በቻይና ዠጂያንግ ግዛት “ዩኒትሪ” የተሰኘው ኩባንያ “ጂ1” በሚል ስያሜ ያመረታቸውን ሮቦቶች ዓቅማቸውን በማሳየት ማስተዋወቅን ዓልሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀው ውድድር በብዙሃን መገናኛዎች መሠራጨቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::
ሮቦት አምራቹ ኩባንያ “ዩኒትሪ” በዠጂያን ግዛት ያዘጋጀው ልዩ የካራቴ እና የቦክስ /የኪክ ቦክሲንግ/ ውድድር “ጂ1” የተሰኙ የሮቦት ምርቶቹን ብቃት ለማስተዋወቅ ያለመ ነው:: በውድድሩ የተሳተፉት “ጂ1” ሮቦቶች አንድ ሜትር ከሰላሳ ሴንቲ ሜትር ቁመት እና 35 ኪሎ ግራም ክብደት ያላቸው መሆኑም ተገልጿል::
በቻይና መንግሥት ባለቤትነት በሚተዳደረው ቻይና ሴንትራል ቴሌቪዥንም (ሲሲቲቪ) በቀጥታ ስርጭት ለእይታ በቅቷል- ውድድሩ:: በመክፈቻው ኘሮግራም አራት “ጂ1” ሮቦቶች ጥንድ ጥንድ ሆነው በመወዳደሪያ ቀለበት ውስጥ ገብተው ተጋጥመዋል::
የሮቦቶቹ ፍልሚያ በሰው ዳኛ ክትትል፣ ህግ እና ደንብን ማስከበር እንዲሁም ለረዢም ደቂቃ ሲያያዙ ወይም ታቃቅፈው ሲቆዩ የማለያየት ተግባርም ተከውኗል::
ተወዳዳሪዎቹ ሮቦቶች በውድድሩ መጀመሪያ የጭንቅላት መከላከያ፣ ደረጃውን የጠበቀ የቦክስ ጓንት ማድረጋቸው ተረጋግጧል- በዳኛው:: በግጥሚያ ተመቶ የወደቀ ሮቦት በወደቀበት ስምንት ሰከንድ ሲቆጠር ካልተነሳ በዝረራ መሸነፉን ዳኛው በምልክት ያሳዩበት ትርኢትም ነበር::
የሮቦቾቹ የፍልሚያ እንቅስቃሴ በርቀት መቆጣጠሪያ መሣሪያ እና የድምፅ ትእዛዝን በሚያቀናጁ ከውድድር ቀለበቱ ውጪ ባሉ ባለሙያዎች ጭምር ነው የተመራው::
የመጀመሪያዎቹ ሁለት ውድድሮች ተካሂደው አሸናፊዎቹ ከተለዩ በኋላ የየጥንዱ አሸናፊዎች የመጨረሻ ለአሸናፊዎች አሸናፊነት ተፋልመዋል::
በመጨረሻም “ዩኒትሪ” የተሰኘው ኩባንያ በውድድሩ ያቀረበው ሮቦት በፍልሚያው በነጥብ የበላይነት አግኝቶ ለአሸናፊነት መብቃቱን ድረ ገጹ አስነብቧል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም