ሥራ ፈጣሪዉ

0
76

ኤለን ሪቭ መስክ እ.አ.አ ሰኔ 28 ቀን 1971 በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ተወለደ። የእንግሊዝ እና የፔንስልቫኒያ ደች ዝርያ ያለው መስክ ያደገው በደቡብ አፍሪካ ነው።  መስክ አባቱ ኤሮል መስክ በደቡብ አፍሪካ ኤሌክትሮ መካኒካል መሐንዲስ፣ አብራሪ፣ መርከበኛ፣ አማካሪ እና ባለሀብት ናቸው። የፀረ-አፓርታይድ ፕሮግረሲቭ ፓርቲ ተወካይ በመሆን የፕሪቶሪያ ከተማ የምክር ቤት አባል ነበሩ፡፡ መስክን ጨምሮ ሁሉም ልጆቻቸው የአባታቸው የፖለቲካ ተጽኖ እንዳደረባቸው ይናገሩ ነበር፡፡

 

መስክ በየሰፈሩ ጀላቲ እንደሚሸጡ  ማንኛውም አፍሪካዊ ነጭ ልጆች እሱም ከወንድሙ ጋር ቤት ለቤት እያንኳኳ ቼኮሌት ይሸጥ ነበር፡፡ መስክ በ10 ዓመቱ ከቪአይሲ-20 የተጠቃሚ መመሪያ እራሱን እንዴት በፕሮግራም መምራት   እንዳለበት በመረዳት የኮምፒዩተር አጠቃቀም ችሎታውን አዳበረ፡፡

ከኮምፒዩተር ጋር የሙጥኝ በማለቱ  በ12 ዓመቱ ትንሽ የኮምፒዩተር ጌም ፈጠረ፡፡ ኋላ ላይ በ500 ዶላር ሸጣት::መስክ እናት እና አባቱ በልጅነቱ በፍች በመለያየታቸው በ17 ዓመቱ ከአባቱ ተለይቶ እናቱ ወደ ምትኖርበት ካናዳ አቀና፡፡ ወደ ካናዳ ከመሄዱ በፊት በፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የጀመረውን ትምህርቱን  በካናዳ ኩዊንስ ዩኒቨርስቲ  ቀጠለ፡፡

 

ከካናዳ በዝውውር ወደ ፔንስልቫኒያ ዩኒቨርስቲ ተሻገረ፡፡ በዛም በኢኮኖሚክስ እና ፊዚክስ የመጀመሪያ ዲግሪውን ያዘ።

ዕድሜው 24 ሲደርስ ደግሞ ወደ ካሊፎርኒያ አቀና፡፡ በስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ በፒኤችዲ በአፕላይድ ፊዚክስ ለመማር ተመዘገበ፡፡ ከዚያ ግን ምን እንደነካው ሳይታወቅ ወዲያኑ ጥሎ ወጣ፡፡ ከዩኒቨርስቲ እንደወጣ ሁለት ነገር ሞከረ፡፡ የድረ-ገጽ መተግበሪያ እና የበይነ መረብ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎችን፡፡

 

ከዚያ በፊት ግን ከወንድሙ ጋር ጽሑፍን ከጋዜጣ ወደ ዲጂታል የሚቀይር  “ዚፕ2” የሚባል ’ሶፍትዌር’ ሠርተው ነበር፡፡ ከብዙ መከራ በኋላ ድርጅቱን ሸጡት፡፡

ከዚያ  በኋላ ነው  ሌሎች ድርጅቶችን የገው፡፡ ከሁለቱ አንዱ ፍሬ አፈራ፡፡ ይሄም የበይነ መረብ የባንክ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ በኋላ ፔይፓል (PayPal) በሚል የሚታወቀው ክፍያን የሚያቀላጥፈው ኩባንያ ነው፡፡

መስክ እ.አ.አ በጥቅምት 2002 ኢቤይ ፔይፓልን በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገዛ፡፡ በዚያው ዓመት በ100 ሚሊዮን ዶላር የጠፈር በረራ አገልግሎት ኩባንያን ስፔስኤክስን መሰረተ።

 

የንግዱ ዓለም የገባው መስክ እ.አ.አ. በ2004 ደግሞ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች ቴስላ ሞተርስ (Tesla Motors Inc.)   ውስጥ ቀደምት ባለሀብት  ሆኖ  ፤ በ2016 በቴስላ የተገዛ እና የቴስላ ኢነርጂ የሆነውን  ሶላር ሲቲ (SolarCity) የተባለ የሶላር-ኢነርጂ ኩባንያ ለመፍጠር ረድቷል። እ.አ.አ በ2008 የዋና ሥራ አስፈፃሚነት ቦታን በመያዝ የድርጅቱ ሊቀመንበር እና የምርት አርክቴክት ሆነ ።

እ.አ.አ በ2013 ደግሞ የሃይፕሎፕ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የክትባት ማጓጓዣ ዘዴን አቅርቧል። እ.አ.አ በ2015 ኦፕን ኤአይ (OpenAl) የተሰኘ ለትርፍ ያልተቋቋመ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ምርምር ኩባንያን በጋራ አቋቋመ።

 

መስክ  የአንጎል ኮምፒዩተር መገናኛዎችን (ኒውሮሊንክን) የሚያዳብር ኒውሮቴክኖሎጂ  እና ሌሎች ኩባንያዎችን በ2016 እ.አ.አ አቋቋመ።  በ2022 ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር ገዝቷል። በመቀጠል ኩባንያውን ወደ አዲስ የፈጠረው  ኤክስ (X)  ኮርፖሬሽን አዋህዶ አገልግሎቱን ከአንድ ዓመት በኋላ እንደ ኤክስ (X) ለወጠ። በማርች 2023 ኤ አይ የተሰኘ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኩባንያ አቋቋመ።

ኢ ኮሜርስ በድረ ገጹ    እንዳሰፈረው መስክ እምቅ የቴክኒክ እውቀት ያካበተ  ሰው እንደሆነ ነው፡፡  በፊዚክስ እና ኢኮኖሚክስ ዲግሪ፣ ስለ ቁጥሮች፣ ቴክኖሎጂዎች እና ፋይናንስ ዕውቀትን በማጣመር የሥራ ባልደረባዎቹ የንግድ አዝማሚያዎችን አስቀድሞ ለመገመት እና በሌሎች ሰዎች አስተሳሰብ ውስጥ ጉድለቶችን የመለየት ጥልቅ ስሜት እንዳለውም  አስፍሯል።

 

በራስ መተማመንን ወደ ፈጣን ውሳኔ አሰጣጥ የሚተረጉመው  መስክ የጠንካራ እና የረጅም ጊዜ እቅዶች ደጋፊ እንዳልሆነ እና በፍጥነት እርምጃ ወስዶ  ከውጤቱ በመማር ኮርሱን እንደ አስፈላጊነቱ የሚያስተካክል የፈጠራ ሰው እንደሆነ በምጣኔ ሃበት ዙሪያ የሚፅፈው   ድረ ገፅ አስነብቧል፡፡

መስክ በከፍተኛ የሥራ ወዳድነት እና ድፍረት በተሞላበት ሁኔታ  ግቦችን በማሳካት ዝነኛ ነው። ከፍተኛ አደጋዎችን በመጋፈጥ ድፍረትን፣ ከፍተኛ በራስ መወሰን እና በተጨባጭ ውጤቶች ላይ በማተኮር ላይ ልዩ የማሰብ ችሎታው ምንም ይሁን ምን ለስኬቱ  አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር መስክ ብሩህነትን ከብዙ ቁርጠኝነት ጋር ያጣምራል ፤ እሱ ትልቅ ያስባል፤ ራእዩን እውን ለማድረግም ጠንክሮ ይሠራል። ይህ የተቀናጀ አቅጣጫ ወደ ታላላቅ ግቦች ለመድረስ በአጭር ጊዜ  በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ በርካታ ኩባንያዎችን እንዴት እንዳገኘ እና እንደሚያሳድግ በከፊል ማሳያ ነው።

ምናልባትም የመስክ በጣም አወዛጋቢ ገጽታ የሚባለው ከሰዎች ጋር ያለው ግንኙነት ነው። መስክ እንደ ሥራ ፈጣሪ እጅግ በጣም ስኬታማ ባለራዕይ ቢሆንም በሰዎች አስተዳደር ረገድ ግን አማካይ መሪ ነው። ይህም ቢሆን ከሌሎች የቴክኖሎጂ ግዙፍ ሰዎች አይለየውም፡፡

 

ሌላው የመስክ በጣም ጉልህ የማህበረሰብ ተጽዕኖ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ያለው ቁርጠኝነት ነው። በቴስላ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እና ታዳሽ የኀይል ምርቶች አማካኝነት  ከቅሪተ አካል ነዳጆች የራቀ ሽግግርን እያሳየ ነው። የእሱ እይታ ብዙ አውቶሞቢሎች ወደ ኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች እየዞሩ ነው። ይህ ለውጥ የህብረተሰቡን አመለካከት፣ ደንቦች እና መሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረ ነው፣ ሁሉም ወደ ፊት ሀሳቡን እየተገበረ መምጣት አለበት የሚል ነው። እሱ ቴስላን ወደ ዘላቂ የኀይል አቅርቦት በማሸጋገር  ግንባር ቀደም ለማድረግ ይፈልጋል።

 

ወደ ፊት  መስክ ማርስን ቅኝ  የመግዛት እና የሰው ልጆችን ባለብዙ ፕላኔቶች ለማድረግ እቅድ አለው። ምንም እንኳን ሳይንሳዊ ልብወለድ ቢመስልም ስፔስኤክስ አስቀድሞ ወደዚህ ግብ ግስጋሴዎችን እያደረገ ነው። ከስታርሺፕ ልማት ጋር  በአሁኑ ጊዜ በግንባታ ላይ ያለ ሙሉ በሙሉ እንደገና ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል የጠፈር መንኮራኩር  በመሥራት መስክ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የጭነት ተልእኮዎችን ወደ ማርስ እንደሚጀምር ተስፋ ያደርጋል፡፡ ይህም  እ.አ.አ በ2050 ማርስ  ራሷን የምትችል ከተማ ማድረግ ነው።

 

ህልሞችን እውን ለማድረግ ካለው ፍላጎት ጋር ዓለማችንን እና ከዚያም በላይ እየቀረጸ ነው። መስክ በአስደናቂ ስራዎቹ እና ሀሳቦቹ በዘመናችን ታሪክ ውስጥ ለራሱ ልዩ ቦታን ፈልፍሎ በማያሻማ ሁኔታ ፈጥሯል። ከአቧራማ የፕሪቶሪያ ጎዳናዎች አንስቶ እስከ አንፀባራቂ የዓለም የቴክኖሎጂ ስራ ፈጣሪነት ጫፍ ደርሷል። እንደ ”ዚፕ2 እና ፔይፓል” ባሉ ኩባንያዎች አማካኝነት መስክ ወደ ቴክኖሎጅ ኢንዱስትሪው ገብቷል፡፡ አዳዲሶችን ፈር ቀዳጅ እያደረገ፣ የጠፈር ጉዞ እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተደራሽ ያደርጋል።

የእሱ ህይወት እና ሥራ ብዙ ወጣቶች እና ሥራ ፈጣሪዎች  የሚቻለውን እንደገና እንዲያስቡ፣ ከምቾት ዞን እንዲወጡ እና እንደ መስክ ደፋር እና ገደብ የለሽ የወደፊት ጊዜን እንዲያስቡ ይገፋፋናል።

ምንጭ- ኒውራ ኪንግ ዶት ኮም (neuraking.com) ፣ ኢ ኮሜርስ የተሰኘ  ድረ ገፅ (ecommerceupdate.org)፣ ጁሊ ፍሎኪን ዶት ኮም (julienflorkin.com) እንዲሁም ዊኪፒዲያ ናቸው፡፡

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here