የሩዋንዳ መንገድ

0
111
Rwanda Political Map with capital Kigali, national borders, important cities, rivers and lakes. English labeling and scaling. Illustration.

ሚያዚያ 1986 ዓ.ም አንድ ግዙፍ የመንገደኞች አውሮፕላን ወደ ኪጋሊ አውሮፕላን ማረፊያ እየተቃረበ ባለበት  ከምድር ወደ ሰማይ በሚተኮስ ሚሳየል ተመታ።  የሁሉም ተሳፋሪዎች ሕይወት አለፈ። የተረፈው ጦሱ ነበር፤ አውሮፕላኑ ውስጥ የብሩንዲ እና የሩዋንዳ ትላልቅ ባለስልጣናት ነበሩበት።  ከዳሬ ሰላም የተነሳው ንብረትነቱ የሩዋንዳ የሆነውን አውሮፕላን ማን እንደመታው እርግጠኛ ማስረጃ ባይኖርም የሩዋንዳ ሰራዊት አባል የሆኑ የቱትሲ ወታደሮች ሳይሆኑ እንደማይቀር ተገመተ። ምክንያቱም የሁለቱም ሀገሮች መሪዎች ከሁቱ ጎሳ ነበሩ።

ቀደም ብሎ  ለሩዋንዳ ሰላም ለማስፈን የተደረገውን የሰላም ስምምነት የመተግበር ሙከራ ለማድረግ ነበር በዳሬ ሰላም ቀጣናዊ ኮንፈረንስ ላይ የተገኙት። በወቅቱ ከቱትሲ ቤተሰብ የተወለደው ጄኔራል ፖል ካጋሜ የሚመራው የሩዋንዳ አርበኝነት ግንባር ውጤታማ በሚባል ግስጋሴ ላይ ነበር። በዚህ መካከል ታዲያ  አውሮፕላኑ ላይ የተፈጠረው ይህ አይነት አስደንጋጭ አደጋ በሩዋንዳ የቱትሲ ማህበረሰብ አባላት ላይ የጥላቻ ዘመቻ ተራገበ። ቱትሲዎችን እንደ ብሄራዊ ስጋት በማድረግ ሁቱዎቹን የመቀስቀስ አደገኛ ስራ በብሄራዊ ሬዲዮው በኩል ሲሰራበት ሰነበተ።

ግድያው የጀመረው ሀሙስ ሚያዚያ 1986 ዓ.ም ነበር። ከሚያዚያ እስከ ሐምሌ ባለው ጊዜ ውስጥ የሩዋንዳን ሰማይ ያስጨነቀው የመከራ ደመና ቶሎ የሚገልጥ አልመስል አለ። በወንድማማች ሩዋንዳውያን መካከል እንደዋዛ የተዘራው ጥላቻ አድጎ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ተለወጠ።

አብዛኛውን የሩዋንዳን ሕዝብ የሚሸፍኑት ሁቱዎች አናሳዎቹን ቱትሲዎች ለማጥፋት በአስደንጋጭ ቁጣ እንዲነሳሱ ተሰበከ። ጎረቤት ጎረቤቱን፣ ቤተሰብ የገዛ የቤተሰቡን አባል፣  መምህራን የገዛ ተማሪዎቻቸውን እንዲገድሉ በይፋ የዘር ማጥፋት ጥሪ ተደረገ።

ብሔራዊ ራዲዮው ‘ዛፎቹን መቁረጥ ጀምሩ!’ … አንድ ቱትሲ ሳያመልጥ እንዲጨርሷቸው ታወጀ፤ በረሮዎችን ግደሉ…የሚሉ አይነት አደገኛ ቅስቀሳ ሲደረግ  ሰንብቷል። ለቱትሲዎች ከለላ የሚሰጥ ምንም አይነት የመንግሥት ተቋም አልነበረም። ባለስልጣናቱ ራሳቸው የወንጀሉ ተሳታፊ ነበሩ እና ቱትሲዎችን መግደል በሕግ የተፈቀደ እስኪመስል በያሉበት እየታደኑ ተገደሉ።

ከዚህ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ቱትሲዎችን የሚደብቅ ምንም ቦታ በሩዋንዳ ምድር አልነበረም።  አያሌ ልብ ሰባሪ የጭካኔ ድርጊቶች ለ100 ቀናት ተፈፀመ። ሁቱዎቹ በነፍስ ወከፍ ገጀራ ይዘው በመውጣት በየመንደሩ ቱትሲዎችን እያደኑ በጭካኔ ጨፈጨፉ። በታሰበበት መልኩ የቱትሲ ሴቶችን ኤች አይ ቪ ባለባቸው ሁቱዎች እንዲደፋፈሩ በማድረግ ስልታዊ የዘር ማጥፋት ተፈፀሙ። በመቶ ቀናት ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን ቱትሲዎች ተገደሉ። በሚሊዮኖች አገር ጥለው ተሰደዱ። ይህን ትራጄዲ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ በዝምታ ተመለከተ። የጥላቻ፣ የጭካኔ እና የግፍ ጥጎች የታዩበት አስጨናቂዎቹ ቀናት የሩዋንዳን በደም አባላ አጨቀዩአት። ያ የሩዋንዳ ሰማይን ከብዶ ለወራት ያስጨነቀው ደመና ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ቱትሲዎችን ሕይወት ካስገበረ በኋላ እየገፈፈ መጣ።

ይሁን እንጂ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉበት አስደንጋጩ የታሪክ ጠባሳ የብዙዎቹን ልብ ሰብሮ ሀገሪቱን የሚጠግን በማይመስል ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ዘፍቋት አለፈ። በተአምር የተረፉት ዓይናቸው እያየ የተገደሉ ወዳጆቻቸውን ስቃይ ከህሊናቸው ተቀርፆ  ዘወትር መንፈሳቸው እየታወከ መኖር ግድ ሆነባቸው። በርካቶች የቤተሰባቸውን ሁኔታ ሳያውቁ እርማቸውን ሳያወጡ የተሰቃዪትን ቤቱ ይቁጠረው። ያልተፅናና ሀዘን፣ ፍትህ ያላገኙ በደሎች፣ ያልታበሰ እንባ ሁለንተናዊ ስብራት እስካልተፈወሱ ድረስ ሩዋንዳ መቼም ሩዋንዳ እንደ ሀገር የመቀጠል እድሏ የተሟጠጠ ይመስል ነበር።

ፍትህ እስካልተሰጣቸው ድረስ የሚሊዮን ሩዋንዳውያን ነፍሳት መቼም አያርፉም፣ በዳዩንም እረፍት እንደነሱት ይኖራል። ስለዚህ ሩዋንዳ ከውጭ አካላት እልቂት ጠማቂ እንጂ መፍትሔ የሚያመጣ አንድም ወዳጅ እንደሌላት ከዚህ በላይ ማረጋገጫ የለም። ለራሷ ችግር ብቸኛዋ መፍትሄ ራሷ ብቻ መሆኗን ቀድማ የተረዳች ይመስላል፣ ቤቷን ዘግታ መከረች፣ ዘከረችና ፍቱን መድሀኒት መስራት ቻለች።

እንዲህ አይነቱን ታሪካዊ ልምድ ለማስተካከል የሩዋንዳ መንግሥት እንደ አንድ የማስተካከያ መንገድ በአካባቢ ደረጃ መንግሥታዊ ተቋማት ለመገንባት ወሰነ። እንደ ሩዋንዳ መንግሥት እነዚህ ተቋማት ዜጎች በማህበረሰባቸው ውስጥ ጉዳዮቻቸውን የሚፈቱበት ፎረም ሆኖ እንደሚያገለግሉ ታመነበት። እነዚህ ተቋማት በተጨማሪ መንግሥት እና ዜጎች ይበልጥ የሚቀራረቡበት መድረክ እንደሚሆኑ እና በሂደቱም የአካባቢ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደቱን ያስጀምረዋል ተብሎ ታመነበት። በሁለተኛ ደረጃም የሸምጋይ ኮሚቴዎችን መመስረት ነበር። እንደ ሩዋንዳ መንግሥት ግምት እነዚህ አካባቢያዊ የሽምግልና ኮሚቴዎች በአካባቢ ደረጃ ያሉ ግጭቶችን በመቀነስ የዜጎችን ጥያቄዎች እንደሚፈቱ ታሰበ።

በ1986ቱ የሩዋንዳ ዘር እልቂት ወቅት እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ ህይወቱን ያጣበት እና ከ250,ሺህ በላይ ሴቶች የተደፈሩበት ነበር። ይህ የዘር ፍጅት፣ የሀገሪቱን ህዝብ ለመንፈስ ስብራት ዳርጎ፣ መሰረተ ልማቶቿን እንዳልነበረ አውድሞ፣ እና ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ አስደንጋጭ መርዶ በመንገር ያለፈ ወደር ያልተገኘለት የክፍለ ዘመኑ ትራጀዲ ሆኖ ይታወሳል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሩዋንዳ ሁሉም ሩዋንዳውያን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደገና በሰላም አብረው እንዲኖሩ የማድረግ መዳረሻ ግብ ያለው ተስፋ ሰጪ የፍትህ እና የእርቅ ሂደት መተግበርን ጀምራ ነበር።

ከዘር እልቂቱ በኋላ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከ120, ሺህ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እና በግድያ በመሳተፋቸው ክስ እንዲመሰረትባቸው ሆኗል። እንዲህ እስር ቤቶቹን ያጥለቀለቀ የበርካታ ጥፋተኞችን የወንጀል ጉዳይ ለማስተናገድ በሶስት ደረጃዎች የተደራጀ የፍርድ ምላሽ ለመስጠት ተሞከረ፡፡ እነርሱም የዓለማቀፍ የወንጀል ችሎት ለሩዋንዳ፣ የሩዋንዳ ብሔራዊ የፍርድ ስርዓት እና የጋቻቻ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ናቸው።

የዓለማቀፍ የወንጀል ልዩ ፍርድ ቤት ለሩዋንዳ የተቋቋመው በ1986 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት ነበር። ልዩ ፍርድ ቤቱ በጥር 01 እና በታህሳስ ወር 1986 ዓ.ም መካከል ባሉት ጊዜያት ውስጥ በሩዋንዳ ውስጥ የተፈፀሙ በዘር ማጥፋት እና ሌሎች አይነት የከፉ የዓለማቀፍ የሰብዓዊ ህግ ጥሰት በመፈፀም ከፍተኛ ተጠያቂነት ያለባቸውን ግለሰቦች የመዳኘት ስልጣን ነበረው። የመጀመሪያ ችሎቱን በ1989 ዓ.ም ላይ የጀመረ ሲሆን በ2003 ዓ.ም ታህሳስ ማብቂያ ላይ ከ92 ክሶች 80ዎቹን አጠናቆ ነበር።

ልዩ ፍርድ ቤቱ ካሳለፋቸው በርካታ ጉልህ የፍርድ ውሳኔዎች መካከል በቀድሞው ከንቲባ ጅን ፖውል አካየሱ ላይ የተላለፈው ውሳኔ ቀዳሚው ነበር። ከንቲባው በዘጠኝ አይነት የዘር ማጥፋት ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ በተፈፀሙ ወንጀሎች በ1990 ላይ ጥፋተኛ ተብሏል። ሌላው በዘር እልቂቱ ወቅት የሀገሪቱ ጠቅላይ ምኒስትር የነበሩት ጅን ካምባንዳ የእድሜ ልክ እስራት የተላለፈባቸው ሲሆን በአንድ የሀገር መሪ በዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈረድ የመጀመሪያው መሆኑ ነው።

የሩዋንዳ ብሄራዊ ፍርድ ቤቶች ዘር ማጥፋቱን በማሴር ወይም ሴቶችን መድፈር ጨምሮ የከፋ ጥፋት በመፈፀም የተከሰሱትን በህግ ፊት አቅርቧል። በ1998 ዓ.ም ላይ ብሔራዊ ፍርድ ቤቶች በግምት 10000 የሚደርሱ የዘር ማጥፋት ተጠርጣሪዎችን ፍርድ ፊት አቅርቧል። በ1999 ደግሞ የሩዋንዳ መንግሥት፣ ለመጨረሻ ጊዜ ከዘር ማጥፋት ጋር በተያያዘ ወንጀል በተፈረደባቸው 22 ሰዎች ላይ ተፈፃሚ ካደረገ በኋላ የሞት ቅጣትን ከልክሏል። ይህም ክሶችን ከዓለማቀፍ ልዩ ፍርድ ቤት ወደ ብሔራዊ ፍርድ ቤቱ የማስተላለፍ እንቅፋትን አስወግዷል።

የጋቻቻ ልዩ የፍርድ ስርዓት ሌላው የዳኝነት ስርዓት በመሆን የተቋቋመ ማህበረሰብ ተኮር ተቋም ነው። በብሔራዊ ፍርድ ቤቱ ገና ፍርድ የሚጠባበቁ በሽዎቹ የሚቆጠሩ ተከሳሾችን ለማስተናገድ ከታች ከመሰረቱ ጀምሮ ፍትህና እና እርቅ ለማምጣት የሩዋንዳ መንግሥት ጋቻቻ በመባል የሚታወቀውን ባህላዊ የማህበረሰብ የዳኝነት ስርአትን  እንደገና አቋቋመ። ገቻቻ በሙሉ አቅም ስራውን የጀመረውም በ1997 ዓ.ም ነበር።

በጋቻቻ ስርዓት በአካባቢ ደረጃ ያሉ ማህበረሰቦች የዘር ማጥፋት ተግባርን ከማቀድ በስተቀር ሁሉንም የዘር ማጥፋት ተጠርጣሪዎችን ወንጀሎች የሚሰሙ ዳኞችን ይመረጣሉ። ፍርድ ቤቶቹ ጥፋተኛው በስራው የመፀፀት ባህሪ ካሳየ እና ከማህበረሰቡ እርቅ ከጠየቀ ቀለል ያለ ፍርድ ይወስንበታል። ብዙ ጊዜ የተፀፀቱ እስረኞች ተጨማሪ ቅጣት ሳይጣልባቸው እና በማህበረሰቡ እንዲያገለግሉ ትእዛዝ ተቀብለው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ።

ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ከ12,000 የሚበልጡ የማህበረሰብ ተኮር ፍርድ ቤቶች 1.2 ሚሊዮን ክሶችን በመላ ሀገሪቱ አስችለዋል። በተጨማሪም የጋቻቻ የፍርድ ቤቶች ለተጎጅዎች የቤተሰባቸው አባላት እና የዘመዶቻቸውን ሞት  እውነታውን የሚያውቁበትን መንገድ በማመቻቸት እርቅ እንዲጠናከር አገልግለዋል። በተመሳሳይም ጥፋተኞች በማህበረሰቡ ፊት ቀርበው ወንጀሎቻቸውን እንዲናዘዙ፣ ፀፀት እንዲያሳዩ እና ይቅርታ እንዲጠይቁ እድል ሰጥተዋል።

በሩዋንዳ የተጀመረው የእርቅ ሂደት ሩዋንዳዊ ማንነትን እንደገና በመገንባት እንዲሁም በመላ ሀገሪቱ የፍትህ፣ የእውነታን እና የሰላምና መረጋጋትን ሚዛን በማስጠበቅ ላይ ያተኮረ ነበር። በሩዋንዳ መንግስት ተበዳዮቹ እና ተጠቂዎቹ በሰላም አብረው እንዲኖሩ ለማደግ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል። ለምሳሌ አሁን ህገ መንግስቱ ሁሉንም ሩዋንዳውያን እኩል መብት እንደሚጋሩ አወጀ። እንዲሁም ልዩነትን እና ከፋፋይ የዘር ማጥፋት ህሳቤዎችን የሚከለክሉ ሕጎች እንዲወጡ ተደረገ።

የእርቅ ጥረቶችን የማድረግ ዋነኛ ሀላፊነት በሩዋንዳ ብሔራዊ አንድነት እና የእርቅ ኮሚሽን ላይ ወደቀ። በእርቅ ዙሪያ የኮሚሽኑ ዋና ዋና ስራዎች  መካከል ‘ኢንጋንዶ’ በመባል የሚታወቀው መርሀግብር ሲሆን በአንድነት በካምፖች ውስጥ የሰላም ትምህርት መስጠት ነበር። ከ1991-2001 ዓ.ም ድረስ ከ90,000 በላይ ሩዋንዳውያን በዚህ የሩዋንዳን ታሪክ እና በሕዝቦች መካከል የተፈጠረውን መከፋፈል መነሾን ግልፅ የማድረግ፣ የሀገር ፍቅርንና የማጠናከር እና የዘር ማጥፋት አስተሳሰብን የመታገል አላማ በነበራቸው መርሀ ግብሮች ላይ እንዲሳተፉ ተደርጓል። በሌላ በኩል ‘ኢቶሮሮ’ የሩዋንዳውያንን እሴቶች የማጠናከር እና ለማህበረሰቡ እድገት የሚታትሩ መሪዎችን የማፍራት አላማ የነበረው መርሀ ግብር አዘጋጅተዋል። ከ1999 እስከ 2001 ዓ.ም ድረስ ከመቶ ሺህ በላይ ሩዋንዳውያን ተሳትፈዋል።

ሴሚናሮች በማዘጋጀት የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል። ከታች ላሉ አመራሮች፣ ለፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ወጣቶች እና ሴቶች በስነልቦና ምክር አሰጣጥ፣ በግጭት  ቅነሳ እና አፈታት ዙሪያ፣ እና በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስልቶች ላይ  አሰልጥኗል።

ሌላው ብሔራዊ ስብሰባዎችን ማካሄድ ነበር። ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የፍትህን፣ መልካም አስተዳደርን፣ ኢሰብአዊ መብቶች፣ በብሔራዊ ደህንነት እና በብሔራዊ ታሪክ ዙሪያ በርካታ ብሔራዊ የምክክር ስብሰባዎች ተደርገዋል።

በሌላ በኩል የሩዋንዳ አንድነት እና እርቅ ኮሚሽን የሩዋንዳ የግጭት ምክንያቶችን እና እንዴት መቀነስ እና መፍታት እንደሚቻል በርካታ የምርመራ ጥናቶችን አድርጎ አሳትሟል።

ሩዋንዳ ረጅም የመሰለ ከባዱን መንገድ ያበጠውን በማፈንዳት መጀመር ነበረባት። እውነታ እና እርቅ የሚል ስልት ለመከተል የወጠነችውን መንገድ በኑዛዜ እንዲተነፍስ ለማድረግ ዜጎች በደላቸውን ህዝብ በተሰበሰበበት እውነቱን እንዲናገሩ የሚያደርግ ስርአት ከእልቂቱ በኋላ የተቋቋመው የሩዋንዳ መንግሥት አመቻቸ፤ ብሶትን አውጥቶ መንገር የፈውስ ግማሽ እንዲሉ። ስለዚህ የሀገሪቱ መንግስት በየቀኑ ከባለስልጣናቱ በመጀመር እስከ ተራው ሕዝብ የሚቀጥል የኑዛዜ ጥሪ አዘጋጀ።

ተበዳዮቹ ከጎዷቸው ሰዎች እና ከብዙ ህዝብ ፊት ለፊት ተገኝተው እንዲናዘዙ እና ይቅርታ እንዲጠይቁ ለማድረግ የጋቻቻ ስርአት አንዱ የግጭት መፍቻ ባህላዊ ፍርድ ቤት ሆኖ ጥቅም ላይ ዋለ። ጥፋተኛው ለአመታት በእስር ከማሳለፍ እስከ የማህበረሰብ ግልጋሎት የሚደርስ ቅጣት ይወሰንበታል፤ ከሁሉም  በላይ ግን ተበዳዮች እውነታቸውን በአደባባይ የሚናገሩበትን እድል አስገኝቶላቸዋል።

ሬኜ ኪንግ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ስትሆን፣ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋው በተጀመረበት ወቅት አመት በአል ወደ ወላጆቿ ቤት አቅንታ ነበር። በርግጥ ከዚያ መአት ተርፋ ዛሬ በካልጋሪ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሆናለች። በጥቃቱ እንደተነሳ ከቤተሰቧ እና ከጓደኞቿ ጋር በመሆን፣ ቋንጭራ ይዘው በዙሪያቸው እየመጡ ከነበሩ ጉዳዮቻቸው ለማምለጥ በጫካ ለመደበቅ እየሸሹ ነበር። ሽሽቱን የጀመሩት 74 እራሳቸውን ነበር፤ በመጨረሻ 14 ሰዎች ብቻ ቀርተው ነበር።

“የእውነት እና እርቅ ኮሚሽኑን አጠቃላይ አውድ ለመረዳት የተወሰነ ጊዜ ወስዶብኛል። ምክንያቱም በባህላዊው የጋቻቻ ስርአት ለእኔ ተገቢ ስፍራ አይደለም ነው የምለው፣ ምክንያቱም የጋቻቻ ሸንጎን እስከማውቀው ድረስ ሁለቱንም ወገን ለመስማት የሚኬድበት ስፍራ ነው። ከዚያም፣ ሰዎች የተፈፀመውን ድርጊት መቀበል እንዲችሉ እና ወደ ቀድሞው እንዲመለሱ የማድረግ የማረጋጋጊያ ፍትህን የሆነ ሰው ያመቻቻል።”

“ነገር ግን በዘር ማጥፋት ዙሪያ ምንም እንደ ቀድሞው የሚባል ነገር የሌለው  እና የሚመለስበት ቀድሞ የለውም። ወደ ኋላ የሚመለስ ምንም አይነት ነገር አልነበረም። ወደ ቀድሞውን ጉርብትናችን እንመለስና ተመልሶ አምድ ላይ የመገናኘትን ጣእም ምን እንደሚመስል ብናውቅ መልካም ይሆናል ከሚለው ታዋቂ ትርክት መሰረት ሀገሪቱ አንዳች መንገድ እየፈለገች መሆኑ የገባኝ እየሰረሰሩ ነበር። የጠፋውን ፈፅሞ ባይመልሰውም ወደ ፊት እንደ ሀገር ለመቀጠል ወሰን ሆኖ አግኝቸዋለሁ።” መብላት ነበር።

“የሰራሁት ነገር ስህተት መሆኑን አውቃለሁ። ስለዚህ ለፈጠርኩት ህመም አዝናለሁ። በዚህ የማግባቢያ ንግግር በህይወት ከተረፉት ይቅርታን የመጠየቅ እና ወደ ፊት ግንኙነታችንን እንደገና የመገንባት እድል አግኝቻለሁ። ነገሩ ሁልጊዜ ይቀላል አይደለም፣ ነግር ግን ወደ ግፊት አብረን ለመስራት በትጋት እንድሰራ አድርጓኛል።” ከአንድ በዳይ ኑዛዜ የተወሰደ፣ በUNDP።

“ቤተሰቤን የገደለብኝን ይቅር ማለት እችላለሁ ብየ አስቤ አላውቅም። ነገር ግን በእነዚህ የእርቅ ሂደቶች አማካኝነት የመቀራረብ ስሜት ማግኘት ችያለሁ። የተፈጠረውን ፈፅሞ መርሳት ማለት አይደለም፣ ነገር ግን ከትዝታው ጋር አብሮ የመኖር እና ለተሻለ ከጥላቻ እና ከመከፋፈል የፀዳ የተሻለ ነገን ለመፍጠር አብሮ የመስራት ጉዳይ ነው፡”፤ ብላለች ይቅርታ ያደረገች አንዲት ሩዋንዳዊት፡፡ የተወሰደ ነው።

(መሠረት ቸኮል)

በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here