሎች)    ወደ ሰው ይተላለፋል፡፡ ቫይረሱ ወደ ሰው ሰውነት በልሃጫቸው እና በምራቃቸው አማካኝነት ከገባ በኋላ በነርቭ ሴሎች ውስጥ ወደ ጭንቅላት ተጉዞ አንጎልና ህብለ ሰረሰር  ውስጥ ይራባል፣ ከዚያም እንደገና ወደ ምራቅ እጢዎች ይመለሳል።

 

የእብድ ውሻ በሽታ ምልክቶች ከታዩ በኋላ ግለሰቡ የመዳን እድሉ አነስተኛ እንደሆነ  የጠቆሙት ባለሙያው፤ አንድ ውሻ እንዳበደ ወይም እንደታመመ የሚታወቀው  ቁጡ ሲሆን፣ ባህሪው ከበፊቱ ሲቀየር፣ አሳደጊዎቹን እና ያገኘውን ሰው ሁሉ ሲነክስ፣ ብርሐን ፣ አየር እና ውኃ መፍራት ሲጀምር ነው፡፡ በተለይ በሽታው የጀመረው ሰሞን ውሻው ጉሮሮው መዋጥ ስለማይችል ውኃ መጠጣት አይችልም፡፡ በዚህም የውኃ ፍራቻ ይታይበታል፡፡ ለሃጩ እና ምራቁ ይዝረበረባል፡፡ መንቀሳቀስ ያቅተዋል፡፡ ከዚያም ተዝለፍልፎ በመውደቅ ይሞታል፡፡

በማሕበረሰቡ ዘንድ “ውሻ የሚያብደው ሲራብ እና ሲጠማ ነው” የሚለው አስተሳሰብ  በተለምዶ እንደሆነ  ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡  በመሆኑም የውሻ ባለቤቶች ውሻዎችን መንከባከብ (መመገብ፤ ማጠጣት) ቢኖርባቸውም  ውሾች የሚያብዱት ግን በእንክብካቤ ማነስ ሳይሆን በቫይረስ መሆኑን   ሊያውቁ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

 

ዶ/ር ግዛቸው እንዳብራሩት በእብድ ውሻ የተነከሰ ሰው በፍጥነት ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል፡፡ ይህ የሚሆነውም  ንክሻው አንገትና ጭንቅላት አካባቢ  ሲሆን፣ ብዙ የነርቭ ሴሎች በሚገኙበት ቦታ (ጡንቻዎች) አካባቢ ከሆነ፣ የተነከሰው ግለሰብ በሽታ የመከላከል አቅሙ ደካማ ሲሆን እና በዕድሜ የገፉ ሰዎች ምልክቶቹ በፍጥነት ይታይባቸዋል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ከጭንቅላታቸው እና ከትከሻቸው የራቀ አካባቢ የተነከሱ እና የዕብድ ውሻ በሽታ መከላከያ የወሰዱ እንዲሁም በሽታ የመከላከል አቅማቸው ከፍ ያለ ሰዎች ምልክቶቹ ከሦስት ወር እስከ አንድ ዓመት ድረስ ቆይቶ ሊታይባቸው እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡

 

በሰዎች ላይ የሚታየው የእብድ ውሻ በሽታ መኖሩ ማሳያ ቅድመ ምልክት  በመጀመሪያ  የተነከሰበት ቦታ ላይ የመጠዝጠዝ፣ የማቃጠል እና የመደንዘዝ ስሜት ይኖረዋል፡፡ ዝቅተኛ ሙቀት፣ መነጫነጭ፣ ማስታወክ እና ሆድ ቁርጠት ሊኖር ይችላል፡፡  በትክክል የውሻ በሽታ መሆኑን የሚናገሩ ምልክቶች የሚመጡት ደግሞ ከነዚህ ምልክቶች በኋላ እንደሆነ የተናገሩት የሕክምና ባለሙያው እነዚህ ጠቋሚ ምልክቶቹ ከአንድ ሳምንት እስከ ሁለት ሳምንት ሊቆዩ እንደሚችሉ፣ እንደየ ደረጃው እና እንደየ ሰው የሰውነት በሽታ የመከላከል  አቅምም ሊወሰን ይችላል፡፡

 

ከነዚህ ምልክቶች በኋላ የሚታዩት ግን በትክክል የውሻ በሽታ መሆናቸውን የሚያመላክቱ  ናቸው ይላሉ፤ ባለሙያው፡፡ እነሱም  የመጀመሪያው  ውኃ መፍራት ነው፣ ከፍተኛ የሆነ ሙቀት፣ የጉሮሮ ጡንቻዎች መወጠር፣ ምራቅን ጨምሮ ምንም አይነት ነገር ለመዋጥ ይቸጋራሉ፡፡ እንዲሁም የተነከሱበት ቦታ ቁስሉ   መጠዝጠዙ ይጨምራል፤ ይመረቅዛልም፡፡ 80 በመቶ  የሚሆኑት  ሰዎች ቁጡ የሆነውን አይነት (Encephalitic rabies )ሲያሳዩ ሌሎች 20 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ፓራሊቲክ (Paralytic rabies )  የሚባለውን ባህርያት ያሳያሉ። ኢንኬፋሊቲክ የሚባለው አይነት የእብድ ውሻ ምልክቶለቹም  ይነጫነጫሉ፣ የሚይዙትን የሚጨብጡትን ያጣሉ፣ ራሳቸውን አለማወቅና ልናከስ የማለት ባሕሪ ያሳያሉ፡፡ በመቀጠል ሰውነታቸው አልታዘዝ ወይም ሽባ ይሆናል፡፡ ብርሃን እና መንቀሳቀስ ይፈራሉ በመጨረሻም ዝም ሊሉ ይችላሉ፡፡

 

ዶ/ር ግዛቸው እንደሚሉት በእብድ ውሻ በሽታ የተነከሰ ሰው በመጀመሪያ ደረጃ ማድረግ ያለበት የተነከሰበትን ቦታ ከ10 እስከ 15 ደቂቃ በንጹህ ውኃ እና በሳሙና በደንብ ማጠብ፤ በፀረ-ተህዋሲያን (አልኮል እና አረቂን ጨምሮ ) ቁስሉ ላይ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህን ማድረጉም ቫይረሱ ወደ ሰውነት ዘልቆ የመግባት መጠኑን ይቀንሰዋል፡፡ ሌላው ውሻው በሽታው እንዳለበት በትክክል የተረጋገጠ ከሆነ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ፀረ-የእብድ ውሻ ክትባት መከተብ አለበት፡፡ መድኃኒቶችንም መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ውሻው ተይዞ ለብቻው ተነጥሎ  እንዲቆይ (ኳረንቲን መደረግ) እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ውሻው  በቀጣይ በሚያሳያቸው ምልክቶች መሠረት የእብድ ውሻ በሽታ እንዳለው እና እንደሌለው ማወቅ ይቻላል፡፡

 

“የእብድ ውሻ በሽታን ምልክት ማሳየት የጀመረ ሰው ከበሽታው ሊድን አይችልም” ያሉት ዶ/ር ግዛቸው፤ በሽታው እስካሁን ፍቱን መድሃኃኒት እንደሌለው ነው የተናገሩት፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ ሕክምናው አጥጋቢ ስላልሆነ ሕብረተሰቡ በእብድ ውሻ በሽታ ከመያዙ በፊት ከፍተኛ የመከላከል ሥራ መሥራት አለበት፡፡ ተጓዳኝ ነገሮች እንዳይኖሩት ግን  አንቲባዮቲክ (ፀረ ብግነት መድኃኒቶች)ሊሰጡት ይችላሉ፡፡

 

ሌላው የእብድ ውሻ በሽታን ለመከላከል የሚያስችል ድህረ ተጋላጭነት ክትባት እንደሚሰጥ ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡  በፊት ለ14 ቀን ይሰጥ የነበረው ክትባት አሁን ወደ አምስት ቀን ዝቅ ማለቱን አንስተዋል፡፡ በአንድ ወር ውስጥ ለአምስት ቀን ክትባቱ እንደሚሰጥ ነው ያብራሩት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንስሳቱ በሽታው እንዳለባቸው ከተረጋገጠ ቫይረሱን ነጥሎ የሚያጠቃ መድሃኒት በደም ስር ይሰጣል፡፡ የሕመም ምልክቶቹን የሚያስታግሱ መድኃኒቶችም ይሰጣሉ፡፡

 

ከዚህ በተጨማሪ ግለሰቡ ምልክቶቹ ከታዩበት ግን የሚሠጠው መድኃኒት አጥጋቢ አይደለም፡፡ ይሁንና በተወሰነ ደረጃ ሕክምናዎችን ማድረግ እንደሚቻል ነው የጠቆሙት፡፡  በመሆኑም  የሚንቀዥቀዥ ከሆነ እንዲረጋጋ የሚያደርግ፣ የሚበሳጭ ከሆነ እንዲተኛ  የሚያስችል  መድሃኒት ይሰጠዋል፡፡ ጽኑ  ሕሙማን  ውስጥ  አስገብቶ  ክትትል እንደሚደረግለትና ሌሎች መድኃኒቶችም እንደሚሰጡ ነው የተናገሩት፤ ይሁንና የመዳን እድሉ ግን አነስተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

