የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል  የነቃ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ

0
74

የዓለም አካባቢ ቀንን ምክንያት በማድረግ “የፕላስቲክ ብክለትን እንግታ!” በሚል መሪ መልዕክት ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

በዓሉን ከግንቦት 19/2017 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል በፓናል ውይይት፣ በጽዳት ዘመቻዎች፣ በስፖርታዊ ውድድሮች፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጠበቅ በሚያስችሉ ተግባራት እና ባለድርሻ አካላትን በሚያሳትፉ ሁነቶች በዞኖች፣ በከተማ አስተዳደሮች፣ በወረዳዎች እና በቀበሌዎች በተለያዩ መርሐ ግብር ሲከናወን ቆይቷል። ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም ደግሞ ክልል አቀፍ የማጠቃለያ መርሐ ግብር በባሕር ዳር ከተማ ተከናውኗል።

 

የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ምቹ  የመኖሪያ አካባቢ ለመፍጠር እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቋል። የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ በልስቲ ፈጠነ በውይይት መድረኩ እንዳብራሩት መሥሪያ ቤቱ ብክለትን ለመከላከል በትኩረት እየሠራ ይገኛል። ይህን ጅምር አጠናክሮ በመቀጠልም  ፅዱ እና የበለፀገች ሀገር ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል፡፡

 

የዘንድሮው የዓለም አካባቢ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ52ኛ፣ በኢትዮጵያ ለ32ኛ፣ እንደ አማራ ክልል ደግሞ ለ28ኛ ጊዜ መከበሩን ነው የተናገሩት። የዓለም የአካባቢ ቀን በ1973 ዓ.ም በየዓመቱ እንዲከበር ሲወሰን በአካባቢ ላይ የሚደርሱ የአካባቢ ብዝኃ ህይወት መጎሳቆል እና የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

 

ምክትል ኃላፊው አክለውም ከፕላስቲክ በተጨማሪም የደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ የአካቢን ንፅህና መጠበቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ዋነኛ የአካባቢ በካይ የሆነውን የፕላስቲክ ምርት ከመጠቀም መቆጠብ፤ ከተጠቀምን ደግሞ ጤናማ የአወጋገድ ዘዴ መከተል እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመሆኑም  ይህንን ጉዳት የሚያመጣ የፕላስቲክ ከረጢት ከመጠቀም ይልቅ ከካርቶን፣ ከጨርቅ እና መሠል የሚሠሩ የዕቃ መያዣ ከረጢቶችን በመጠቀም ከፍተኛ የሆነውን የፕላስቲክ ቆሻሻ ብክለት መቀነስ እንደሚቻል ተመላክቷል።

 

አቶ በልስቲ እንደገለፁት ፕላስቲክ በሰዎች፣ በእንስሳት እና በብዝኃ ሕይወት ላይ ጉዳት እያደረሰ፣ በሥነ ምኅዳር ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ እያስከተለ ነው። የአካባቢ ብክለት የሰው ልጆችን አደጋ ላይ የሚጥል ነው፤ የጤና ጠንቅ መሆኑንም ተናግረዋል። ፕላስቲክን በየቦታው ከመጣል መቆጠብ፣ ይልቁንም በአግባቡ መያዝ እና ወደ ፋብሪካዎች በማስገባት መልሶ መጠቀም እንደሚገባም አመላክተዋል። ስለዚህ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለራሱ፣ ለቤተሰቡ እና ለትውልዱ ጤና በማሰብ አካባቢውን ማጽዳት አለበት ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል። በውይይት መድረኩ በተሳታፊዎች ለተነሱ ሐሳብ እና አስተያይቶች ምላሽ እና ማብራሪያ በመስጠት ተጠናቋል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here