ጤና ይስጥልኝ አንባቢያን! እንዴት ናችሁ? የዛሬ ሀሳቤ መነሻ ሰሞናዊ መረጃ ነው፡፡ በቅርቡ በአንድ ሙያዊ ስልጠና የመሳተፍ እድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ ያኔ ታዲያ “የብልጽግና መንግሥት የሚያራምደው የመሀል ፖለቲካ ነው” የሚል ሀሳብ ከአንድ የፓርቲው አመራር ሲነገር ሰማሁ፡፡
የመሀል ፖለቲካ ማለት ቀለል ባለትርጓሜ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ እና ያሉ ፓርቲዎች እና አገዛዞች ከሚያራምዷቸው የተለያዩ ርእዮተ ዓለሞች እና ከአከናዎኗቸው ተግባራት መካከል መልካም መልካም የሆኑትን እየመረጡ ማራመድ እና ተሞክሯቸውን መውሰድ ነው፡፡
ይህንን እሳቤ በግሌ ስለተቀበልኩት እና ስለወደድኩት ቀጥሎ የመጣልኝ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ እና ከነበሩ የአገዛዝ ሥርዓቶች ሊቀሰም የሚችል ምን ዓይነት መልካም ተሞክሮ ይኖራል? ምንስ መውሰድ እንችል ነበር የሚለው ጥያቄ ነበር፡፡
ለጥያቄዬ ምላሽ አገኝ ዘንድ ቢያንስ ቢያንስ ከንጉሣዊው ሥርዓት እስከ ብልጽግና ዘመን በነበረው አገዛዝ ውስጥ የከተከናዎኑ ተግባራትን ሁሉ ማጥናት እና መመርመር ያለብኝ ቢሆንም ጉዳዩ ግን ሰፊ ጊዜና ምርምር በመጠየቁ በናሙናነት የደርግን ሥርዓት ብቻ በወፍ በረር መቃኘት ተገደድኩ፡፡
እናም የወፍ በረር ቅኝቴ ውጤት ቀይ ሽብር የተሰኘው ጥፋቱ ባያደበዝዝበት ኖሮ ደርግ የሄደበት መንገድ እና ካከናዎናቸው ተግባራት በመልካም ተሞክሮነት ሊቀሰሙ እና ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚችሉ በርካታ ስኬቶች እንደነበሩት መረዳት ቻልኩ፡፡
የየትኛውም አገዛዝ የሚከተለው ርእዮተ ዓለም እና የሚያራምደው ሥርዓት መልካም መሆን እና አለመሆን የሚለካው ለሚመራት ሀገር እና ህዝብ በሚያስገኘው ልማት፣ እድገት እና ጥቅም በመሆኑም ደርግ አሳክቷቸዋል ያልኳቸውን ትዝብቶቼን አንድ፣ ሁለት… እያልኩ ላጋራችሁ፡-
- ሚሊዮኖችን ከመሀይምነት ነፃ አውጥቷል
ትምህርት የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ፣ የብልፅግናም ሀዲድ መሆኑን ቀድሞ የተረዳ ይመስላል – ደርግ፡፡ “ያልተማረ ይማር፣ የተማረ ያስተምር!” ከሚል መፈክር (መሪ ቃል) ጋር “የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ፣ እድገት በህብረት የእውቀት እና የስራ ዘመቻ…” የሚል ሰፊ እቅድ ዘርግቶ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ጭምር ምሁራን እና ተማሪዎች እንዲዘምቱ እና ያልተማሩ ዜጐችን ሁሉ እንዲያስተምሩ አደረገ፡፡
ፆታ እና እድሜ ባልገደበው በዚሁ ዘመቻ ታዲያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጐች ማንበብ መፃፍ ችለው ከመሀይምነትም ነፃ ወጡ፡፡ ይህ ታላቅ ዘመቻ ዓለምን ያስደመመ፣ ዓለማቀፍ እውቅና እና ሽልማትን ያስገኘ ደርግ በትምህርቱ ዘርፍ ያስመዘገበው የማይታበል ታላቅ ስኬት ነውና አንድ በሉ፡፡
- የተራቆቱ ተራሮችን ደን አልብሷል
የዓለማችንን ሰፊ ጥቅጥቅ ደን መገኛ አማዞንን “የዓለም ሳምባ” እያልን መጥራታችን በአጭር ቃል እስትንፋሳችን በመሆኑ ነው፡፡ ከሚያመነጭልን ኦክስጂን ባሻገር ለዝናብ መኖር የሚያበረክተው አስተዋፅኦም ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ላይ በቁሳቁስ ልማት እና ማገዶ ዘርፍ ለሰው ልጅ የሚሰጠው ግልጋሎት ሲታከልበት አስፈላጊነቱ ግድ የሚለንን ደን “ዛፍ ህይወት ነው” እያልንለት እንገኛለን፤ ዛሬ ድረስ፡፡
ይህን የደን ጥቅም በውል የተረዳው እና በዚያው ዓመታትም በወሎ እና ትግራይ ለተከሰተው እና ህዝብ ለጨረሰው ድርቅ አንደኛው መንስኤ የአካባቢ መራቆት መሆኑን ጠንቅቆ የተገነዘበው ደርግ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከወን የደን ልማት ዘመቻ ከፈተ፡፡
በዘመቻው እድሜው እና አቅሙ ለሥራ ብቁ የሆነ ዜጋ ሁሉ በሚኖርበት ቀበሌ እና አቅራቢያ በሚገኙ የተራቆቱ ተራሮች ላይ ዛፍ እንዲተክል ተደረገ፤ ዜጐች በዘመቻ የተከሉት ችግኝ እንዲፀድቅም ከእንስሳት ንክኪ የሚጠብቁ እና የሚንከባከቡ ሰራተኞች ተቀጠሩ፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ታዲያ ተራቁተው የነበሩ ተራሮች ሁሉ ደን ለበሱ፤ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለምን የአየር ሚዛን ለማስጠበቅ ትልቅ ፋይዳ በሚያበረክተው ደን ልማትም ኢትዮጵያ ኮራች፤ መሪዎቿም ስለስኬታቸው ለሽልማት በቁ፤ ሁለት አትሉም? በነገራችን ላይ የተከልነወን በአግባቡ ባለመንከባከባችን አምና በተከልንበት ተራራ ላይ ዘንድሮም ሌላ ችግኝ እየተከልን እንገኛለንና የደርግን የመንከባከቢያ ተሞክሮ መውሰድ እንዳለብን ነው የታዘብኩት፡፡
- “መሬት ላራሹን” አሳክቷል
በፊውዳሊዝም ሥርዓት ተንሰራፍቶ የነበረውን የመደብ ልዩነት ለማስቀረት ምሁራን እና ተማሪዎች በሠላማዊ ሰልፍ ጭምር ያቀርቡት የነበረውን ህዝባዊ ጥያቄ በአዋጅ የመለሰው ደርግ ነው፡፡ በዚህ እርምጃውም የመሬት ከበርቴዎች በገባሩ አርሶ አደር ላይ ያደርሱት የነበረው ብዝበዛ ቀርቷል፤ አርሶ አደሩ የመሬት ባለቤት ሆኗል፤ ሞፈር ዘመት ተወግዷል፤ በዚህም በዜጐች መካከል የነበረው የተጋነነ የሀብት ልዩነት እንዲቀራረብ አስችሏል፡፡
በፋብሪካዎች እና ተቋማት የሚሰሩ ወዛደሮች ተመጣጣኝ ክፍያ እንዲያገኙ እና ሰብአዊ መብቶቻቸው እንዲጠበቁ መደረጉም የዚሁ የመደብ ልዩነትን የማቀራረብ ስኬታማ ውጤት ነበር፡፡
- በ “ሰፈራ” የአርሶ አደሩን ህይወት ማዘመን ችሎ ነበር፡፡
ሰማኒያ አምስት በመቶው ህዝብ አርሶ አደር በሆነባት ሀገር የዚህን ህዝብ አኗኗር፣ ስልተ ምርት እና የምርት መገልገያ መሳሪያዎች ሁሉ እስካልዘመኑ ድረስ ሀገራዊ እድገት እንደማይታሰብ የተረዳው ደርግ አርሶ አደሩን ከተበታተነ ጐጥ እያሰባሰበ በተመረጡ የሰፈራ መንደሮች እንዲከትሙ አድርጐ ነበር፡፡
ሰፈራው የተካሄደው በሁለት መንገድ ነበር፡፡ አንደኛው በድርቅ የተጠቁ፣ ዝናብ አጠር የሆኑ እና ለምነታቸው በተራቆተ የምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮችን ለም ወደሆነው የምእራብ ኢትዮጵያ (የጎንደር፣ የጎጃም እና የወሎ) አካባቢዎች ማስፈር ሲሆን ሁለተኛው በሌሎቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ከየጐጡ እየተሰባሰቡ በተመረጠ መንደር እንዲሰፍሩ ማድረግ ነበር፡፡
ሰፈራው አርሶ አደሮቹ ዘመናዊ እርሻ እንዲጠቀሙ፣ ውኃ፣ መብራት፣ ት/ቤት፣ ጤና ጣቢያ… የመሳሰሉትን መሠረተ ልማቶች እንዲያገኙ ያደረገ ብቻ ሳይሆን በተለይ በድርቅ ከሚጠቃው ምስራቅ ኢትዮጵያ ለተነሱት ደግሞ ብዙ ህይወትን የታደገ ኘሮግራም ነበር፡፡
በጣና በለስ ኘሮጄክት አማካኝነት ሰፊውን የመተከል ለም መሬት በማልማት ከራሳቸው አልፈው ለመላው ኢትዮጵያዊ እና ለውጪ ገበያ ጭምር የሚተርፍ የግብርና ምርት እንዲያመርት የታቀደለትን የፓዊ ሰፈራ እና የየትኖራ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበራትን የሰፈራ ኘሮግራም ማስታወስ ብቻ ዛሬም ድረስ የሚያስቆጭ እና ወደ ፊትም በሜካናይዝድ እርሻ እንድንቀዬር መልካም ተሞክሮ የሚሰጥ መሆኑን የምንማርበት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡
ኘሮግራሙን ደርግን ለመጣል የፖለቲካ ኘሮፖጋንዳ የተጠቀመበት እና በኋላም በስልጣን ዘመኑ እንዲፈራርስ ያደረገው ህወሀት ኋላ ላይ “የኔ” የሚለውን ህዝብ በሰፈራ መንደሮች እንዲኖር ማድረጉን ስናስብ ደግሞ ኘሮግራሙ አዋጭና ጠቃሚ መሆኑን መገንዘብ አያቅተንምና ዛሬም የብልጽግና (የእድገት) መንገድ እንደሆነ ይታየኛል፡፡
- የሀገር ሉአላዊነትን ለማስከበር ሁሌም ዝግጁ እና ቁርጠኛ ነበር
ደርግ ሀገሩን ጠንካራ እና የማትደፈር ለማድረግ በነበረው ቁርጠኛ ፍላጐት ሳቢያ ጠንካራ የባሕር ኃይል፣ ውጤታማ እና ብቁ አየር ኃይል እና ፅኑ የሀገር ፍቅር ያለው የምድር ጦር እግረኛ ሰራዊት መገንባት ችሎ ነበር፡፡ በዚህም ታላቋን ሶማሊያን እንገነባለን በሚል በምስራቅ እስከ አዋሽ 700 ኪ.ሜ፣ በደቡብ 350 ኪ.ሜ ለመያዝ አቅዶ ወረራ በመፈፀም ድሬዳዋ ድረስ የዘለቀውን የዚያድባሬ ወራሪ ሰራዊት በመምታት ጥቃቱን በአጭር ጊዜ ቀልብሶ የካራማራን ድል አጐናጽፏል፡፡
- በዲኘሎማሲው ዘርፍም የተሳካለት ነበር፡፡
የአፍሪካ አባት የምንላቸው ቀዳማዊ ኃይለ ሠላሴ፣ ኩዋሚ ኑክሩማህ ፣ ኔሬሬ እና አጋሮቻቸው የመሰረቱትን የአፍሪካ ህብረት አጠናክሮ አስቀጥሏል፤ በቅኝ ግዛት ስር የነበሩት ዝምባብዌ እና ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ነፃ እንዲወጡ ሰራዊት እስከማሰልጠን በዘለቀ ቁርጠኝነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፤ የአፍሪካ ኩራትም ሆኗል፡፡
የዲኘሎማሲያዊ ስኬቱ ከአህጉሩም አልፎ እስከ ሩስያ፣ ኩባ፣ ኮሪያ ሊቢያ እና የመን ድረስ የዘለቀ ስለነበር እብሪተኛው ዚያድባሬ በወረረን ጊዜ የአነዚህን ሀገራት ወታደራዊ ድጋፍ እስከማግኘት አዝልቆናል፡፡
ይኽው ዲኘሎማሲያዊ ግንኙነት ከወታደራዊ ድጋፍም አልፎ በትምህርቱ መስክ ለበርካታ ኢትዮጵያዊያን የውጪ የትምህርት እድል (ስኮላር ሺኘን) አስገኝቷል፡፡
- የብሔር እና የፆታ እኩልነትን በማሳፈን ግንባር ቀደም ተዋናይ ነበር፡፡
ያራምደው የነበረው የሶሻሊዝም ሥርዓት በራሱ በሰው ልጆች እኩልነት የሚያምን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በኢትዮጵያ የብሔረሰቦች ጥናት ‘ኢንስቲትዩትን’ በማቋቋም በምሁራን ማሰጠናት የጀመረው ደርግ ነው፡፡ በሀገሪቱ ሬዲዮ ጣቢያ እና ኘሬስ ድርጅት ከአማርኛ ውጪ በኦሮምኛ እና ትግርኛ ሥርጭት እንዲጀመር ያደረገውም ደርግ ነው፡፡
ከፆታም አኳያ ሴቶች ከማጀት ወጥተው የመማር፣ የመስራት፣ የመንቀሳቀስ እና የመዝናናት መብት እንዲኖራቸው፣ የመምረጥ እና መመረጥ መብታቸው እንዲከበር ያደረገውም የዚያው ሥርዓት መሪ ደርግ ነው፡፡
- የሲቪክ ማህበራትን አቋቁሟል
በመላ ሀገሪቱ የገበሬዎች፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የመምህራን፣ ከተማ ነዋሪዎች ወ.ዘ.ተ ማህበራትን በማቋቋም ቡድናዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንዲሰሩ እና እንዲታገሉ አድርጓል፡፡
- በቁጠባ ቤቶች ግንባታ ቀዳሚ ነው
አሁን ድረስ ዜጐችን ለድህነት እየዳረገ የሚገኘውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ ሲል አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጐች በአነስተኛ ኪራይ የሚኖሩባቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች መገንባት የጀመረው ደርግ ነው፡፡ በእነዚያ ቤቶች ዛሬ ድረስ የዘለቁ በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጐች በእዛው ቤት ልጅ ወልደው አሳድገው ለቁም ነገር አብቅተውበታል፡፡
- ለኢትዮጵያ ጀግኖች እና ህፃናት አምባዎችን ገንብቷል
አባቶቻቸው የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስከበር ሲታገሉ የተሰዉባቸውን ህፃናት እና ለሀገራቸው ሲታገሉ አካላቸው የጐደለን የኢትዮጵያ አርበኞች መንከባከብ የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር መሆኑን የተገነዘበው ደርግ ለህፃናቱ እና ለተጐጂዎቹ ጀግኖች መኖሪያ፣ መጦሪያ እና መማሪያ አምባዎቹም ገንብቷል፡፡
አንባዎቸ ሀገር ጅግኖቿን እና ባለውለታዎቿን እንደምታከብር ማሳያ እና ለዜጐች የሀገር ፍቅር መገንቢያም ነበሩ፡፡
አንባዎቹን ህውሀት ስልጣን በጨበጠ ዘመን ያፈረሳቸው ቢሆንም ዛሬ ግን አስፈላጊነታቸው ታምኖበት እንደገና እንዲቋቋሙ የማድረግ ተግባር በሀገር መከላከያ ሠራዊት በኩል እየተደረገ በመሆኑ ይኸው የደርግ ጅምር እጅግ መልካም እንደነበር ያመላክታል፡፡
- ጉቦ እና ስርቆትን አጥብቆ ይከላከል ነበር
በደርግ ዘመን ጉቦ መብላት እና ሙስና ውስጥ መገኘት በራስ ላይ እንደመፍረድ ነበር፡፡ የዚያው ዘመን ሹማምንት የግላቸው መኖሪያ ቤት እንኳ ያልነበራቸው ሆነው መገኘታቸው የንፅህናቸው ማሳያ ነው፡፡
ምርትን ደብቆ ዋጋ ማስወደድ እና የአንድ ኮታ ለሌላ አሳልፎ መስጠትን የመሳሰሉ የንግድ ሻጥሮችን በማያወላውል እርምጃ ማክሸፍም ችሏል፡፡
- ኪነጥበብን እና ስፖርትን በልዩ ትኩረት አሳድጓል፡፡
ኪነ ጥበብን ርእዮተ ዓለምን ለማስረጽ ከመጠቀም አልፎ ለተዝናኖት እና ለገፅታ ግንባታም ጭምር እንዲያገለግል ያደረገው ደርግ ነው፡፡ በየክፍለ ሀገራቱ የከፍተኛ ኪነት የተባሉ ቡድኖችን በማደራጀት የኢትዮጵያ ባህል እና ትውፊቶችን ማስተዋወቅ ተችሏል፡፡ በዚህ ረገድ የላሊበላ፣ ፋሲለደስ እና ግሽ ዓባይ ኪነቶችን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ በተለያዩ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ከተሞች በመዘዋወር የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ያስተዋወቀው “ህዝብ ለህዝብ የተሰኘው” የኪነት ቡድንም የዚያው ትኩረት ውጤት ነበር፡፡ ከእነዚያ የኪነ ጥበብ ቡድኖች ውስጥም በርካታ የስነ ጥበብ ባለሙያዎችን እና የጥበብ ሥራዎችን ማግኘት ተችሏል፡፡
ደርግ በስፖርቱ በኩል የነበረው ትኩረትም ቀላል አልነበረም፡፡ ብቁ ዜጋ ለማፍራት በሚል መርህ ከታዳጊ እስከ ጐልማሳ የሚሳተፍበት “ማስ ስፖርት” ማካሄድ የዘወትር ጧት ተግባር ነበር፡፡ በውድድር ስፖርቶች ዘርፍም በት/ቤቶቹ በመከላከያ እና ፖሊስ ሰራዊቶች ውስጥ ዓመታዊ ውድድሮች ይካሄዱ ነበር፡፡ ፋብሪካዎች ክለብ ይገነባሉ፤ የየክፍለ ሀገሩ ምርጥ ቡድኖችም አመታዊ ፉክክር ያደርጉ ነበር፡፡
14ኛውን የመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ ዋንጫ የወሰድነውም በዚሁ ዘመን መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በዚያ ጊዜ ታዲያ አማኑኤል እና ነጋሽ ተክሊት ከኤርትራ፣ ገብረ መድን ኃይሌ ከጐጃም፣ ሙሉጌታ ከበደ ከወሎ የተገኙ የክፍለ ሀገራት ምርጥ ቡድኖች ፍሬ ነበሩ፡፡ ይህም ስፖርት በየክፍለ ሀገሩ ጭምር ከፍተኛ ትኩረት እንደነበረው አመላካች ነው፡፡
ቀሪውን እናንተው ጨምሩበትና ካለፉት እና ካለው አገዛዝ መልካም መልካሙን እየመረጡ በተሞክሮነት በመውሰድ መጠቀምን /ማስቀጠልን/ ይከተላል ለተባለው የመሀል ፖለቲካ መርህ የስኬት መንገድ እናመላክት እላለሁ፡፡
(ጌቾቪች)
በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም