የልጅነት ቀለም

0
119

ልጅነት የብዙ ትዝታዎች የክምችት ቋት ነው። ሲያልፍ ባይታዎቅም ትዝታው ግን አይለቅም። በብዙ ሃሳቦች እና ጉጉቶች ተሞልቶ ነገን የመናፈቅ፣ በተስፋ ገመድ የመጎተት ጊዜ ነው። ልጅነት ከነባራዊው ዓለም እውነታ ጋር የመተዋወቂያ ጊዜ በመሆኑ ይነስም ይብዛ ደስታው ላቅ ያለ ነው።

ልጅነት ከትምህርት ቤት ውሎ ጋር ሲዳበል ደግሞ ትዝታው የትዬለሌ ነው። ከተወለዱበት ቀዬ ወጣ ብሎ ከሌላ መንደር ልጆች ጋር የመተዋወቅ ዕድል ይፈጥራል። ልጅነት ስሜቱ ዓለምን በአንድ ዕዝ ስር የማስተዳደር ያህል ያይላል፤ አዛዥ ናዛዥ የሆኑ ያህል ሁለት ክንድ የማትሞላ ቁመት በኩራት ትወጠራለች።

 

ብዙ የልጅነት ገጠመኞች አስቂኝነታቸው የሚታወቀው ተጎርምሶ ክፉና ደጉን መለየት ሲጀመር ነው። በወቅቱማ ድርጊቶቹ ልክ እንደሆኑ ስለሚታሰብ ለመሳቅ የሚደፍር የለም። እከሌ እንደዚህ … ሆነ፤ እንደዚህ … አለ እየተባለ እንደ ተረት እየተተረተ የሳቅ፣ የጨዋታ ምንጭ ይሆናል። የልጅነት ገጠመኝ ለማስተባበልም ዕድል አይሰጥም፤ ተፈጥሯዊ ንድፈ ሃሳብ እንደሚያራምድ ደራሲ ሁሉም ነገር ሳይከለስ፣ ሳይበረዝ እንደወረደ የሚቀርብበት ነውና።

የልጆችን ጠብ ወላጆች ጣልቃ ገብተው ያጋግሉትና ከምንም ያሻግሩታል። ይኳረፋሉ፣ ይተማማሉ፣ ጠና ሲልም በክፉ እየተያዩ ይተላለፋሉ፥ ሰላምታ አልባ። ልጆች ግን በወላጆቻቸው ተግባር ያፍራሉ፣ ይስቃሉ እልፍ ሲልም ‘ሙድ’ ይይዛሉ። “ስንጣላ ተጣሉ፣ ስንታረቅስ ለምን አይታረቁም? ‘ፋሽናቸው’ ጠብ ነው እንዴ? ይላሉ በሆዳቸው። ከተነፈሱት፣ ከተናገሩትማ ሌላ ታሪክ ይጠብቃቸዋል። ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ በሚለው የሐገራችን ብሒል መካሪነት በዝምታ ቀን ያሳልፋሉ።

 

“አልሰሜን ግባ በለው” እንዲሉ ወላጆች “ልጀን እንዴት እንደተፈነከተ አላያችሁም? ከእከሌ ጋርማ በፍፁም አልታረቅም!” ይላሉ። ልጆች አሁንም ይስቃሉ እንዲህ እያሉ “እንዴ… ቁስሉ’ኮ ድኗል፤ ከዛ ፍንከታ በኋላ ስንቴ ደምቼስ፣ ስንቴ ተፈንክቼስ! አሁን በቅርቡ አቡሻ የእከሌ ልጅ ወንዝ ወርደን ከዓይኔ አሸዋ የበተነብኝን ቢሰሙማ ጭራሽ ያብዳሉ!” ይላሉ ልጆች ሆዬ።

 

ቁስሉ ሽሮ፣ ጠባሳው ጠፍቶ’ኮ ወላጆች የተነጋገሩት የቃላት ሰምበር ብቻ ነው የቀረው። ልጆች ሲጣሉ የተጣሉ ወላጆች ልጆች ሲታረቁ መታረቅ እንደ ሰማይ ይርቅባቸዋል። ለመታረቅ የንስሃ አባት ተግሳጽና የሁዳዴ ፆምን መግባት ይጠብቃሉ። ሼሁ አንተም ተው አንተም ተው እስኪሉና ረመዳን እስከሚቃረብ ይጠበቃል። ወይ ወላጆች! ዕድሜ ሲገፋ ትልቅ ሰው ሲኾን ቀልዱ ጥቂት ጠቡ ግዙፍ ነው የሚሆነው። እርቅ ጣጣው ብዙ ይሆናል።

የልጆች ጠብ የጨዋ ጠብ ነው። ብዙ ጊዜ ማስቲካ፣ ከረሜላ፣ ፓስቲኒ ለዕርቅ የሚጠየቁ ካሳዎች ናቸው። የውሸት ዕርቅ የሚባል ነገር አይታወቅም። ጠቦች ሁሉ ጊዜያዊ ዕርቆች ሁሉ የዕውነትና ዘላቂ ናቸው። ብዙዎቹ እርቆች ያለ አስታራቂ በልቦና መሻት ብቻ የሚከዎኑ ናቸው። ታዲያ ልጅነት ቢናፈቅ ምኑ ይገርማል? ይሄ ሁሉ የዋሃትና መታደል ታጭቆበት!

 

ልጆች ለቀለም ትምህርት ብቻ አይደለም የትምህርት ቤት ደጅ የሚረግጡት፤ የህይዎትን ምዕራፍ አሃዱ ብሎ ለመጀመርም እንጅ። በሰፈር፣ በአካባቢ ብቻ ተወስኖ የነበረ ልጅ ትምህርት ቤት ሲገባ ወደ አንድ አዲስ ዓለም እንደተቀላቀለ ይቆጠራል። መምህራን፣ ተማሪዎችና ከጠቃላይ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ የህይዎቱ አንድ አካል ይሆናሉ። እንዲሁ ሲታሰብ የሚጨንቅ ቢመስልም ዕለት ዕለት አዲስ ነገር እንደ አሸን የሚፈላበት የህይዎት ዑደት በመሆኑ ከጭንቀቱ ይልቅ ጉጉቱ ይበረታል። ተማሪዎች እርስ በርስ ለመግባባትና አመል ላመል ለመዋሃድ በሚያደርጉት ጥረት አብሮ የመኖር ክህሎትን ያዳብራሉ። ምሳ ቋጥሮ በመሄድ አብሮ መብላትን ይለማመዳሉ፤ እንብላ በመባባል ከቤተሰብ ባለፈ ሌላ ቤተሰባዊነትና መተሳሰብ ለመፍጠር በመሞከር “መወለድ ቋንቋ ነው” ከሚለው የሃገራችን አባባል ጋር ፊት ለፊት ይተዋወቃሉ። መተዋወቅም ብቻ ያይደለ ለአመታት የሚዘልቅ፣ በክፉና በደግ የማይጠወለግ አንድ ሃበሻዊ ኪዳን ይኖራቸዋል።

 

በዚሁ ሁሉ መሃል የህይወት፣ በተለይ ደግሞ የዘመናዊው ዓለም መገለጫ የሆነው ውድድር ይሉት ነገር “እንተዋወቅ፥ አለሁ” ይላል። በጤነኛ መንገድ እስከተመራ ድረስ መኖሩ እምብዛም አይገድም። ከክፍል አንደኛ ለመውጣት የሚደረግ እሽቅድድም፣ ቀድሞ ሰልፍ ቦታ ለመገኘት የሚደረግ እሽቅድድም፣ ባንዲራ ወደሰንደቅ ለማውጣት የሚደረግ እሽቅድድም፣ የመምህር ማጥፊያ (ዳስተር) እና ሌሎች ቁሳቁስ ለመቀበል የሚደረግ እሽቅድድም፣ ሌላውን እንተወውና መገረፊያ ለበቅ ለመቁረጥ ወይም ደግሞ ከጎረቤት ክፍል ተውሶ ለማምጣት የሚደረገው የእኔ እኔ እሽቅድድምስ? እንደዛም እንደዚህም እያለ የውድድሩን ዓለም በደምብ እንተዋወቀዋለን።

 

ልጅነት በአዳዲስ ትውውቆች የተሞላ በመሆኑ ሌላ ሰሙ ‘ሰርክ አዲስ’ ሊባል ይችላል። ወደሰፈር የሚወስደውን ዋና መንገድ ተወት አድርገን ቅያስ ወይም አቋራጭ መንገድ ማጥናት ይጀመራል።

“…ገባኝ አሁን ገና

ከ… አቋራጭ ጎዳና…”

እንዲል ዜመኛው። የመንደሩ መውጫና መግቢያ በሚገባ ይታሰሳል፣ መንደርተኛው በደምብ ይጠናና ይታወቃል፤ ከዛ በኋላማ ‘እኔ ነኝ የሰፈሩ ‘ካቦ’ ይመጣል። ቅያስ ቅያሱን ተጉዞ ተልኮ ቶሎ ከተፍ ይባልለታል፤ “ወንድ ልጅ በሄደበት መንገድ አይመለስም” የሚለው ሃገርኛ አባባል በወጉ ይተገበራል፤ ለምን ቢሉ የመንገድ ችግር የለማ! አቋራጭ ጎዳናዎች ነፍ ናቸዋ!

 

የሆነው ሆኖ እነዚህ አቋራጭ የሰፈር ቅያሶች በቀን እንጅ በማታ ብዙ አይመከሩም። አንድ ቢሉ ሲመሻሽ የዱርዬ መናሃኸሪያ ናቸው፤ ሁለት ቢሉ ‘አባ እንጉጉ’ ሊኖር ይችላል። ማን ያውቃል? ይህ ሁሉ ሚሆነው ታዲያ “አባ እንጉጉ መጣ” ሲሉት “የታል?” የሚል ጠያቂ ትውልድ ላይ አይደለም። ፓፓዬ ከነፍሬው በልቶ ከሆዴ ይበቅላል ብሎ የሚጨነቀው ገራገር ትውልድ የተገኘ እሁን ነው። ይሄ ገራገር ትውልድ እውቁ የቦሊውድ አክተር ሻሩክ ካኸን የሚያረጅ የሚሞት የማይመስለው ከልቡ አድናቂ እና መራቂ ነው። ውሳኔ የሚለውን ፊልም አይቶ ያለቀሰ፣ ስርዬትን አይቶ በፍርሃት የራደ፣ የወንዶች ጉዳይን አይቶ በሳቅ የተንፈራፈረ፣ ፕሪዝን ብሬክን አይቶ ሰውነቱን በንቅሳት ለማዥጎርጎር ፈልጎ ገሚሱ የቤተሰቡን ቁጣ ፈርቶ፣ ገሚሱ ደግሞ ፈጣሪ አይወደውም ሃራም ነው ብሎ አስቦ፣ የተቀረው ደግሞ የሚነቅሰው አዋቂና የሚነቀሰው የማረሚያ ቤት ካርታ ቅጡ ጠፍቶት ተቸግሮ የተወው ነው። በጣም ጥቂቱ ግን በስክሪፕቶ ቀፎና ‘ቅንጭብ’ በሚባል ወተት መሰል ነገር በሚተፋ ተክል ያቅሙን የሞነጫጨረ አድናቂ እና ተደናቂ ትውልድ ነበር።

(ደረጀ ደርበው)

በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here