እርግማኑ የተነሳለት ሀብታም ክለብ

0
128

ፓሪሴን ዥርሜን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ካሳካ በኋላ ዘ ኢንድፔንደንት በፊት ገጹ “ኳታር የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አነሳች” የሚል መልዕክት ያለው ጽሁፍ አስነብቧል። የመድረኩን ዋንጫ ለማሳካት ረብጣ ቢሊዮን ዶላሮችን ያፈሰሱት የኳታር ንጉሣውያን ቤተሰቦች በእርግጥም ተሳክቶላቸው የሚፈልጉትን ዋንጫ ማሳካት ችለዋል። የጣሊያኑን ክለብ ኢንተር ሚላንን አምስት ለባዶ በማሸነፍ ነው በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን ያሳኩት። ድሉም ለፈረንሳያውያን የፓሪሴን ዥርሜን ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን ለኳታራውያን ጭምር መሆኑን ዘ ኢንድፔንደንት ዘግቦታል።

 

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የአውሮፓ እግር ኳስ ገጽታ በአስደናቂ መንገድ ተቀይሯል። በተለይ የገልፍ ሀገራት ንጉሣውያን ቤተሰቦች የእግር ኳስ ኢንቨስትመንትን መቀላቀላቸው በመካከላቸው የፉክክሩ ሙቀት ከፍ እንዲል አድርጎታል። በተለይ የኳታር እና የሳውዲ ንጉሣውያን ቤተሰቦች በእግር ኳስ ኢንቨስትመንት መሳተፋቸው በመካከለኛው ምስራቅ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ተጽዕኗቸው እንዲጨምር አድርጓቸዋል።

በእግር ኳስ ስፖርት ውስጥ ጎልተው ስማቸው ከሚነሱት የንጉሣውያን ቤተሰብ ክለቦች መካከል የፈረንሳዩ ክለብ ፓሪሴን ዥርሜን አንዱ ነው። እ.አ.አ በ2011 የኳታር ስፖርት ኢንቨስትመንት የፓሪሱን ክለብ ፓሪሴን ዥርሜንን መግዛቱን የአትላንቲክ ካውንስል መረጃዎች አመልክተዋል። በወቅቱ ፓሪሴን ዥርሜን በአውሮፓ ክለቦች ደረጃ 48ኛ ላይ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።

 

እ.አ.አ በ2002 “የፈረንሳይ ሊግ አንድ”  ተብሎ በአዲስ ቅርጽ ከመጀመሩ በፊት ዋንጫ ያነሳ ሁለት ጊዜ ብቻ ነበር። ክለቡ እንኳን በአውሮፓ ምድር ፈረንሳይ ውስጥም ስኬታማ የሚባል ክለብ አልነበረም። በፈረንሳይ ሴንት ኢቴን እና ማርሴ ከሀብታሙ ክለብ የተሻለ ክብር እና ሞገስ እንደንበራቸው ዘ ኢንድፔንደንት ያስነብባል። ፓሪሴን ዥርሜን ከተመሰረተ 54 ዓመታት ሆኖታል። በ1991 እ.አ.አ በካናል ፕላስ ባለቤትነት ከተያዘ በኋላ በርካታ መዋለ ንዋይ ፈሰስ በማድረግ ወደ ታላቅነት እንዲሸጋገር መሰረት ጥለዋል።

 

በአውሮፓ ትልልቅ ስም ያላቸውን ኮከቦች ጆርጅ ዊሃን እና ዴቪድ ቤካምን በማስፈረም በሊግ አንድ ተፎካካሪ ክለብ መሆን ችሏል። ከሦስት ዓመታት በኋላም ሁለተኛውን የሊግ አንድ ዋንጫ አሳክቷል። በተጨማሪም እስከ 90ዎች መጨረሻ ድረስ ሦስት የፈረንሳይ ዋንጫ እና ሁለት የሊግ ዋንጫም አሳክቷል። በ90ዎች እየፈካ የነበረው የፓሪሱ ክለብ ለውጥ በፈረንጆች ሚሊኒየም ዋዜማ እየደበዘዘ እና እየከሰመ መጥቷል። የፓርክ ደ ፕሪንስ አስተዳደራዊ መዋቅር መበላሸቱም ክለቡ በፈረንሳይ ሊግ አንድ ተፎካካሪ እንዳይሆን መሰናክል ሆኖታል።

እ.አ.አ 2011 የፓሪሴን ዥርሜን ትልቁ አቢዮት እና ለውጥ የተጀመረበት ጊዜ ነው። የኳታር ንጉሣውያን ቤተሰቦች ፓሪሴን ዥርሜንን በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓም አስፈሪ ቡድን ለማድረግ የደለበ የነዳጅ ዘይት ገንዘባቸውን በክለቡ ላይ ማፍሰስ የጀመሩበት ወቅት ነው። ረብጣ ቢሊዮን ዶላሮችን በማውጣት ፓርክ ደ ፕሪንስን የኮከቦች መዳረሻ አድርገውታል። ዝላታን ኢብራሂምሞቪች፣ ኔይማር ጁኔር እና ሊዮኔል ሜሲ በፈረንሳዩ ሀብታም ክለብ ቤት ከተጫወቱት መካከል የሚጠቀሱት ናቸው።

 

በየጊዜው የአውሮፓ ኮከቦች መንሀሪያ የሆነው ፓሪሴን ዥርሜን የፈረንሳይ ኃያል ክለብ መሆን ችሏል። ባለፉት 13 ዓመታትም ያለ ተቀናቃኝ የትኛውንም ከለብ ጣልቃ ሳያስገባ በተከታታይ የሊግ አንድ ዋንጫን አሳክቷል። የኳታር ንጉሣውያን ቤተሰቦች ፓርክ ደ ፕሪንስ መድረሳቸውም ሊግ አንድን የአንድ ፈረስ ግልቢያ ብቻ እንዲሆን አድርገውታል። በአጠቃላይም እስካሁን 49 የሀገር ውስጥ ዋንጫዎችን አሳክተዋል። ክለቡ አሁን ላይ በፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን በዓለም ቁጥር አንድ ሀብታም ክለብ ጭምር መሆን ችሏል።

 

ባሳለፍነው ጥር ወር ፎርብስ መጽሔት ባወጣው መረጃ መሰረት በ2024 እ.አ.አ ሦስተኛው ትርፋማ የእግር ኳስ ክለብ መሆኑን ይነግረናል። እንደ ዴሎቲ ጋዜጣ መረጃ ደግሞ በየዓመቱ በአማካይ 806 ሚሊዬን ዩሮ በላይ ትርፍ ያገኛል። የክለቡ አጠቃላይ የሀብት መጠን አራት ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ይገመታል። የተጫዋቾች ስብስብም በዓለም ላይ ሰባተኛው ውድ ክለብ ያደርገዋል። ፓሪሴን ዥርሜን አሁን ላይ በአውሮፓ እና በዓለም ስመጥር እና ዝነኛ ክለብ ሆኗል።

 

በፈረንሳይ ብዙ ደጋፊ ያለው ክለብም ሲሆን 35 ሚሊዬን ደጋፊ እንዳለው መረጃዎች አመልክተዋል። ክለቡ በሀገር ውስጥ እጅግ ስኬታማ ሲሆን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ብቻ ነበር በዋንጫ መደርደሪያው(ሼልፍ) ላይ ያልነበረው። ይህንንም ለማሳካት ባለፉት 14 ዓመታት ከአራት ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ በላይ አውጥተዋል። በርካታ አሰልጣኞችን ሹመዋል፤ ሽረዋል፣ በአውሮፓ አሉ የተባሉ የእግር ኳስ ኮከቦችንም አስኮብልለዋል፤ ጥቂት የማይባሉ የስፖርት ዳይሬክተሮችንም ቀያይረው ሞክረውታል።

 

ሲቀርቡት የሚሸሻቸውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ለማንሳት በተለያየ ወቅት ቡድኑን በዝላታን፣ ምባፔ፣ ኔይማር እና ሜሲን በመሳሰሉ ግለሰቦች ዙሪያ ለመገንባትም ሞክረዋል። ከ2021 እስከ 2023 እ.አ.አ የሜሲ፣ ኔይማር እና ምባፔ ጥምረት የፊት መስመሩን አስፈሪ ቢያደርገውም እቅዱ ግን ከሽፏል። ከዚህ ሁሉ ቢሊዮን ዶላሮች ወጪ ያተረፉት የፓሪሱን ክለብ የእግር ኳስ ምልክት (ብራንድ) ማድረግ፣ የታላላቅ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያዎችን ቀልብ መሳብ እና በፋሽን ኢንዱስትሪው በጎ ተጽእኖ መፍጠር ብቻ ነበር።

ፓሪሴን ዥርሜን አሰልጣኞችን እና የስፖርት ዳይሬክተሮችን ቶሎ ቶሎ መቀያየሩ ክለቡ የራሱ የእግር ኳስ ማንነት እና ባህል እንዳይኖረው አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። የሀገር ውስጥ አንበሳ ብቻ ሆኖ ለዓመታት የቆየው ክለብ በመጨረሻም ተሳክቶለት ዘንድሮ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አንስቷል። በተጫዋቾች ዝውውር በየጊዜው ከፍተኛ ገንዘብ የሚያወጣው የፈረንሳዩ ሀብታም ክለብ እስካሁን የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ማሳካት ለምን ተሳነው? የብዙዎች ጥያቄ ነው።

 

ወደ ፓርክ ደ ፕሪንስ የሚደርሱ ተጫዋቾች ከክለቡ ለውጥ እና እድገት ይልቅ በራሳቸው የተደላደለ የግል ህይወት ላይ ማተኮራቸው፣ ከእግር ኳስ ሙያቸው ውጪ በፋሽን እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ መጠመዳቸው ክለቡ ሳይሻሻል እስካሁን እንዲቆይ አድርገውት ነበር። አጥቂ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው ቡድኑን መገንባታቸውም በአውሮፓ መድረክ ስኬታማ እንዳይሆን ያደረገው ሌላኛው ምክንያት ነው። የአማካይ ክፍሉ እና የኋላ ክፍሉ ከፊት መስመሩ ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑ ክለቡ ባሰበው መንገድ እንዳይጓዝ አድርጎታል። በተጨማሪም ወጥ እና ቀጣይነት ያለው የታክቲክ ፍልስፍና በፓርክ ደ ፕሪንስ አለመኖሩ፣ በየጊዜው የሚሰበስባቸው ኮከቦች አብረው ለመጫውት መቸገራቸውም ክለቡን ውጤታማ እንዳይሆን ያደረጉት ሌላኛው ምክንያት ነበር።

 

በዙፋን ላይ የሚቀመጡ አሰልጣኞችን መታገስ አለመቻሉ ክለቡ የራሱ የሆነ የእግር ኳስ ፍልስፍና እንዳያዳብር አድርጎት ቆይቷል። በእነዚህ እና ሌሎች ምክንያቶች የፈረንሳዩ ኃያል ክለብ ወደ አውሮፓ መድረክ ሲመጣ ጉልበቱ ቄጤማ ሆኖ በተደጋጋሚ  በጊዜ ከውድሩ ውጪ ሆኗል። ከለቡ በታክቲክ የበሰለ አለመሆኑ፣ ከእግር ኳስ ይልቅ ንግድ ላይ ትኩረት ማድረጉ እንዲሁም ተጫዋቾች ከሜዳ ውጪ ልቅ ባህሪ እና ስነ ምግባር መያዛቸው በታላቁ መድረክ ለመፎካከር አቅም አንሷቸው ቆይተዋል።

 

በ2020 እ.አ.አ በጀርመናዊው አሰልጣኝ ቶማስ ቱህል እየተመራ ፍጻሜ ቢደርስም በባየርሙኒክ ተሸንፎ ዋንጫውን ሳያሳካ መቅረቱ የሚታወስ ነው። ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ እስከ ግማሽ ፍጻሜ ተጉዞ በማንቸስተር ሲቲ ከውድድሩ ውጪ መሆኑ ይታወሳል።  ከ2022 እስከ 2024 እ.አ.አ በታላቁ መድረክ በብዙ ተጠብቆ የነበረው ክለብ በጊዜ በጥሎ ማልፉ ተሰናብቷል።

 

የኳታር ንጉሣውያን ቤተሰቦች እና የክለቡ ፕሬዝዳንት  ናስር አል ከሊፊ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በጥብቅ ከመሻታቸው የተነሳ ፈረንሳያዊው ኬሊያን ምባፔ ክለቡን እለቃለሁ ሲል ከብዙ ማማሊያ ጋር ለሁለት ዓመታትም ቢሆን በፓርክ ደ ፕሪንስ ማቆየታቸው አይዘነጋም። በመጨረሻ ግን ተጫዋቹ በነጻ ዝውውር ወደ ሳንቲያጎ ቤርናቢዮ አቅንቷል። የባለተሰጥኦውን መኮብለል ተከትሎ በአሰልጣኝ ሊዊስ ኤንሪኬ የሚመራው ክለብ አዲስ እቅድ በመንደፍ በየትኛውም ተጫዋች ትክሻ ላይ ያልተንጠለጠለ ቡድን አዋቀረ። ይህ ቡድን በወጣት ኮከቦች የተገነባ ሲሆን የቡድኑ አማካይ እድሜም 24 ዓመት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

ቡድኑ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የሻምፒዮንስ ሊግ፣ የሊግ አንድ፣ የኩፕ ዴ ፍራንስ ዋንጫዎችንም አሳክቷል። ይህንንም ተከትሎ የሦስትዮሽ ዋንጫ ያሳካ የመጀመሪያው የፈረንሳይ ክለብ መሆን ችሏል። አሰልጣኝ ሊዊስ ኤንሪኬም ከሌላኛው ስፔናዊ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ቀጥሎ በሁለት ክለቦች የሦስትዮሽ ዋንጫ ያሳካ አሰልጣኝ ሆኗል። ኤንሪኬ ከዚህ በፊት በባርሰሎና ከ2014/15 እ.አ.አ የሦስትዮሽ ዋንጫ ማንሳቱ አይዘነጋም።

 

ባለፉት ሁለት ዓመታት አሰልጣኝ ሊዊስ ኤንሪኬ ቡድኑን ለመገንባት 695 ሚሊዬን ዩሮ ገንዘብ አውጥቷል። ይህም ባለፉት ስድስት ዓመታት አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ቡድኑን ለመገንባት ካወጣው ገንዘብ ጋር ሲነፃጸር በመቶ ሚሊዬን ዩሮ ብቻ እንደሚያንስ የጎል ዶት ኮም መረጃ አስነብቧል። በዘንድሮው የሻምፒዮንስ ሊጉ መድረክ ኦስማን ደምበሌ፣ አሽራፍ ሀኪሚ፣ ብራድሌይ ባርኮላ፣ ዴዜር ዱዌ፣ ኑኖ መንዴዝ፣ ፋቢያን ሩዝ እና ኪቪቻ ክቫራስኬሊያ አስደናቂ ብቃት የነበራቸው ተጫዋቾች ናቸው።

 

ኦስማን ደምበሌ የውድድሩ ኮከብ ተብሎ መመረጡ አይዘነጋም። አሽራፍ ሀኪሚ በሻምፒዮንስ ሊጉ ታሪክ አራት ግቦችን በማስቆጠር እና አምስት ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል ባለክብረወሰን ተከላካይ መሆን ችሏል። የ20 ዓመቱ አጥቂ ዴዜር ዱዌም የፍጻሜውን ጨምሮ በተለያዩ ሦስት የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ወሳኝ ግቦችን ያስቆጠረ የመጀመሪያው ወጣት አጥቂ ሆኗል። አሰልጣኝ ሊዊስ ኤንሪኬ  ፓርክ ደ ፕሪስ ከደረሰ በኋላ ወጣቶች እንደ ቡድን እንዲጫወቱ እድል ሰጥቷቸዋል። በሻምፒዮንስ ሊግም በየጨዋታው በአማካይ ከ44 በመቶ በላይ መሻሻል እያሳየ  ነው እስከ መጨረሻው ተጉዞ  ለዋንጫ የበቃው።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here