 

የእብድ ውሻ በሽታ በደም ምርመራ መኖሩ እንደሚረጋገጥ ነው የተናገሩት፡፡ እንዲሁም  ከጭንቅላት በሚወሰድ ናሙናዎች (ብዙ ጌዜ ከሞቱ ሰዎች) በኤልክትሮ ማይስክሮኮፕ ቫይረሱ በሚፈጥራቸው ሪያክሽኖች መለየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የቫይረሱ መጠን የሰውነታችን “አንቲ ቦዲ” መጠን እና የተነከስንበት ቦታ ለጭንቅላት ያለው ርቀት በደም ለሚሰራ ናሙና ውጤት አስተዋጾ እንዳላቸው  አብራርተዋል፡፡

 

እንደ ባለሙያው ገለጻ ብዙ ጊዜ ምርመራዎች የሚደረጉት ምልክቶች ከታዩ በኋላ ነው፡፡ ቫይረሱ ክፍት በሆነ ቁስል፣ አፍ ወይም ዐይን ውስጥ ከገባ ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ የሚችልበት እድል ሊኖር ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ሥነ ምግብ ምርምር እና ኢንስቲትዩትን ዋቢ በማድረግ በሰጡን መረጃም እናቱ በዕብድ ውሻ በሽታ የሞተች አንድ ሕጻን በዛው ቫይረስ ተይዞ ሞቷል፡፡

 

በእብድ ውሻ በሽታ የተያዙ ሰዎች የሚታከሙት ለብቻቸው በጨለማ ክፍል ውስጥ ነው፡፡ የሚንከባከባቸው አካልም ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ነው የነገሩን፡፡ በተለይ የአፍ መሸፈኛ እና የዕጅ ጓንት መጠቀም አለበት፡፡ እንዲሁም ስለታማ ነገሮችን በጋራ መጠቀም የለበትም፡፡  ከሰው ውደ ሰው መተላለፉ ጥልቅ የሆነ ጥናት እንዳልተደረገበት ነው የገለጹት፡፡ ይሁንና በተለይ የተቆረጠ የሰውነት ክፍል ውስጥ ከገባ የመተላለፍ እድሉ ሊኖር እንደሚችል ነው የጠቆሙት፡፡

 

ዶ/ር ግዛቸው እንዳብራሩት የመጀመሪው የእብድ ውሻ በሽታ መከላከያው ውሻዎችን ማስከተብ ነው፡፡ የውሻ ባለቤት የሆነ ሰው ውሻውን ማስከተብ አለበት፡፡ በዓመት አንዴ ወይም ሁለቴ ማስከተብ ግድ ነው፡፡ ሁለተኛ ውሻዎችን ማሰር ጥሩ ነው፡፡ የታሰረ ውሻም አያስተላልፍም ሳይሆን ከሌሎች ጋር ንኪኪ ሊኖረው ስለሚችል የታሰረውም መከተብ አለበት ነው ያሉት፡፡

 

የውሻ ባለቤቶች ምልክት ያሳዩ እንስሳትን መለየት እና ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ምልክቶች ከታዩባቸው ውሻዎች ጋር ቅርበት ያላቸው ሰዎች በሙሉ መከተብ እንዳለባቸው ነው ያሳወቁት፡፡ ክትባቱ ሙሉ በሙሉ  ይሰራል ማለት አይደለም የሚሉት ዶ/ር ግዛቸው፤ ክትባቱ እንደማንኛውም ክትባት የጎንዮሽ ጉዳት ሊኖረው እንደሚችልም  ጠቁመዋል፡፡

 

በአማራ ክልል ከሐምሌ 1/2016 ዓ.ም እሰከ ግንቦት 17 2015 ዓ.ም ስድስት ሺህ 670 ሰዎች በተጠረጠረ የእብድ ውሻ የተነከሱ ሲሆን 76 ሰዎች የእብድ ውሻ በሽታ ምልክቶቹ ታይቶባቸዋል፡፡ ምልክቱ ከታየባቸው ውስጥ 34ቱ ለሕልፈት መዳረጋቸውን የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here