አውስትራሊያዊቷ የ34 ዓመት ወጣት በ24 ሰዓታት ውስጥ 7079 “ፑልአኘ” በመስራት አዲስ ክብረወሰን ማስመዝገቧን ዩፒአይ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል:: ኦሊቪያ ቬንስን ለዓለም የክብረወሰን ባለሙያዎች ስለ ውጥኗ በማስታወስ እንደተናገረችው አንዳች ፈታኝ የሆነ ነገር ለመፈፀም ማሰቧን ለባለቤቷ እና ለአሰልጣኟ በነገረቻቸው ወቅት በ24 ሰዓታት “ፑል አኘ” መስራትን ሲጠቁሟት እንደማይሆንላት በመገመት ተሳልቃባቸዋለች፡፡
ውላ አድራ አስባበት አጠያይቃ ቀደም ብሎ የተመዘገበው ክብረ ወሰን በ24 ሰዓታት 4081 መሆኑን ተገንዝባ እንደማይሆንላትም ትወስናለች፡፡
ኦሊቪያ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በ2021 እ.አ.አ በፓላንዳዊቷ ፓውላ ጐርሎ የተያዘውን ክብረወሰን ማለትም 4081 በ24 ሰዓት የሰራችውን “ፑልአኘ” አውጥታ አውርዳ የራሷን ቀመር ሰርታ ከሦስት ወራት ልምምድ በኋላ ባደረገችው ሙከራ ከ12 ሰዓታት በኋላ ባጋጠማት የቋንጃ ጅማት መተሳሰር ለማቆም ተገዳለች:: ኦልቪያ ያጋጠማት ጉዳት ለሁለት ወራት ከልምምድ አግዷት ከቆየች በኋላ አገግማ ለሁለተኛ ጊዜ ለመሞከር ተዘጋጀች፡፡
በሁለተኛው ክብረ ወሰን ለማስመዝገብ ያደረገችው ጥረትም ችግሮች እንደነበሩበት ነው የተናገረችው፡፡ በሙከራዋ ከአስራ ዘጠኝ ሰዓታት በኋላ ከፍተኛ የድካም ስሜት እንደተሰማት እና አካሏ መዛሉንም ጠቁማለች: :
በመጨረሻም በስልጠና፣ በልምምድ ወቅት የረዷትን ባለቤቷን እና የአሰልጣኟን ልፋት አሰላስላ በተሻለ ደረጃ መፈፀም እንደሚኖርባት ወስና ከ19ኛው ሰዓት አልፋ 20፣ 21… 24 ሰዓታት መግፋት ቻለች::ኦሊቪያ ቬንስን በአማካይ በደቂቃ አምስት በዚሁ ስሌት በ24 ሰዓታት 7079 “ፑልአኘ” በመስራት አዲስ የዓለም ክብረወሰን አስመዝግባለች::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም