ዓለምን ያስደነገጠዉ ድንገተኛዉ ጥቃት

0
86

ዩክሬን የሸረሪት ድር (Spiderweb Operation) የሚል ስያሜ በተሰጠው ዘመቻ ሰሞኑን በሩሲያ ላይ አስደንጋጭ ጥቃት ፈጽማለች። በማግስቱ ደግሞ የክሪሚያ ድልድይን በውኃ ውስጥ በሚፈነዱ ፈንጂዎች መታሁ ብላለች:: ይሁንና ከሰዓታት በኋላ ድልድዩ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ሩሲያ አስታውቃለች።

 

ቢቢሲ እንደዘገበው ድልድዩ እ.አ.አ በ2014 ሩሲያ የክሪሚያን ባሕረ ገብ መሬት ወደ ግዛቷ ከቀላቀለች በኋላ በሩሲያ የተሠራ ሲሆን ሩሲያን ከዩክሬን የሚያገናኝ ነው፡፡ ድልድዩ በዩክሬናዊያን ዘንድ የተጠላ ነው። ዩክሬን በድልድዩ ላይ ሁለት ጊዜ (እ.አ.አ በ2022 እና በ2023) ጥቃት አድርሳለች። ከሰሞኑ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮልዲሚር ዜሌንስኪ  “የሸረሪት ድር” በሚል  ዘመቻ ከሩሲያ   ቦምብ ጣይ  አውሮፕላኖች ውስጥ አንድ ሦስተኛውን  መምታታቸውን  አስታውቀዋል፡፡ ጥቃቱ  መላ  ዓለምን   ያስደነገጠ፤  ያስገረመም  ነበር። ዩክሬን “አደረኩት” ብላ ስኬቷን ስታውጅ ዜናው ለዩክሬናዊያን እና ለደጋፊዎቿ (በዋናነት ለምዕራባዊያን) ፈንጠዝያን ሲፈጥር ሩሲያን አንገት አስደፍቷል፡፡

 

ዩክሬን  በርካታ ድሮኖችን አስርጋ በማስገባት ሩሲያ አለኝ ከምትላቸው ቦንብ ጣይ አውሮፕላኖች መካከል 41 ያህሉን እንዳወደመች ነው የተናገረችው። ጥቃቱ የተፈጸመው እህልና ፍራፍሬ በተሞሉ ኮንቴነሮች ውስጥ በድብቅ በገቡ ሰው አልባ አውሮፕላኖች  ነው:: በውስጣቸው በርካታ ድሮኖችን በድብቅ የያዙ ረዣዥም ተሽከርካሪዎች ወደ ሩሲያ እንዴት ገቡ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡

 

በተለይም ዩክሬን ወደ ሩሲያ ከአንድ ሺ ኪሎ ሜትር በላይ ዘልቃ እንዴት ጥቃት መፈጸም ቻለች የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ሩሲያ አሉኝ የምትላቸው የተራቀቁ  አየር መከላከያዎች ምንም ማድረግ አለመቻላቸው የሩሲያን አቅም ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ሆኗል።

ዩክሬን በጥቃቱ ከቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች በተጨማሪ 34 በመቶው የሚሆነውን የሩሲያን የአየር ሚሳኤል ተሸካሚ መርከቦች መወድማቸውን አሳውቃለች፡፡ በዚህም ሰባት ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሶባታል ሲል ነው የአውስትራሊያው ኤን ቢ ሲ የዘገበው፡፡

የዩክሬን ጦር ኃይሎች ጄኔራል እንዳስታወቀው በጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባቸው የጦር አውሮፕላኖች መካከል አንድ ብርቅዬ “A-50” የስለላ አውሮፕላን፣ “TU-95 ኤም ኤስ” እና “TU-22 ኤም 3” ቦምቦች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

 

ይሁንና እነዚህ መረጃዎች በገለልተኛ ወገን ያልተረጋገጡ ሲሆን ሩሲያም በጥቃቱ ላይ ይፋዊ ምርመራ መጀመሯን ገልጻለች። ሮይተርስ አረጋገጥኩት ብሎ በምስል አስደግፎ ባሰራጨው ዘገባ ደግሞ የዘመቻው የድሮን ምስል በርካታ አውሮፕላኖች ቢያንስ በሁለት ቦታዎች መመታታቸውን ያሳያል።

ቴሌግራፍ በበኩሉ ከዩክሬን አገኘሁት ባላቸው ምስሎች ብርቅ የሆነውን ኤ-50 የስለላ አውሮፕላንን በተሳካ ሁኔታ ሲደበደቡ መመልከቱን መስክሯል። ይህ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የቁጥጥር አውሮፕላን   ሞስኮ የዩክሬን አየር መከላከያዎችን ለማግኘት እና ከቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች እና ተዋጊ ጄቶች ጋር የሚደረጉ ጥቃቶችን ለማስተባበር ከፍተኛ እገዛ ሲያደርግ የቆየ ነው፡፡

 

በተያያዘም  “ኪዬቭ የአሜሪካ የስለላ መረጃ ከሌላት በስተቀር የሰሞኑን  ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም  በሩሲያ አየር መንገዶች ላይ ጥቃት መፈጸም አትችልም ነበር” ሲሉ የቀድሞ የፈረንሳይ ከፍተኛ የጦር ኃይል መኮንን ጊላም አንሴል መናገራቸውን የሩሲያው የዜና ወኪል ታስ ዘግቧል፡፡ የጦር መኮንኑ እንደሚሉት ይህ የሚቻለው እና የሚታሰበው በሳተላይት ግንኙነት ድጋፍ ብቻ ነው። “ዩክሬናዊያን እንደዚህ አይነት ሥርዓቶች የላቸውም እና በርቀት መሥራት ከቻሉ ምንም ጥርጥር የለውም በአሜሪካ ድጋፍ ነበር” ብለዋል፡፡

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የባይደን አስተዳደር ዩክሬን በሩሲያ አየር ማረፊያዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት እንዳቀደች እንደማያውቁ የዋይት ሀውስ ዘጋቢ ጄኒፈር ጃኮብስ ምንጮቹን ጠቅሰው ተናግራዋል። ዩክሬን በሩሲያ ላይ ያደረሰችውን ጥቃት ለመከወን ከ18 ወራት በላይ እንደተዘጋጀችበት ማሳወቋን ልብ ይሏል።

እንደ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር አንድሬይ ብሎሶቭ ገለጻ ግንቦት 24 ዓ.ም (እ.አ.አ ሰኔ 01/2025) ኪዬቭ  በአምስት የሩሲያ ክልሎች በሚገኙ የጦር ሰፈር የአየር ማረፊያዎች ላይ ሰው አልባ  ድሮኖችን በመጠቀም በርካታ የሽብር ጥቃቶችን ፈጽማለች፡፡ የመከላከያ ሚኒስትሩ  የደረሰባቸውን ድንገተኛ ውርጅብኝ “የሽብር ጥቃት” ብለውታል፡፡ ይሁንና የመከላከያ ሚኒስትሩ ከአምስቱ ክልሎች መካከል በሦስቱ ክልሎች የተቃጣን የድሮን ጥቃት በተሳካ ሁኔታ መከላከላቸውን ተናግረዋል፡፡

 

በጥቃቶች የተጎዱ የአውሮፕላን ቁጥሮችን በዝርዝር ባይናገሩም በርካታ አውሮፕላኖች መቃጠላቸውንና ነገር ግን እሳቱን በፍጥነት ማጥፋት መቻሉን ነው የገለጹት። በሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን በማንሳት በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አረጋግጠዋል።

ሩሲያ ይህ አስደንጋጭ ጥቃት ከተፈጸመባት ማግስት በተርክዬ ዋና ከተማ ኢስታንቡል ለሁለተኛ ዙር የሰላም ድርድር ከዩክሬን ጋር ተቀምጣ ነበር፡፡ በድርድሩም ተጨማሪ እስረኞችን ለመለዋወጥ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ቢሆንም ግን የዩክሬን ተደራዳሪዎች ሩሲያ በድጋሚ ያለ ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁሙን ውድቅ እንዳደረገች ጠቁመዋል።

 

የተርክዬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲቢሃ እንዳስታወቁት  ሁለቱ ወገኖች ተጨማሪ የጦር እስረኞችን ለመለዋወጥ ተስማምተዋል፡፡ ከሁለቱም ወገን የስድስት ሺህ ወታደሮችን አስከሬንም ይለዋወጣሉ።

በንግግራቸው ወቅት ሩሲያ እና ዩክሬን ስለወደፊቱ የሰላም ስምምነት ራዕያቸውን የሚገልጹ ሰነዶችንም ተለዋውጠዋል፡፡ ኪየቭ ከድርድሩ በፊት ለሩሲያው ወገን ረቂቁን ማቅረቧን ልብ ይሏል።

 

በኢስታንቡል ድርድር ላይ የዩክሬን መደምደሚያን አስመልክቶ ሲቢሃ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ሞስኮ ለሰነዱ ምላሽ አለመስጠቷ ታውቋል፡፡ ጉዳዩ በድርድር ወቅት እንደተነሳ ገልጸው ነገር ግን የሩሲያው ወገን “በስብሰባው ወቅትም ሆነ በኋላ ምንም ዓይነት ሀሳብ አልሰጠም” ብለዋል።

ይሁንና ከድርድሩ በኋላ ሩሲያ በሁለቱ ሀገራት ግጭት አፈታት ዙሪያ ለቀረበው ሰነድ ምላሽ ሰጥታለች፡፡ አናዶሉ እንደዘገበው ሩሲያ ዩክሬን ወታደሮቿን ከዶኔትስክ፣ ሉሃንስክ፣ ዛፖሪዝሂያ እና ኬርሰን ክልሎች እንድታስወጣ ጠይቃለች፡፡ ለዩክሬን የሚሰጠውን ማንኛውንም የጦር መሳሪያ እና የመረጃ አቅርቦት እንዲታገድ እና ማንኛውም የውጭ ወታደራዊ ኃይል በሀገሪቱ ግዛት እንዳይኖርም አሳስባለች።

ሩሲያ አክላም የተኩስ አቁም ትግበራው ልዩ በሆነው የሩሲያ – ዩክሬን የክትትል ማዕከል ቁጥጥር ይደረግበታል ነው ያለችው፡፡ በተጨማሪም “ሞስኮ እና ኪዬቭ ለፖለቲካ እስረኞች ምህረት ያደርጋሉ፡፡ እናም ዩክሬን “የማርሻል” ሕጉን በመሰረዝ የእርቅ ሰላሙ በተደረገ በ100 ቀናት ውስጥ ምርጫ ማካሄድ ይኖርባታል” ስትል ነው ያሳወቀችው።

 

በሰነዱ ክሬሚያ፣ ዶኔትስክ፣ ሉሃንስክ፣ ዛፖሪዝሂያ እና ኬርሰን ክልሎች እንደ የሩሲያ አካል ሆነው ከዓለም አቀፉ ወገን ዕውቅና ማግኘት አለባቸው የሚለውን አጽንኦት ሰጥታበታለች። በተጨማሪም ዩክሬን ከአውሮፓ እና ከኔቶ ጋር ገለልተኛ እና አጋር ያልሆነ አቋም እንዲኖራት ያዝዛል፡፡ ዩክሬን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዲኖራትም አይፈቅድም፡፡ እንዲሁም ዩክሬን የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ሙሉ መብቶች፣ ነፃነቶች እና ጥቅሞች ማረጋገጥ አለባት የሚልም ተካቶበታል።

 

በተጨማሪም በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለው የሰላም ስምምነት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሕጋዊ አስገዳጅ ውሳኔ መጽደቅ አለበት የሚል ሰነድ ነው ሩሲያ ያቀረበችው።

 

ሩሲያ እንደምትለው እ.አ.አ ከ2014 ጀምሮ በዩክሬን በዶኔትስክ እና በሉሃንስክ ሕዝቦች ሪፐብሊክ ላይ ተፈፀመ ባለችው ጥቃት 316 ሕጻናት ሲገደሉ አንድ ሺህ 249 ቆስለዋል፡፡ ከሟቾች ውስጥ 69ኙ ሕጻናት ናቸው፡፡ 237 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በኢስታንቡል በተደረጉት ንግግሮች ላይ የተወሰኑ ስምምነቶች ከተደረሱ በኋላ በዩክሬን ያለውን ግጭት ለመፍታት የሚደረገው ሥራ መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡ ፔስኮቭ የሩሲያ ዋና ግብ የዩክሬን ግጭት ዋና መንስኤዎችን ማስወገድ እና ዘላቂ ሰላማዊ እልባት ማግኘት መሆኑን ገልጸዋል። “በኢስታንቡል የተካሄደው ድርድር ጠቃሚ ቢሆንም የአጭር ጊዜ መፍትሔዎችን እና ግኝቶችን መጠበቅ ስህተት ነው” ማለታቸውን በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ በቴሌግራም ገጹ አጋርቷል፡፡

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን የኔቶ አባል መሆንን የሚመለከት ድንጋጌ በሄግ ከሰኔ 24 – 25 (እ.አ.አ) በሚካሄደው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የመጨረሻ መግለጫ ላይ እንደማይካተት አንድ የዲፕሎማቲክ ምንጭን ጠቅሶ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። ሕብረቱ ዩክሬንን ለመደገፍ “ምንም አዲስ የፋይናንስ ቃል ኪዳን” ለማድረግ እንዳላሰበም ነው የዘገበው።።

 

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here