ከሦስት ዓመት በፊት በወሊድ ምክንያት ባጋጠማት ደም መፍሰስ ሕይዎቷ ሊያልፍ ሲል በተሰጣት የደም ልገሳ ሁለተኛ የመኖር እድል እንዳገኘች የገለጸችልን የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ፋሲካ ወርቁ ደም ከመለገሷ በፊት ስለ ደም ልገሳ የተሳሳተ ግንዛቤ እንደነበራት ነው የገለጸችልን። ፍሲካ እንዳለችው በፊት ደም መለገስ ለከፍተኛ ህመም ሊዳርግ ይችላል የሚል አስተሳሰብ ነበራት። አሁን ግን ደም ከለገሱ ሰዎች ባገኘችው ተሞክሮ አመለካከቷ ተስተካክሏል። ምንም እንኳ ከጤናዋ ጋር ተያይዞ ደም ለግሳ እሷም እንደሌሎቹ የሰዎችን ሕይወት መታደግ ባትችልም ደም መለገስ ለሚችሉ ሰዎች ግን ”ሕይዎቴ የተረፈው በተለገሰኝ ደም ነው” በማለት ደም መለገስ የሚያስገኘውን ጥቅም ታካፍላለች፡፡
በጣና ሀይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ዳንኤል ዘላለም በበኩሉ በትምህርት ቤቱ ደም የመለገስ ዘመቻ ላይ ነበር ያገኘነው፡፡ ተማሪ ዳንኤል እንዳለው እድሜው ከ18 በላይ ሲሆን ሰባት ጊዜ ደም ለግሷል፡፡ “ደም መለገስ የፈልግኩት ሰዎችን ለማዳን በማሰቤ ነው፤ ይህን በማድረጌም የመንፈስ ደስታ አግኝቻለሁ” ብሏል፡፡
ደም መተኪያ የሌለው ከሰው ብቻ የሚገኝ ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ ያለ ደም መኖር አይቻልም፡፡ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን እና ኦክስጅንን ወደ ሴሎች ለማድረስ ደም በሰዎነትዎ ውስጥ ይሰራጫል፡፡ አንድ ሰው ቀዶ ጥገና ሲያደርግ ወይም ድንገተኛ አደጋ ደርሶበት ብዙ ደም ከፈሰሰው በሚሰጠው ትክ ደም የጠፋውን ደም መተካት ይችላል፡፡
ከስጦታዎች ሁሉ የላቀ ስጦታ እንደሆነ ብዙዎች የሚስማሙበት የደም ልገሳ በተለምዶ የሚያስፈራ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን የአንድን ሰው ሕይዎት ለማዳን የሚረዳ ቀላል አስደሳች ነገር ነው፡፡ ደም ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የመለገስ ጥቅሙ ማብቂያ የለውም፡፡
አንዴ የለገሱት ደም እስከ ሦስት ሰዎች የማዳን አቅም እንዳለው ሲያውቁ ደግሞ የሚፈጥረው ደስታ ወደር የለውም፡፡ ታዲያ ይህን የምታውቁት ግን ደም ስትለግሱ ብቻ ነው፡፡ ደም የሚያስፈልጋቸው ሰዎች በደም ምክንያት ሕይዎታቸው ሲቀጥል ከማየት ባለፈ ምን የሚያስደስት ነገር አለ!፡፡
እኛም አጠቃላይ የደም ልገሳና ስርጭቱ ምን ይመስላል? የሚለውን ለማወቅ ወደ ፈለገ ሕይዎት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል አምርተን ነበር፡፡ የሆስፒታሉ የላብራቶሪ ኳሊቲ ኦፊሰር (ባለሙያ) አቶ አምላኩ አታላይ እንደገለጹት ሆስፒታሉ በዋናነት ደም የሚያገኘው ከባሕር ዳር የደም ባንክ ነው፡፡ የደም ባንኩ ከተለያዩ በጎ ፈቃደኛ ከሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ያሰባሰበውን ደም አስፈላጊ የሚባሉትን ቅድመ ምርመራዎች በማድረግ ወደ ጤና ተቋማት ያሰራጫል፡፡
በጤና ተቋማቱ የሚገኙ የላብራቶሪ ክፍልም የመጣውን ደም ከየትኛው ደም ከሚያስፈልገው ሕመምተኛ ጋር ይስማማል የሚለውን ነገር በመለየት ለሕሙማኑ ይሰጣሉ፡፡ በዘንድሮ ዓመት የዘጠኝ ወር አፈጻጸምም ሆስፒታሉ አራት ሺህ አራት መቶ አንድ “ዩኒት” ደም ከደም ባንክ የተቀበለ ሲሆን አራት ሺህ ሦስት መቶ ሃያ አምስቱን ለህሙማን ለግሷል፡፡
እንዲሁም ከደም ባንክ ተመዝግበው የሚመጡ የደም አይነቶች በየአይነታቸው ተመድበው ከ2 እስከ 4 ዲግሪ ሴንትግሬድ በሆነ ሙቀት በፍሪጅ ውስጥ ይቀመጣሉ፡፡ በሰው ሰውነት ውስጥ ያለ ደም የአንድ መቶ ሃያ ቀን እድሜ ሲኖረው ከሰው ከወጣ በኋላ ግን ለ42 ቀናት ብቻ ይቆያል፡፡ ባለሙያው አክለው እንደገለጹት በሆስፒታሉ ራሱን ችሎ የደም መለገሻ ቦታ በመዘጋጀቱ ማንኛውም ፈቃደኛ ሰው በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ደም መስጠት ይችላል፡፡
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጽኑ ሕክምና እና የደም ባንክ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ አንዳርጌ አጥናፍ እንደገለጹት እንደ ሀገር ደም ልገሳ የተጀመረው እ.አ.አ በ1962 ወይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1969 ዓ.ም ነው፡፡ መስራቹም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ነበር፡፡
በወቅቱ የተለያዩ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች በማጋጠማቸው ምክንያት የደም ባንክ ሊቋቋም ችሏል፡፡ ከዚያም በዋና ዋና የሀገሪቱ ከተማዎች የደም ባንኩ ተቋቁሟል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል 10 የደም ባንኮች የሚገኙ ሲሆን የባሕርዳር፣ የደሴ እና የጎንደር ደም ባንኮች ጥሩ አፈጻጸም በማሳየት በተደጋጋሚ በሀገር ደረጃ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በተያዘው የበጀት ዓመት በዘጠኝ ወር ውስጥም 50 ሺህ 862 “ዩኒት” ደም ተስብስቦ 42ሺህ 342 ዩኒት ደም በክልሉ ለሚገኙ ለ166 የመንግሥት እና ለግል የጤና ተቋማት ተከፋፍሏል፡፡
አስተባባሪው እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ የሕብረተሰቡ ደም የመለገስ ግንዛቤ ጨምሯል፡፡
የሚታየው ነገር ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን የዜጎችን ሕይዎት ለማትረፍ ደም የመለገስ ሂደት ላይ መረባረብ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ደም አይሸጥም አይለወጥም! ይህን ሲያደርግ የሚገኝ ሰው በሕግ እንደሚቀጣም አስገንዝበዋል፡፡
በመኪናም ሆነ በተለያዩ ምክንያት ድንገተኛ አደጋ ደርሶባቸው ደም ለፈሰሳቸው ሰዎች፣ የተፈጥሮ አደጋ ላጋጠማቸው ሰዎች ፣በወሊድ ምክንያት ደም ለፈሰሳቸው እናቶች ፣የደም ማነስ ላለባቸው ሕጻናትም ሆነ አዋቂዎች፣ ለካንሠር ታማሚዎች፣ የሰውነት መድማት ችግር ያለባቸው፣ የቀዶ ጥገና ለሚያደርጉ ሰዎች ደም ይለገሳል፡፡ አቶ አንዳርጌ እንዳሉት በሆስፒታል ተኝተው ከሚታከሙ ከሰባት እስከ አስር ከሚሆኑ ሰዎች መካከል አንዱ ደም ያስፈልገዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡
ደም ለመለገስ ሊያሟላቸው የሚገቡ አንዳንድ መሰረታዊ መስፈርቶች እንዳሉ ያብራሩልን አስተባባሪው ደም ለመለገስ መጀመሪያ ፈቃደኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ “እኔ ደም ለግሼ የሌሎችን ሕይዎት ማዳን አለብኝ” የሚል በጎ ፈቀደኝነት የመጀመሪያው ደም ለመስጠት ወሳኝ መስፈርቱ እንደሆነ ነው የጠቆሙት፡፡ ከዚያም ዕድሜው ከ18 እስከ 65 እና ክብደቱ ከ45 በላይ የሆነ ሰው፣በደም የሚተላለፍ በሽታ (ኤች አይቪ፣ የጉበት ቫይረስ እና የአባላዘር በሽታዎች) የሌለበት ሰው ደም መለገስ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል የዓለም የጤና ድርጅት ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ደም በሚለገስበት ጊዜ ለጋሹ በጥሩ ጤንነት ላይ መኾን አለበት፡፡
ጉንፋን፣ የጉሮሮ መቁሰል፣ የሆድ ቁርጠት፣ ወይም ማንኛውም (ኢንፌክሽን) መመረዝ ካለበት በሽታው እስኪሻለው ድረስ ደም መስጠት አይችልም፡፡ ጸረ-ባክቴሪያ (አንቲባዮቲክ) መድሃኒት የሚወስዱ ሰዎች ቢያንስ መድሃኒቱን ከጨረሱ ከሰባት ቀናት በኋላ ነው ደም መስጠት የሚችሉት፡፡ በቅርብ ጊዜ ንቅሳት የተነቀሰ ወይም ቀዶ ጥገና ካደረገ ስድስት ወር ያላለፈው ሰው ደም መለገስ አይችልም፡፡ ነፍሰጡሮች እና ጡት አጥቢዎች ደም እንዲለግሱ አይመከርም፡፡ እንዲሁም አስም፣ ደም የሚፈሳቸው፣ ካንሰር ያለባቸው፣ የደም ማነስ ያለባቸው ሰዎች ደም መስጠት አይችሉም፡፡ በየዓመቱም አንድ ሰው ለአራት ጊዜ ያህል ደም መለገስ ይችላል፡፡ ታዲያ ደም ሲለግስ ሦስት ወር ( በየሦስት ወሩ) ሊያልፈው ግድ ይላል፡፡
ደም በመለገስ የሌሎችን ሰዎች ሕይዎት ከማዳን በተጨማሪ ለጋሹ የሚያገኘው የጤና በረከቶች እንዳሉ ነው አስተባባሪው የጠቆሙት፡፡ ምንም እንኳን ሙሉ ምርመራ ባይደረግም ደም ከመወሰዱ በፊት በሚደረግ ጥቂት ምርመራዎች የጤናዎን ሁኔታ እንዲያውቁ ያስችለዎታል፡፡ እነሱም፡-ለሰብዓዊ አገልግሎት ተሳታፊ ያደርጋል፡፡
የደም ዓይነትን ያለክፍያ በነጻ የማወቅ ዕድል ይፈጥርልዎታል፣ እ.አ.አ. በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ደም በመለገስ ብቻ የደም ፍሰትን ለማሻሻል እና የደም ቧንቧን መዘጋትን ለመቀነስ ይረዳል፡፡ በተጨማሪም ሆውስተን ሔልዝ ኬር ድረ ገጽላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው በካንሰር የመያዝ እድልን ይቀንሳል፡፡
ታዲያ የዓለም የደም ለጋሾች ቀን በየዓመቱ ሰኔ 14 ቀን በመላው ዓለም እንደተከብረ ልብ ይሏል። እለቱ የዓለም ጤና ድርጅት በተለያዩ የደም ልገሳ ዘርፎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ የፈጠረው ዓለም አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና ዘመቻ አካል ነው። ለሌሎች ሰዎች በሕይወት እንዲቆዩ ሁለተኛ እድል ለሚሰጡ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ በጎ ፍቃደኞች፣ ምንም ሳይከፈላቸው ደም ለሚለግሱት ምስጋና የሚቀርብበት ዕለት ነው። የእነሱ ልግስና ሕይወትን ያስቀጥላል፣ ያድናልም፡፡ ደም ስጡ ተስፋን ስጡ በአንድነት ሕይወትን እናድናለን። የዘንድሮው የዓለም የደም ልገሳ በዓል መሪ ቃል ነው፡፡ እ.አ.አ. በ 2005 በተካሄደው የዓለም ጤና ድርጅት የደም ለጋሾች ቀን በየዓመቱ ሰኔ 14 ቀን ለካርል ላንድስቲነር ልደት ክብር ሲል በዓለም ደረጃ እንዲከበር ወስኗል።
ካርል ላንድስቲነር እ.አ.አ በ1901 ሰዎች የተለያዩ አይነት ቀይ የደም ሴሎች ማለትም የተለያዩ የደም ክፍሎች እንዳላቸው አረጋግጧል። ግኝቱ ተመሳሳይ የደም ቡድን ባላቸው ሰዎች መካከል ደኅንነቱ የተጠበቀ ደም እንዲሰጥ አድርጓል። የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው እያንዳንዱ የደም ልገሳ የተስፋ ስጦታ ነው። ደም ለተለገሱ ሰዎች (ታካሚዎች) በሕይወት እና በሞት መካከል ያለውን ልዩነት ሊያመለክት ይችላል፡፡ ደም ልገሳ የጋራ ጥረት እና ጠንካራ የትብብር ተግባርም ነው።
ደም መለገስ በድንገተኛ አደጋዎች እና በወሊድ ጊዜ ለሚፈጠር ደም መፍሰስ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕይወትን ለማዳን ይረዳል። እናም ሳትሰለቹ እና ሳትሰስቱ ደም ለግሱ! ሕይዎት አድኑ ! እንላለን፡፡ ፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም