አበርዴር ብሔራዊ ፓርክ በኬኒያ ከዋና ከተማዋ ናይሮቢ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ፓርኩ በቀጣናው የሚገኘውን ብዝሃ – ህይወት ለመጠበቅ በ1950 እ.አ.አ 767 ኪሎ ሜትር ስከዌር ስፋት ይዞ ነው የተመሰረተው:: መገኛው – ዝቅተኛው 2000 ሜትር ከፍተኛው የመልካዓ ምድር አቀማመጥ 4000 ሜትር ተለክቷል:: አበርዴር ብሔራዊ ፓርክን ለመጐብኘት አመቱን ሙሉ የተመቸ ነው፤ ሆኖም ተመራጮቹ ደረቅ ወቅቶች ማለትም ከሰኔ እስከ ጥቅምት እንዲሁም ከታህሳስ እስከ የካቲት ያሉት ወራት ናቸው:: የዓየር ንብረቱ ከ14 ዲግሪ ሴልሽየስ እስከ 18 የተለካ ሲሆን ቀዝቃዛ ነው፡፡ የፓርኩ ቀጣና ዓመቱን ሙሉ ዝናብ የሚያገኝ ቢሆንም ከመጋቢት እስከ ግንቦት ከፍተኛ መጠን የሚጥል በመሆኑ ጭቃ የሚበዛባቸው ምቹ ያልሆኑ ወራት ናቸው፡፡ ጅረቶች፣ ፏፏቴዎችን መመልከት ለሚሹ ግን ወራቱ በምቹነት ይምከራሉ:: ፓራኩ በእጽዋት ሀብት ታዋቂ ነው፤ በተራራማ እና ኮረብታዎች ደኖች፣ ቁጥቋጦ እንዲሁም ደልዳላ ሳር ለበስ ሜዳዎች ተንጣሎበታል፡፡
በፓርኩ 290 የአእዋፍ ዝርያዎች መኖራቸውም ተረጋግጧል፤ ከዱር አራዊት አምስቱ ግዙፎች ዝሆን፣ ቀጭኔ፣ ጥቁር አውራሪስ፣ ጐሽ እና ነብር ይገኙበታል:: ከተሳቢ እንስሳት እባብ እና እንሽላሊት በሜዳማ ሣር ምድሩ በዝተው ይስተዋላሉ፡፡ ደኖች እና ቁጥቋጦ በሚበዛው ቀጣና የንብ መንጋ፣ በተለያዩ ቀለማት የተንቆጠቆጡ ቢራቢሮዎች ሲርመሰመሱ መቃኘትም ይቻላል በፓርኩ:: በፓርኩ ቀጣና ለመድረስ በዓየር ትራንስፖርት ተጓጉዞ ኒዬሪ እና ሚዊጋ ላይ አርፎ በተሽከርካሪ መዝለቅ ይቻላል:: በፓርኩ ውስጥ ለጐብኚዎች “The Ark of Tree lodge” ከፍ ካለ ተራራ፤ ሌላኛው “Aberdare country club” የተሰኘው በሚዊጋ አቀበት ላይ የተሰራው ተጠቃሽ ማረፊያ ናቸው፡፡
ለጐብኚዎች ጥር እና የካቲት እንዲሁም ከሰኔ እስከ መስከረም ያሉት ወራት ደረቅ ወቅት በመሆናቸው ይመከራሉ:: ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ኬኒያን ሳፈሪ፣ አፍሪካ ኬኒያ ሳፈሪ፣ እንዲሁም አበርዴር ካንትሪ ክለብ ድረገፆችን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም