መልካም ፀባይ ወይም ስነ ምግባር የሚባለው ስለሌላው ጥቅም እና ደህንነት ሲባል በአንድ ሰው ላይ ለሚጣሉ የሕግ፣ የስነ ምግባር እና የሞራል ግዴታዎች መገዛትን ወይም ለእነዚህ ግዴታዎች ታዛዥ መሆንን የሚያመለክት ጉዳይ እንደሆነ የፍትሕ ሚኒስቴር ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ምክትል ረዳት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ስመኘው መንበሩ ይገልፃሉ፡፡
አቶ ስመኘው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት ለባህላዊ እና ማኅበራዊ መብቶች ጥበቃ እና እውቅና መስጠቱን ጠቁመዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ የወጣው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግም ለመልካም ባህል እና ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆኑ ጉዳዮችን በወንጀል የሚያስቀጡ መሆናቸውን አስቀምጧል ብለዋል፡፡ ይህም በአንድ በኩል መንግሥት በህገ መንግሥቱ የተጣለበትን መልካም ባህሎች እና ልማዶች እንዲጎለብቱ የማድረግ ኃላፊነት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለሞራል እና ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች ከመሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች እና ነጻነቶች እንዲሁም ከዲሞክራሲያዊ መብቶች ጋር ተቃርነው ሲገኙ የመቅጣት ኃላፊነት እንዳለበት የሚያሳይ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
መንግሥት ሕግ እና ፖሊሲ ሲያወጣ እና ሲያስፈጽም፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ወይም ሌሎች እርምጃዎችን ሲወስድ እና ውሳኔዎችን ሲወስን ከመልካም ባህሎች እና ልማዶች፣ ሰብአዊ ክብር፣ ከመሰረታዊ ነጻነቶች እንዲሁም ከህገ መንግስቱ እና ከሌሎች ዝርዝር ሕጎች ጋር ያላቸውን ተደጋጋፊነት እና ተመዛዛኝነት ማጤን ይገባዋል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ሕግ የማኅበረሰብ እሴቶች ነጸብራቅ እና ማስፈጸሚያ መሳሪያ ነውና፡፡
ለሞራል እና መልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆኑ ወንጀሎች ስንል በአንድ አካባቢ ወይም ማኅበረሰብ ለረዥም ጊዜ በባህላዊ፣ ኃይማኖታዊ እና ልማዳዊ ወይም ሞራላዊ ሕግጋት እና እሴቶች ተቀባይነት በማግኘታቸው እንደ ትክክለኛ አድራጎት ተወስደው የሚፈጸሙ ፀባዮችን የሚጻረሩ ሌሎች አድራጎቶችን ማለት እንደሆነ አቶ ስመኘው ገልጸዋል፡፡ እነዚህም በሀገራችን የፍትሐብሔር እና የወንጀል ሕግጋት እወቅና ተሰጥቷቸው ጥበቃ እና ቁጥጥር የሚደረግባቸው ናቸው፡፡
እነዚህ ለሞራል እና ለመልካም ስነ ምግባር ተቃራኒ ነገሮች እንደ ግብረ ሰዶም እና በጋብቻ ላይ ጋብቻ ይጠቀሳሉ፡፡ በተጨማሪም አሳፋሪ፣ ጸያፍ እና የብልግና ድርጊቶችን በአደባባይ መፈጸም እና ማስፈጸም፣ ለህዝብ መግለጽ እና ማሳየት፣ ሴቶች እና ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን ለዝሙት ማቅረብ፣ ማቃጠር እና መነገድ፣ አመንዝራነት እና በዘመዳሞች መካከል የሚፈጸም ጋብቻ ወይም የግብረ ስጋ ግንኙነት…… የመሳሰሉት ወንጀሎች ናቸው፡፡
ከወንጀል ሕጉ ድንጋጌዎች መረዳት እንደሚቻለው የወንጀል ኃላፊነት የሚያስከትለው ፀያፍ ወይም የብልግና ድርጊቶችን በአደባባይ ለህዝብ መግለጽ ወይም ማሳየት ነው፡፡ ይህም ቲያትሮችን፣ ሲኒማዎችን፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ወዘተ… በመጠቀም ሊፈጸም እንደሚችል ይታመናል፡፡ ድርጊቱ ለአንድም ሰው ቢሆን ከተገለጸ ጸያፍ እስከሆነ ጊዜ ድረስ የሚያስጠይቅ ይሆናል፡፡
ባለሙያው እንደሚገልጹት እነዚህ ለሞራል እና መልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ወንጀሎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ይህም በእነዚህ ወንጀሎች በቀጥታ ተጠቂ የሆኑት ሰዎች በቀጥታ ከሚደርስባቸው አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት በተጨማሪ በማህበራዊ ዘርፍ የሚያስከተሉትን ቀውስ ስንመለከት ለተላላፊ በሽታዎች፣ ላለመግባባት፣ ሱሰኝነት፣ ጭንቀት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ መገለል፣ የጥፋተኝነት ስሜት፣ ድብርት፣ ፍርሃት፣ ብስጭትና ራስን ማጥፋት ወዘተ … መንስዔ መሆናቸውን መረዳት ይቻላል፡፡ ጤናን በሚመለከትም እነዚህ ወንጀሎች ለተላላፊ በሽታዎች ዋነኛ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
በኢኮኖሚ ዘርፍም ቢሆን በሞራልና መልካም ጠባይ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የኢኮኖሚ አምራችነት ምጣኔን በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑ ይገለፃል፡፡ በፖለቲካ ረገድም ለሞራልና ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ወንጀሎች ለሌሎች ወንጀሎች (አስገድዶ መድፈር፣ ግድያና ራስን ማጥፋት፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና በሰዎች መነገድ፣ በሱስ መያዝና ህገወጥ ወይም አደገኛ እጾችን ወይም መደኃኒቶችን ማዘዋወርና መጠቀም) መስፋፋት መንሰዔ ስለሚሆኑ በአንድ ሀገር ወይም ማህበረሰብ ሰላምና ደህንነት ወይም ተረጋግቶ መኖር ላይ አሉታዊ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡
በዋናነት ይላሉ አቶ ስመኘው እነዚህን ተግባራት ወንጀል በማድረግ መደንገግ ያስፈለገበት ምክንያት መንግሥት የህብረተሰቡን እሴቶች፤ ሞራል ለመጠበቅ ሲባል ለመልካም ጸባይ ተቃራኒ የሆኑ ተግባራትን ብሎም በማህበረሰቡ ጸያፍ የተባሉ እና የተወገዙ ወይም ብርቱ ተቃራኑ የሆኑ ተግባራትን በዜጎች እንዳይፈጸሙ ለመከላከል ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ተግባራት እንደ መልካም ልምምድ እንዳይቆጠሩ መጠበቅ እና መቆጣጠር ይህን አልፈው ጥፋት የፈጸሙትንም በመቅጣት እና በማስተማር የመጠበቅ ኃላፊነቱን መወጣት ስላለበት ነው፡፡ ይህን የሚወጣው ደግሞ የመጀመሪያው በማህበረሰቡ ፀያፍ የተባሉ እና ተቀባይነት የሌላቸውን ድርጊቶች ወንጀል አድርጎ በመደንገግ ነው፡፡
በሕጉ የተከለከሉትና በወንጀል የሚያስቀጡት ፀያፍና የብልግና ድርጊቶችን እንዲሁም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን መፈጸም ወይም መግለጽ ብቻ ሳይሆን ማስፈጸምም የወንጀል ኃላፊነትን ያስከትላል፡፡ ምክንያቱም ወንጀሉ በቀጥታ ብቻ ሳይሆን በሦስተኛ ወገኖች ወይም ሕጋዊ ሰውነት ባላቸው ድርጅቶች ወይም ተቋማት አማካኝነትም ሊፈጸም ስለሚችል ነው፡፡
መንግሥት ወንጀል በማለት ከፈረጀ እና በሕግ ከደነገገ በኋላ እነዚህ ድርጊቶች በዜጎች እንዲሁም የሕጋዊ ሰውነት የተሰጣቸው ድርጅቶች ፈጽመው ሲገኙ ደግሞ በወንጀል ሕጉ እንቀጽ አንድ በግልጽ እንደተመለከተው አጥፊዎችን መቅጣት ብሎም የተቀጡት ሰዎች በተጣለባቸው ቅጣት ሌሎች እንዲማሩ ማድረግ እና አጥፊዎች ድጋሚ እንደዚህ አይነት ተግባራትን እንዳይፈጽሙ የማድረግ ግዴታ እንደተጣለበት ነው ባለሙያው የሚያብራሩት፡፡
በዚህም መሰረት እነዚህን ተግባራት በ1996 ዓ/ም በወጣው የወንጀል ሕግ በርዕስ አራት ምዕራፍ አንድ ክፍል አራት ስር በመልካም ጸባይ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሉች በሚል ርዕስ ስር ከአንቀጽ 639 እስከ 645 በሚጠቀሱ አንቀጾች እነዚህን ተግባራት ወንጀል አድርጎ ደንግጓቸው እናገኛለን፡፡
እነዚህን ድርጊቶች መፈጸም የሚያስከትለውን የወንጀል ተጠያቂነት እና ቅጣት ስናይ በወንጀል ሕጉ የተለያዩ አንቀጾች ብሎም በኮምፒዩተር አዋጅ ቁጥር ቁጥር 958/2008 አንቀጽ 12 በተደነገገው መሰረት ይለያያል፡፡ የተወሰኑትን ለማዬት እና ለማስገንዘብ ያክል በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 639 ስር ያለውን የሕግ ድንጋጌ ስናይ ‘’ማንም ሰው ህዝብ በሚያዘወትርበት ቦታ ወይም ህዝብ ፊት የግብረስጋ ድርጊትን ወይም ለመልካም ጠባይ ወይም ለመልካም ስነ-መግባር ብርቱ ተቃራኒ የሆነውን ማንኛውንም ሌላ ጸያፍ ድርጊት የፈጸመ ወይም በአኳኋን ያሳየ እንደሆነ” ከሦስት ወር እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከአንድ ሺህ ብር በማይበልጥ ገንዘብ እንደሚቀጣ እና ድርጊቱ የተፈጸመው ደግሞ አካለ መጠን ባልደረሱ ልጆች ፊት በሆነ ጊዜ ቅጣቱ ከስድስት ወር እስከ ዓምስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
እንዲሁም በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 640 የተደነገገውን ስናይ ‘’ጸያፍ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ጽሁፎችን፤ ምስሎችን፤ ስዕላዊ መግለጫዎችን (ፖስተሮችን)፤ ፊልሞችን ወይም ሌሎች ነገሮችን ያዘጋጀ ወደ ሃገር ውስጥ ያስገባ ወይም ወደ ውጭ ሃገር የላከ፤ ያጓጓዘ፤ የተቀበለ፣ የያዘ፣ ለህዝብ ያሳዬ፣ ለሽያጭ ወይም ኪራይ ያቀረበ ያከፋፈለ፣ ያሰራጨ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ከቦታ ቦታ ወይም በእነዚህ ነገሮች የነገደ እንደሆነ” ከሦስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት አና በመቀጮ ነገሩ ከባድ ሲሆን ደግሞ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እስራት እና ገንዘብ እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡ ሌሎች ድንጋጌዎችም በዝርዝር ለመልካም ጸባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን በመዘርዘር ቅጣት ያስቀመጡ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
በወንጀል ሕጉ ወንጀል ተደርገው ከተዘረዘሩት ተግባሮች በተጨማሪ በኮምፒዩተር አዋጁ ቁጥር 958/2008 አንቀጽ 12 ስር ደግሞ አንድ ሰው ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት የኮምፒዩተር ስርዓትን በመጠቀም ያሰራጨ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡ ስለሆነም እነዚህ ለመልካም ጠባይ እና ለሕዝብ ሞራል ተቃራኒ የሆኑ ተግባራትን መፈጸም ሰፋ ባሉ የወንጀል ሕጉ አንቀጾች በዝርዝር የተሸፈኑ በመሆኑ ሁሉንም በዝርዝር ማቅረብ የሚቻል አይሆን፤ ነገር ግን እንደማሳያ ከቀረቡት የሕግ ድንጋጌዎች እና ካስቀመጡት የቅጣት መጠን ተነስተን ለመልካም ጠባይ እና ሞራል የሚፈጸሙ ድርጊቶችን በተለያየ መልኩ መፈጸም ከቀላል እስራት እስከ 10 ዓመት ሊደርስ በሚችል ጽኑ እስራት ሊያስቀጡ የሚችሉ መሆኑን ነው፡፡
በመጨረሻም ባለሙያው እነዚህን ወንጀሎች መቆጣጠር ደግሞ መልካም ባህሎችን ከማሳደግ ባሻገር የሕግና የፍትህ ሥርዓቱን በማሳደግ ተገቢ ቁጥጥር ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡ በተለይም እነዚህ ወንጀሎች በድብቅ የሚፈጸሙና አንዳንዴም ሕጋዊ ንግዶችን ሽፋን በማድረግ ስለሚፈጸሙ ወደ ፍትሕ አካላት ቀርበው (ተጋልጠው) የቅጣት ውሳኔ ሲተላለፍባቸው በብዛት አይስተዋልም፡፡ ስለሆንም ማህበረሰቡም ሆነ የፍትሕ አካላት እነዚህ ወንጀሎች የሚፈጸሙበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውሰጥ በማስገባት የየራሳቸውን ሚና በመጫወት ሀገራዊ ግዴታቸውን መወጣትና ትውልዱን በመልካም ጠባይ እና ስነ ምግባር መቅረጽ እንደሚኖርባቸው ነው የገለፁት፡፡፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም