የቀለጠ ዓለት ከመሬት ውስጥ ወደ ላይኛው ገፀ ምድር ገፍቶ ለመውጣት መቃረቡን በዙሪያው የሚገኙ እፅዋትን በመገምገም ከሚያሳዩት ለውጥ በመነሳት እሳተ ገሞራ ከመፈንዳቱ በፊት የጥንቃቄ ርምጃዎችን ለመውሰድ እንደሚያስችል ሳይንስ አለርት ድረገጽ ከሰሞኑ ለንባብ አብቅቶታል::
እሳተገሞራ ንቁ ሆኖ ከውስጥ ወደ ገፀምድር እየገፋ ለመፈንዳት ሲቃረብ የቀለጠው ዓለት (ማግማ) ከፍተኛ መጠን ያለው ካርቦንዳይ ኦክሳይድን ይለቃል:: ይህን ልቀት እጽዋት፤ ወደ ውስጥ ሲስቡት እድገትን ያስቀጥላል ልምላሜን ያላብሳቸዋል::
በእፅዋቱ ላይ የሚታዩት ለውጦች በተለይም (NDVI)(normalized difference vegetation indexs) ከተለመደው ከእፅዋት ከሚገኘው መረጃ የበለጠ ልዩነትን ያመላክታሉ:: ሁነቱን ከጠፈር ላይ ባሉ ሳተላይቶች ማየት ቢቻልም መሬት ላይ በቦታው ተገኝቶ በመለኪያ መሳሪያ ለመከታተል አስቸጋሪ ነው:: በመሆኑም በእፅዋት ላይ ከሚታየው ለውጥ በመነሳት ቅድመ ትንበያን ማከናወን እንደሚችል ነው ያረጋገጡት – ተመራማሪዎቹ::
የሆውስተን ዩኒቨርሲቲው የእሳተ ገሞራ ተመራማሪ ኒኮል ጊን እንዲሁም የማክጊል ዩኒቨርሲቲው የእሳተ ገሞራ ተመራማሪ ሮበርት ቦግ ጥናት እና ምርምር ባደረጉባቸው ሁለት የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ቦታዎች የእፅዋት ቅጠሎችን ለውጥ በተጨባጭ ማስተዋላቸውን ነው ያረጋገጡት:: ይህም በሳተላይት ከተወሰደ ምስል ጋር አባሪ ሆኖ መደገፉ ለእውነትነቱ ማስረጃ መሆኑን ነው ያሰመሩበት::
ተመራማሪዎቹ እስከ አሁን የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎችን ለመተንበይ የሚያስችሉ በርካታ ምልክቶች ወይም ቀድሞ ማወቂያ ሁነቶች እንደ ነበሩ አመላክተዋል:: ለአብነት የመሬት ውስጥ እንቅስቃሴን በመለካት፣ የመሬት ከፍታ መጨመርን በመመልከት፣ ከነዚህ በተጨማሪ በቅርቡ የተገኘው በቀጣናው የሚገኙ የእፅዋት ቅጠሎች የሚያሳዩት ለውጥ ሦስተኛ ማረጋገጫ ሊሆን እንደሚችል ነው አፅንኦት ሰጥተው ያሰመሩበት::
የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ መቃረብን በዙሪያው በሚገኝ የእፅዋት ቅጠሎች ማገናዘብ እፅዋት በሌሉበት ቀጣና ተግባራዊ ሊሆን ባይችልም በእፅዋት ለተሸፈኑ ቦታዎች ውጤታማ ተገቢነት ያለው ቅድመ ፍንዳታ ማስጠንቀቂያ ሊሆን እንደሚችል ነው ያደማደሙት – ተመራማሪዎቹ፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም