ፈተና  ያበረታት

0
126

የተወለደችው አስመራ ቢሆንም ነፍስ ካወቀች በኋላ ያደገችው አዲስ አበባ ነው፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ ማንኛውንም የቤት ሥራ ሠርታ እንዳደገች የምትገልፀው የዛሬ ባለታሪካችን ራሄል አሰፋ ትባላለች፡፡ ገና በ12 ዓመት ዕድሜዋ ቆሎ በመሸጥ ራሷን ለመደገፍ ስትጥር እንደቆየች እና  በ 14 ዓመቷ ደግሞ አሳዳጊዋ በሞት ስለተለየቻት ወጥ ቤት በመቀጠር ሠርቶ ራስን መደገፍ እንደጀመረች አጫውታናለች፡፡

የ15 ዓመት ታዳጊ ሆና ትዳር የመሠረተችው ራሄል በዓመቱ ደግሞ የልጅ እናት ለመሆን ችላለች ፤ በወቅቱ እንጀራ አባቷ ከባሕር ዳር አዲስ አበባ በመምጣት ወላጅ እናት እንዳላት እና አሳዳጊዋ ክርስትና እናት እንደነበረች ተነግሯት ወላጅ እናቷ ጋር ለማገናኘት በ1994 ዓ.ም ወደ ባሕር ዳር ከተማ እንደመጣች ትናገራለች፡፡

ባሕር ዳር  መጥታ ትንሽ እንደቆየች ልጅ ይዞ ቤት ውስጥ ካለሥራ መቀመጥ ስለሰለቻት በ17 አመቷ ቀበሌ 10 አካባቢ ቤት በመከራየት በወቅቱ “ሜድሮክ” የሚባለው ህንፃ እየተሠራ ስለነበር በ200 ብር   በወጥ ቤት ሠራተኝነት ተቀጠረች፡፡ በወቅቱ ለልጇ ጠባቂ ሠራተኛ ቀጥራ  ታሳድግ ነበር፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ደሞዟ  ደግሞ በቂ እንዳልነበረ የምታስታውሰው ራሄል  ቅዳሜ ከሰዓት ጀምሮ የወጥ ቤቱ ሥራ ስላልነበረ በሥራ ቦታዋ ያሉ የጋራጅ ቤቶችን ልብስ አጥቦ በማስረከብ እና በተጨማሪ ደግሞ የተከራየችበት ቤት እንጀራ ስለሚያስረክቡ ማታ ማታ እንጀራ በመጋገር ሌላ  ገቢ በማግኘት ልጇን በጥሩ ሁኔታ ታሳድግ  እንደነበር ትናገራለች፡፡

ባለቤቷ ከአዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳር መጥቶ አብሮ መኖር ሲጀምሩ ግን ሥራ ወጥታ መሥራቷን እንዳልወደደው ነው የምትገልፀው፡፡ ባለታሪካችን በዚህ ምክንያትም እንደገና ቤት ውስጥ ያለምንም ሥራ እንድትውል ማድረጉን እና በዚህ መካከል ሁለተኛ ልጃቸውን ለመውለድ  ስትቃረብ ግን ባለቤቷ በመጥፋቱ  እና  ሥራ አጥ በመሆኗ ለከፍተኛ ችግር ዳርጓታል፡፡

ወቅቱ 1997 ዓ.ም ስለነበር ችግር ውስጥ ገብቶ ይሆናል በሚል ባለቤቷን በመፈለግ እንዲሁም የእለት ጉርስን ለመሸፈን እና ልጇን ለማሳደግ ከፍተኛ ውጣውረድ እንደነበረው አንስታ በወቅቱ የ8 ወር ነፍሰጡር ብትሆንም በኪራይ ቤት ስላለች ኑሮን ለማሸነፍ  በግለሰብ ምግብ ቤት ወጥ ቤት ተቀጥራ መሥራት ጀመረች፡፡ ልጇን ስትወልድም ጥቂት ቀን ብቻ በማስፈቀድ ቶሎ ወደ ሥራ መመለሷን አስታውሳ በዚህ አጋጣሚ ልጇን የሚጠብቅ ሰው ስላልነበረ ለእናቷ እየተወች  ነበር የምትሄደው፡፡ በዚሁ ወቅት ወላጅ እናቷ ደግሞ ችግር ውስጥ ናት በሚል በወቅቱ አለም አቀፍ ጉዲፈቻ በመንግስት በኩል ይሠጥ ስለነበር ልጇን ለመንግስት ሰጠችባት፡፡ ልጇን ለመውሰድ ወደ እናቷ ቤት በሄደችበት ወቅት ልጇን እናቷ ጋር በማጣቷ ደግሞ ሥራዋን በመተው ልጇን ለመፈለግ ወደ አዲስ አበባ እንድትመላለስ ምክንያት እንደሆነ ጉዳዩን ዛሬም እንደ አዲስ በእንባ ታስታውሳለች፡፡

ገንዘቧ ሲያልቅ ወደ  ባሕር ዳር በመመለስ ከጉልት እስከ ወጥ ቤት ያገኘችውን ሠርታ  እና እቁብ ሰብስባ አዲስ አበባ ይገኝበታል በተባለው “ሚሽነሪ ኦፍ ቻሪቲ” የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት በር ላይ ትልቁ ልጇን ይዛ በመቀመጥ ብዙ ጊዜ ማሳለፏን አስታውሳለች፡፡ በመጨረሻም ትልቁ ልጇ እንዳይጎዳ በማሰብ እዛው አካባቢ ባለ የግንባታ ድርጅት ጎን ሻይ ቤት በመክፈት ቁጭ ብላ መጠበቅ ጀመረች፤ በምትሠራበት አካባቢ የግንባታ ሠራተኛ እና እህቱ እንደሷ ልጅ በጉዲፈቻ ተወስዳበት የሚፈልግ ግለሰብ በማግኘቷ በድርጅቱ የተወሰዱ ልጆችን ዝርዝር መመልከት ብትችልም የሷ ልጅ የተላከበት ሥም ተቀይሮ በመሄዱ ማግኘት ሳትችል እንደቀረች ዛሬ ላይ በእንባ ጉንጮቿ እየራሱ ነው የምትገልፀው፡፡

ምንም እንኳን  ፍንጭ ባይኖርም አንድ ቀን አገኘዋለሁ በሚል ተሥፋ ሥራዋን እየሠራች ለአንድ ዓመት ብትጠብቅም የልጇ አለመገኘት እና ሥራውም ቀዝቀዝ በማለቱ ሁለተኛ ትዳር መሥርታ እንደገና ወደ ባሕር ዳር መመለሷን ትገልፃለች፡፡

በወቅቱ ቤት ማፅዳት፣ ልብስ ማጠብ፣ አሻሮ መቁላት፣ ሻይ ቤት፣ ምግብ ቤት…. የተገኘውን ሁሉ እየሠራች በተከታታይ ሦስት ልጆች እናት የሆነችው ወ/ሮ ራሄል  የልጇን ፍለጋ ጉዳይ በስሜታዊነት ሳይሆን በተረጋጋ መንፈስ መረጃውን ከምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም በመሄድ እና በመፈለግ  የሄደበትን ትክክለኛ ሥም አግኝታ ስፔን መሄዱን እና ከጉዲፈቻ ወላጆቹ ጋር ያለውን ፎቶ ለማግኘት ቻለች፡፡  ባለፉት አምስት ዓመታት  በፌስቡክ ያለበትን ሁኔታ በመከታተል ላይ እንደሆነች እና ሌሎች ልጆቿን ሰብስባ ስታሳድግ እሱ መነጠሉ ከፍተኛ የጥፋተኝነት ሥሜት እንደሚያንገበግባት ነው የምትገልፀው ፡፡

ወ/ሮ ራሄል ዛሬ ላለችበት ሥራ መነሻ የሆናት አጋጣሚ በሰፈር ውስጥ ያሉ ሰዎችን ሹሩባ የመሥራት ችሎታ ያላት ቢሆንም እንደ ሥራ አስባ የማታውቀው ነገር በመሆኑ በነጻ ሥትሠራ ቆየች፤  የበዓል ወቅት አካባቢ ባጋጣሚ አንዲት ሴት ቀለበት የሚባል የሹሩባ ሥራ እንድትሠራት ጠይቃት በወቅቱ በዊግ 10 ብር የሚሠራውን ሥራ ሠርታት 40 ብር ሥትከፍላት ደግሞ ያላሰበችውን የፀጉር ቤት ሥራ ለመሥራት ተነሳሳች፡፡

በወቅቱ ጓደኛዋ ፀጉር ቤት (የውበት ሳሎን) ስለነበራት አጥባ እና ጥቅልላ ለፀጉር ቤቱ እሷ ደግሞ ሹሩባ እየሠራች ለራሷ እንድትወስድ በመስማማት ሥራ ጀመረች፡፡ ምንም እንኳን በወቅቱ ሹሩባ በፀጉር ሦስት ብር በዊግ ደግሞ 10 ብር ቢሠራም በቀን የሁለት ብር እቁብ እየጣለች ኑሮዋን መደጎም ጀመረች፡፡

በወቅቱ ሥራዋን ያዩ ሰዎች ጠንካራ ሠራተኛ ናት እና ብቻዋን ልጆች የምታሳድግ እናት ብለው  ስለመሰከሩላት የባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ አቅም ለሌላቸው መሥራት ለሚችሉ ጠንካራ ሴቶች ኮንደሚኒየም መሥሪያ በጊዜአዊነት ሰጥቷት የራሷን ፀጉር ቤት አንድ ወንበር እና ጠረጴዛ በመግዛት መሥራት ጀመረች፡፡

ቀሥ በቀስ የምትጥለው እቁብ ሲወጣላት ማጠቢያ፣ መሥሪያ እንዲሁም ደግሞ  የፀጉር ማድረቂያ (ካስክ) በመግዛት በአንድ ዓመት ውሥጥ የተሟላ ፀጉር ቤት ማድረግ እና ልጆቿን  አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ ከትምህርት ሰዓት ውጭ እሷ ጋር እንዲሠሩ በማድረግ ሥራዋን አጠናከረች፡፡

ሥራው ከተጀመረ አንድ ዓመት በኋላ ግን የፀጉር ቤት እቃዋ የተሟላ በመሆኑ “ሃብታም ናት ድጋፍ አይገባትም” የሚል ቅሬታ ሰዎች ስላነሱ ቦታውን ልቀቂ በመባሏ እቃውን ሰብስባ በተከራየችው ቤት በማስቀመጥ የምትሠራበት አካባቢ አባይ ማዶ  ሆቴል ከነ ዕቃው በወር 15 ሺህ ብር በወር ተከራየች፡፡

በወቅቱ ትላለች ወ/ሮ ራሄል “ከፀጉር ቤት እቃ የእለት ጉርስ እና ልብስ በቀር በጥሬ ገንዘብ ያተረፍኩት ገንዘብ ከ700 ብር የዘለለ አልነበረም፤ ቤቱ ውስጥ ግን ብርጭቆ ሳይቀር በኪራይ ስለነበረው በብሩ በ150 ብር ነጭ አረቄ፣ ሜንት አረቄ፣ ግማሽ ኪሎ ሽሮ እና በርበሬ በመግዛት ሥራ ጀመርኩበት፡፡”በማለት ከፀጉር ሙያ ወደ ምግብ ሥራ የገባችበትን አጋጣሚ ትገልፃለች፡፡

ሥራው በተጀመረ እለት አልጋ የያዙ ሰዎች ሽሮ እና መጠጥ በመፈለግ ሲመጡ እንጀራ ከጎረቤት ከ,ሱቅ በዱቤ በመውሰድ መሸጥ እንደጀመረች እና ወይን የሚፈልጉ ሰዎች ሲመጡ ደግሞ ከጎረቤት ሱቅ በማምጣት 50 ብር እያተረፈች በማቅረብ በአንድ ቀን ውስጥ 3400 ብር ማግኘት ቻለች፡፡

መኖሪያዋም መሥሪያዋንም እዛው አድርጋ ሥራውም ሞቅ ብሎ በግ  ድረስ መሸጥ ጀምራ እንደነበረ አስታውሳ በመሃል የኮረና መከሰት እና ባለቤቱ ገበያ ሞቅ ሲል እራሴ እሠራዋለሁ ብሎ ልቀቂ ስላላት መኖር ብትችልም ያሰበችውን ያህል መለወጥ ሳትችል ቤቱን ለቀቀች፡፡

የመጀመሪያ ልጇ እሷ ጋር ፀጉር ይሠራ ስለነበር እና ሙያውንም ስላዳበረ ምግብ በመሥራት ከምትቸገር በፀጉር ሙያው መሥራት እንዳለባት ስለገፋፋት የምግብ ሥራውን በመተው በዳያስፖራ አካባቢ በመከራየት የፀጉር ቤት ሥራን ከልጆቿ ጋር  በመሥራት በአካባቢው ረጅም ጊዜ መቆየት መቻሏን ትገልፃለች፡፡

በፆም ወቅት የፀጉር ቤት ሥራው ሲቀዘቅዘ ጎን ለጎን እርጥብ፣ (ዳቦ በአትክልት)ክረምት ሲመጣ ደግሞ ማታ ማታ በቆሎ በመቀቀል እና በመሸጥ ከፍም ዝቅም ብላ እንደምትሠራ ትገልፃለች፡፡

“ለልጆቼ የማወርሳቸው ትልቁ ነገር ሥራ ነው፡፡” የምትለው ወ/ሮ ራሄል የመጀመሪያ ልጇ ከሷ ባገኘው እውቀት አዲስ አበባ በፀጉር ባለሙያነት ጥሩ ብር ተከፍሎት እየሠራ እንደሆነ እና ሦስተኛ ልጇም ጥሩ የፀጉር ሥራ ባለሙያ መሆን እንደቻለ ታነሳለች፡፡

ትምህርታቸውን በአግባቡ ተከታትለው እና አጥንተው ሲጨርሱ በሥራ ቦታዋ ተገኝተው አብረው እንዲሠሩ እንደምታደርግ የምትገልጸው ወ/ሮ ራሄል ልጆችን ብቻቸውን ላለመተው እና ከትምህርት ውጭ ሠርተው ብቻ መለወጥ እንደሚችሉ ለማሳየት በማሰብ በማንኛውም ሰዓት በአቅማቸው የቤት ውስጥም ሆነ የውጭውን  ሥራ ሠርተው እንዲያድጉ ማድረጓን ትገልፃለች፡፡

የወ/ሮ ራሄል አራተኛ ልጅ የሆነው በሱ ፍቃድ ምንይሻዋል እናታቸው ሠርታ የምታሠራ እና ምንም ነገር ስትሞክር ተስፋ የማትቆርጥ በመሆኑ ከሷ ብዙ ትምህርት እንደወሰደ ይገልፃል፡፡ሌሎች ሦስቱ ልጆች በጸጉር ቤት ሥራው ጎበዝ እንደሆኑ ገልፆ እሱ ግን በትምህርቱ ጠንካራ ተማሪ ስለሆነ ከጥናት ውጭ የቤቱን ሥራ በማገዝ እንደሚረዳት እና ወደፊት ደግሞ ትልቅ ቦታ ደርሶ እናቱን የመርዳት ህልም እንዳለው ይናገራል፡፡

በህይወቷ ያላለፈችበት ሥራ እና መከራ እንደሌለ የምታነሳው ወ/ሮ ራሄል ሂደቱ የበለጠ እንድትበረታ እንጂ ተስፋ እንዳትቆርጥ ስላደረጋት ልጆቿን ብቻዋን በጥሩ ስነምግባር እና የሙያ ባለቤት ማሳደግ መቻሏን ነው የገለፀችው፡፡

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here