ነፋስ በመስረቅ የተከሰሰችው ሀገር

0
62

በሰሜን ባሕር ቀጣና ቤልጄዬም የነፋስ ኃይል ማመንጫ መቅዘፊያዎቿን በነፋስ አቅጣጫ ወይም ትይዩ ከፊት በመትከሏ ሦስት በመቶ የሚሆን ኃይል ኔዘርላንድ እንደተሰረቀባት በመግለጽ መክሰሷን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል::

የኔዘርላንድ የአየር ሁኔታ ትንበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ የቤልጄዬም የነፋስ ኃይል ማመንጫ “ተርባይኖች” ከሀገሩ ማለትም ከኔዘርላንድ  አየር መስረቃቸውን ተናግረዋል:: ዋና ሥራ አስፈፃሚው ሬምኮ ቨርዚጅልበርግ ከቤልጂዬም ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት ቤልጂዬም የነፋስ ሀይል ማመንጫ “ተርባይኖችን” ከኔዘርላንድ በፊት በመትከሏ ሦስት በመቶ የሚሆን  የነፋስ ኃይል ከኔዘርላንድ ይሰርቃሉ::

 

የነፋስ ኃይል መሰብሰቢያ “ተርባይን” ነፋስ ባለበት ትይዩ ሲተከል የሚኘው ኃይል እና በነፋስ ትይዩ ከተተከለ “ተርባይን” ጀርባ ሲተከል የሚኘው የኃይል መጠን የተለያየ መሆኑን ነው፡፡

የጠቆሙት- ዋና ስራ አስፈፃሚው::  ለዚህ በማሳመኛ ነጥብነት ያነሱት ከፊት ለፊት የሚተከሉ  “ተርባይኖች” ከፍ ያለ ኃይል  ወይም ግፊት ሲያገኙ ከኃላ የሚተከሉት የዓየር ፍጥነትም ሆነ ግፊታቸው የቀነሰ  መሆኑን ነው ያሰመሩበት::

የነፋስ ግፊት “ከተርባይን” ወይም መቅዘፊያ ማማ ከፊት እና ከኋላ ሲለካ የኃይል መጠኑ የተለያየ መሆኑን ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በአገራት መካከል የተሻለ የተቀናጀ አሰራር እንዲሰፍንም ጠይቀዋል::

 

ከነፋስ ኃይል መሰብሰቢያ መቅዘፊያ ማማዎች “ተርባይኖች” ጀርባ የሚለካው የነፋስ ፍጥነትም ሆነ የሚገኘው ግፊት አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል:: ለዚህ ከፊት ያሉ ተርባይኖች የነፋሱን ግፊት እንደሚቀንሱት ማረጋገጣቸውን ነው  ያሰመሩበት::

የኔዘርላንድ የአየር ሁኔታ ትንበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ በሀገሪቱ በስተምእራብ በሚገኙ የነፋስ ኃይል መቅዘፊያ “ተርባይኖች” ባሉበት ቀጣና ሌሎች አገራትም ሊተክሉ ስለሚችሉ ችግሩ አሳሳቢ እንደሆነ ነው የጠቆሙት:: በመሆኑም ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋት ለነገ ወይም ይደር የማይባል ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት:: በመጨረሻም  የሰሜን ባህር ቀጣና ቀስበቀስ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ማማዎች በብዛት ሊተከሉበት እንደሚችል ጠቁመው የአየር ስርቆት ወደ ግጭት አድጐም በአገራት መካከል ጦርነት እንዳያስነሳ መስራት እንደሚገባ በማሳሰብ ነው ያደማደሙት::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here