ትናንትን መቃኘት፣ ነገን ማለም

0
76

”ትውልድ በመምህር ይቀረጻል፤ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል” በሚል መሪ መልዕክት ክልላዊ የመምህራን ውይይት የማጠቃለያ መድረክ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል። ከሁሉም የክልሉ ዞኖች ከተውጣጡ መምህራን ጋር በተደረገው ውይይት ወቅታዊ የፖለቲካ እና የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች፣ የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት፣ ወቅታዊ የሰላም ሁኔታው እና መፍትሄው በስፋት ተዳሷል፡፡

በውይይቱ ክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር መምህራንን ለማይገባ እንግልት፣ ግድያ እና መሳደድ እንደዳረጋቸው አንስተዋል፡፡ የሀሳብ እና የፖለቲካ ርዕዮት ልዩነት ቢኖርም እንኳ በሀገር ጥቅም እና ሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ መደራደር እንደማይገባም በመምህራኖቹ አጽንኦት ተሰጥቶ ተነግሯል፡፡

የአማራ ክልል ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ሳይፈቱ ጊዜ መውሰዱ ለአሁናዊ የሰላም እጦቱ ዋና ምክንያት መሆኑን አንስተዋል፡፡ የችግሩ መቀጠል ክልሉ በልማት ወደ ኋላ እንዲቀር፣ የሚፈለገው የተማረ የሰው ኃይል እንዳይፈራ እንቅፋት መሆኑም ተነስቷል፡፡ ለትምህርት ጥራት የሚመደበው በጀት ከዋጋ ግሽበት ጋር የተጣጣመ አለመሆኑ በትምህርት ዘርፉ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ከፍተኛ ስለሚሆን ሊታሰብበት እንደሚገባም ተጠይቋል። የመምህራን ደመወዝ አነስተኛ መሆን፣ የደረጃ ዕድገት፣ የዝውውር፣ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ፣ የትምህርት ዕድል ማስተካከያ ይሰጣቸው ዘንድ ተጠይቋል፡፡

በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) መሪ ቃሉ “ነገ ልጆቻችን ምን አይነት ሀገር ይጠብቃሉ” የሚል አደራን እንደተሸከመ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ትውልድ ቀራጭ ባላደራ የሀገር ዋስትና የሆኑት መምህራን ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ጠቁመዋል፡፡

ልዩነቶች የሚፈጥሯቸው አለመግባባቶች በየትኛውም የዓለም ጫፍ የሚያጋጥሙ ናቸው፡፡ ልዩ የሚያደርገው ግጭቶች የሚፈቱበት፣ ጥያቄዎች የሚመለሱበት አግባብ እንደሆነ ዶ/ር ሙሉነሽ አንስተዋል፡፡ “ሀገር የሁሉም ናት፤ የሁሉም ከሆነች ደግሞ ውድቀቷም፣ ልማቷም፣ ድህነቷም፣ ብልጽግናዋም የሁላችንም ነው የሚሆነው” ብለዋል፡፡ ይህንን የተረዳ ማኅበረሰብ በመፍጠር ሁሉም በየሚናው፣ በተሰጠው መክሊት እና ኃላፊነት ልክ ተባብሮ በመሥራት “ለልጆቻችን የተሻለች ሀገር” ማስረከብ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ እንዳሁኑ  ፊደል ባልቆጠሩ ልጆቿ ነጻነቷን አስከብራ የኖረች ኩሩ ሀገር ሆና ሳለ አሁን ወዳለንበት ቀውስ እንድንገባ ያደረጉ ምክንያቶችን ለይቶ በምክክር መፍታት ይገባል፡፡ ለዚህም ትናንትን በደንብ መቃኘት፣ ዛሬን ሆኖ መገኘት እና ነገን ማለም እና ማቀድ ግድ የሚልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

የእርስ በእርስ ግጭት ውጤቱ ጥፋት መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ሙሉነሽ፣ የባዕዳን አጀንዳ አስፈጻሚ ላለመሆን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። በመተባበር ክልሉን ወደ ሰላም መመለስ ቀዳሚው ተግባር ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

አሁን ያለው ችግር እንዲቀጥል መፍቀድ በትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ላይ ጫና መፍጠር ነው፡፡ እንደ ዶ/ር ሙሉነሽ ገለፃ የትምህርት ጥራት ጉድለት ሥራ ፈጣሪነትን ሳይሆን ሥራ ፈላጊነትን ያበረታታል፤ ከተቀጠረ በኋላም ችሎታ የሌለው፣ በአግባቡ የማያገለግል ሠራተኛ እንዲኖር በማድረግ በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል አስተዳደራዊ ችግር እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል።

በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ በበኩላቸው ትምህርት ያለፈን ታሪክ በውል አውቆ  የወደፊቱን ለመተንበይ ዋና መሳሪያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አሁን ያለውን ዘመን ዕውነትን በዕውቀት ላይ ተመስርቶ መበየን የማይቻልበት ዘመን መሆኑን ርእሰ መስተዳደሩ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ደግሞ የማኅበራዊ ሚዲያ በነገሰበት እና ኅብረተሰቡ በስሜት በሚነዳበት ወቅት አሁንም ያለውን እና የቀጣዩን እውነት በትክክለኛው መንገድ ለማወቅ ብቸኛው መንገድ ዕውቀት ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም ዋነኛው አቅም መምህራን መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር ግን መምህራን ከሌላው የማኅበረሰብ ክፍል በተለየ መንገድ የጸጥታ ስጋቱ ሰለባ ሆነው እንዲቆዩ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ችግሩ የመምህራንን ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመሥራት ተነሳሽነት የገደበ፣ የሙያው ባለቤት መሆናቸውን በነጻነት እንዳይናገሩ ያደረገ፣ ትውልድ የመቅረጽ ኃላፊነታቸውን ያለምንም እንከን እንዳይወጡ አድርጎ መቆየቱን ርዕሠ መስተዳድሩ አስታውሰዋል፡፡

የጸጥታ ችግሩ ክልሉ በትምህርት ዘርፍ የተለየ ስብራት እንዲገጥመው ማድረጉን ጭምር ጠቅሰዋል፡፡ በርካታ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ማቋረጣቸውን፣ 60 በመቶ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ በመራቃቸው ጠቃሚ ላልሆነ ማኅበራዊ ሚዲያ እና መሰል ለሕይወት ጠንቅ ለሆኑ ነገሮች መጋለጣቸውን አስታውቀዋል፡፡ ይህም ለነገ ሕይዎታቸው ብልሽት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ ዶክተር፣ ፓይለት (አብራሪ)… እና ሌላ ሕልምን ዛሬ ላይ ሆነው በነገ ለማሳካት አርቀው የሚያስቡ ታዳጊዎች የጦርነት ልምምድ ሲያደርጉ ማስተዋል እጅግ እንደሚያሳዝንም ርዕሠ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገልጸዋል፡፡

“መምህራን ፖለቲከኞች፣ ትምህርት ቤቶችም የፖለቲካ መድረክ አይደሉም” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ፣ ትውልድን በሚቀርጹ እና ማኅበረሰብን በሚያገለግሉ መምህራን ላይ ጥቃት ሊፈጽምባቸው እንደማይገባ ተናግረዋል።

አቶ አረጋ ከበደ መንግሥት አቅሙ በፈቀደ መጠን የመምህራንን የአካል እና የሙያ ደኅንነት ለማስከበር እንደሚሠራ ገልጸዋል። “መምህራንን ማገት እና ማጎሳቆል እንደ ዝና የሚቆጠርበት የጸጥታ ችግር ውስጥ እንገኛለን” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ፣ መምህራን ማስተማር በሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ውስጥ ብቻ መማር ማስተማር እንዲያከናውኑ እንጂ ችግር ባለበት አካባቢ ገብተው እንዲያስተምሩ እስካሁን የተቀመጠ አቅጣጫ አለመኖሩንም አረጋግጠዋል፡፡ በአጠቃላይ የጸጥታ ችግሩ መምህራንን ያልተፈለገ መስዋዕትነት እንዳያስከፍል ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ሲካሄድ መቆየቱን ነው ረዕሠ መስተዳድሩ ያስታወሱት፡፡

መምህራን ከጥቅማ ጥቅም ጋር በተገናኘ ላነሱት ጥያቄ ርእሰ መስተዳደሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ለመምህራን የቤት መሥሪያ የቦታ ካሣ 318 ሚሊዮን ብር መፈቀዱን አስታውቀዋል፡፡ ከደረጃ ዕድገት፣ ከዝውውር እና ከመሰል የመምህራን ጥቅማ ጥቅሞች መከበር ጋር በተገናኘ የተነሱ ጥያቄዎች በሂደት ተፈትሸው ማስተካከያ እንደሚሰጥባቸው ገልጸዋል፡፡

የጄአይጂ ክፍያን በተመለከተም በአማራ ክልል የሚኒስትሮች ምክር ቤት የወሰነው መፈጸሙን አንስተው ከመምህራንም አኳያ የክልሉ መንግሥት ያስቀረው ጥቅማጥቅም እንደሌለ አረጋግጠዋል፡፡

ለትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ በጀት ቢመደብም አብዛኛው እየዋለ ያለው ለደሞዝ ክፍያ ነው ያሉት ርእሰ መስተዳደሩ፣ ትምህርት ዘርፉ ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንት ግን አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ የሥራ ገበያውን ታሳቢ ባደረገ አግባብ የትምህርት ዘርፉን መደገፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በአማራ ክልል ለተፈጠረው ግጭት መንግሥትም ይፋዊ የሰላም ጥሪ ማቅረቡን ያስታወሱት ርእሰ መስተዳደሩ፣ መምህራን የክልሉን ችግር ምንጭ እና መፍትሄ አስተውለው ለመፍትሄው በትጋት እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here