ብክለት ይብቃ፣ ውበት ይምጣ!

0
85

በዓለም ላይ እያጋጠመ ያለው የፕላስቲክ ቆሻሻ ብክለት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም (United Nation Environment Programme – UNEP) ሀገራት እና ተቋማት በካይ የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን ለማስወገድ የተለያዩ አማራጮችን ተግባራዊ እንዲያደረጉ አሳስቧል።

በመሆኑም የዓለም ሀገራት ይህን ችግር ለመቅረፍ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ ባሻገር የሚወጡ ሕጎችን እና መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝቧል። መረጃው አክሎም በየዓመቱ በአማካይ 400 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የፕላስቲክ ቆሻሻ ይመነጫል ይላል። በአሁኑ ጊዜም ከ75 እስከ 199 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የፕላስቲክ ቆሻሻ በውቅያኖስ እና በሐይቆች ውስጥ እንደሚገኝ አመላክቷል።

በዚህም በየዓመቱ ከ100 ሺህ የሚበልጡ የውቅያኖስ እንስሳት በፕላስቲክ ብክለት ምክንያት ይሞታሉ። በተጨማሪም በምድር ላይ የሚኖሩ እንስሳት ሳይቀር የወደቀን ፕላስቲክ ሲመገቡ ለሞት እየተዳረጉ መሆኑን መረጃው ጠቁሟል።

የጅርጅቱ መረጃ እንዳብራራው የኘላስቲክ ቆሻሻ ለመበስበስ ከ400 ዓመታት በላይ ይወስድበታል። ይህም በአፈር ጤንነት ላይ ጉዳቱ የከፋ ነው። ኘላስቲክ በአፈር እና ውኃ አካላት ላይ፣ በአካባቢ አየር፣ በአካባቢ ሥነ ውበት፣ በሰው እና በእንስሳት ጤና ብሎም በምጣኔ ሀብቱ ላይ የሚያስከትለው ችግር ከፍተኛ ነው።

ችግሩን ለመከላከል ታዲያ የሰው ልጆች የፕላስቲክ ከረጢት ከመጠቀም ይልቅ ከካርቶን፣ ከጨርቅ እና ከመሠል ነገሮች የሚሠሩ የዕቃ መያዣ ከረጢቶችን መጠቀም እንደሚገባ ተመላክቷል።

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ከሰሞኑ የፕላስቲክ ምርቶች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያደርግ አዋጅ ወጥቷል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅ ቁጥር 1383/2017 ሥራ ላይ እንዲውል ማጽደቁ ይታወቃል፡፡ አዋጁ የአየር፣ የውኃ እና የአፈር ብክለትን ለመቀነስ እና የዜጎች ጤንነትን ለመጠበቅ የጎላ አበርክቶ ያለው እንደሆነም ተነግሯል፡፡

የብክለት ቁጥጥር፣ የሚወጡ ሕጎችን ተግባራዊ ማድረግ እና ከማኅበረሰቡ ጋር ተግባብቶ መሥራት ደግሞ ግንባር ቀደም ተግባራት ሊሆኑ እንደሚገባ ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል።

ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም የዓለም አካባቢ ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ “የፕላስቲክ ብክለትን እንግታ” በሚል መሪ መልዕክት ክልላዊ የማጠቃለያ ውይይት በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል። የፕላስቲክ ብክለት በአካባቢ ላይ እያደረሰ ያለውን ተጽዕኖ የሚያሳዩ ጥናታዊ ፅሑፎች ቀርበውም ውይይት ተደርጓል። በውይይት መድረኩም የሃይማኖት አባቶች፣ የናቡ ኢትዮጵያ ባለሙያዎች፣ የምርምር ተቋማት፣ በማኅበረሰቡ ተቀባይነት ያላቸው ግለሰቦች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በዓሉ ከግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል በፓናል ውይይት፣ በጽዳት ዘመቻዎች፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጠበቅ በሚያስችሉ ተግባራት እና በተለያዩ ሁነቶች በዞኖች፣ በከተማ አስተዳደሮች፣ በወረዳዎች እና በቀበሌዎች ሲከናወን ቆይቶ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም ክልል አቀፍ የማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ ተከናውኗል።

በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ምቹ  የመኖሪያ አካባቢ ለመፍጠር እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን አስገንዝቧል። የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ በልስቲ ፈጠነ በውይይት መድረኩ እንዳብራሩት ብክለትን ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ ይገኛል። ምድርን ከብክለት በንቃት የሚጠብቅ ትውልድ መገንባት እንደሚገባም ጠቁመዋል። ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን በየአካባቢው ከመጣል ይልቅ መልሶ የመጠቀም ልምድ እንዲያዳብር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልፀዋል።

የዘንድሮው የዓለም አካባቢ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ52ኛ፣ በኢትዮጵያ ለ32ኛ ጊዜ፣ በአማራ ክልል ደግሞ ለ28ኛ ጊዜ ነው የተከበረው። የዓለም የአካባቢ ቀን በ1973 ዓ.ም በየዓመቱ እንዲከበር ሲወሰን በአካባቢ ላይ የሚደርሱ የአካባቢ ብዝኃ ህይወት መጎሳቆል እና የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

ምክትል ኃላፊው አቶ በልስቲ እንዳሉት ከፕላስቲክ በተጨማሪም የደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ የአካባቢን ንፅህና መጠበቅ፣ አካባቢን ከቆሻሻ ፅዱ ማድረግም የየዕለት ተግባር ሊሆን ይገባል። ማኅበረሰቡ ፅዳትን ደግሞ ከራሱ መጀመር ግድ ይላል።

አቶ በልስቲ እንዳብራሩት ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ለዱር እንስሳት ምቹ የሆነ አካባቢ ለመፍጠር፣ የአካባቢ ጥበቃ ዘላቂነትን የማረጋገጥ፣ የደን ሀብትን የመጠበቅ እና የማልማት ሥራ እየሠራ ነው። ይሁን እንጂ የደረቅ እና የፍሳሽ ቆሻሻዎች አወጋገድ ችግር በአካባቢ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል። በተለይም የፕላስቲክ አጠቃቀም እና አወጋገድ ችግር ፈታኝ መሆኑን ነው የገለፁት። ንጹህ እና ጤናማ አካባቢ ለመፍጠር አካባቢን በመጠበቅ፣  በማልማት እና በቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ላይ ሁሉም በኃላፊነት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

አካባቢን በሚበክሉ እና በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ጉዳት በሚያደርሱ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች እና ተቋማት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የተናገሩት አቶ በልስቲ ፕላስቲክ ለረጅም ዓመታት በአፈርም ሆነ በውኃማ አካላት ላይ በመቆየት ለፍጥረታት ሁሉ ጠንቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕላስቲክ በሰዎች፣ በእንስሳት እና በብዝኃ ሕይወት ላይ ጉዳት እያደረሰ፣ በሥነ ምኅዳር ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ እያስከተለ ይገኛል። ፕላስቲክን በየቦታው ከመጣል መቆጠብ፣ በአግባቡ መያዝ እና ወደ ፋብሪካዎች በማስገባት መልሶ መጠቀም እንደሚገባ ምክትል ኃላፊው መክረዋል። ስለዚህ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለራሱ፣ ለቤተሰቡ እና ለትውልዱ ጤና በማሰብ አካባቢውን ማጽዳት፣ ውብ፣ ፅዱ እና ለኑሮ ተስማሚ ከተማን ለመፍጠር ኅብረተሰቡ ባለቤት መሆን አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

የፕላስቲክ ብክለት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ የናቡ ኢትዮጵያ ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአቅም ግንባታ አማካሪ ባይህ ጥሩነህ  ናቸው። አማካሪው ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሑፍ የኘላስቲክ ወይም የፌስታል ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱ በአካባቢ፣ በምጣኔ ሀብት፣ በጤና እና በከርሰ ምድር ውኃ ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አብራርተዋል።  ናቡ ኢትዮጵያ መንግሥታዊ ያልሆነ ሀገር በቀል ድርጅት ሲሆን ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል በአካባቢ ጥበቃ፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና ልማት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።

አማካሪው እንዳሉት የፕላስቲክ ብክለትን ለመከላከል ናቡ ኢትዮጵያ በባሕር ዳር እና ጎንደር ኘላስቲክን መልሶ መጠቀም ላይ እየሠራ ይገኛል። ለአብነትም በባሕር ዳር ከተማ ፈታኝ የነበረው የፕላስቲክ ብክለት ፕላስቲክን መልሶ መጠቀም የሚችሉ ማሕበራት ተደራጅተው ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ መቀነሱን ጠቅሰዋል። ፕላስቲክ ከብክለት መንስኤነት ወጥቶ ለብዙዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ለዕለት እንጀራቸው ማግኛም ሆኗል።  ከዚህ ቀደም የተለያዩ ፕላስቲኮች (ሃይላንዶች) መፋሰሻ ቱቦዎችን (ዲሽ ቦይ) በመዝጋት ከተማዋን በጎርፍ እንድትጥለቀለቅ ምክንያት ነበሩ። ማኅበረሰቡ የሚበሰብሱ እና የማይበሰብሱ ቆሻሻዎችን ቤት ላይ እንዲለይ እየተሠራም ይገኛል። የፕላስቲክ አጠቃቀምን ለማስተካከል አማራጮችን በተመጣጣኝ ዋጋ በስድስት ከተሞች ለሚገኙ የመሸጫ ሱቆች እየቀረበም ነው። በቀጣይ ደግሞ በሌሎች ከተሞች ለማስፋት ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል።

ፕላስቲኮችን በመሰብሰብ መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ከሚጠቀሱት መካከል በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው  አይቸው፣ ሜሮን እና ጓደኞቹ የሃይላንድ ሪሳይክል (መልሶ መጠቀም) ማኅበር አንዱ ነው። የማኅበሩ አባል የሆነው አይቸው ደባሱ እንደተናገረው ማኅበሩ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በፕላስቲክ መልሶ መጠቀም ዘርፍ ተሰማርቶ በከተማዋ የሚገኙ ሃይላንዶችን ሰብስቦ በመፍጨት ለፋብሪካዎች ያቀርባሉ።

አይቸው አክሎም ቆሻሻን ወደ ሀብት መቀየር ይገባል ሲል ነው የእነሱን ተሞክሮ በማንሳት የተናገረው።  ማሕበራቸው ለ15 ሰዎችም ቋሚ የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። በከተማዋ የሚገኙ ከ1500 በላይ ዜጎች ደግሞ ሃይላንዶችን በመልቀም ያስረክቧቸዋል። ባለፉት ሦስት ዓመታት (ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ) 15 ሚሊዮን 566 ሺህ 625 “የሃይላንድ” ፕላስቲኮችን በመፍጨት ለፋብሪካዎች ማቅረባቸውን አብነት አንስቷል። ማኅበሩ ከባሕር ዳር ባለፈ በተለያዩ ከተሞች ጭምር የሃይላንድ ፕላስቲኮችን እየሰበሰበ በመፍጨት  ወደ አዲስ አበባ እንደሚላኩ ተናግሯል።

አቶ ባይህ ጥናቶችን ዋቢ አድረገው እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ ፕላስቲክን ወደ ሀገር ቤት ከሚያስገቡ ሀገራት መካከል ሁለተኛዋ  ናት። ለዚህም 17 ሚሊዮን ዶላር (ሁለት ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ) ወጪ ታደርጋለች። ይህም የሀገርን ምጣኔ ሀብት እየጎዳ ነው። በተለይም በቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት በመሆን ከቱሪዝሙ የሚገኘውን ገቢ እያሳጣ ነው።

በሌላ በኩል መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሩዋንዳ ቆሻሻን በማስወገድ እና ብክለትን በመከላከል በኩል ከአፍሪካ ካሉ ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ናት። በዘርፉ የተሻለ ሥርዓትም ዘርግታለች። በሠራችው ጠንካራ ተግባርም የቱሪዝም ከተማ ተብላለች።

በሩዋንዳ ያለው ውጤታማ ሥርዓት የማኅበረሰቡ እና የባለሥልጣናት የቅንጅት ሥራ ነው ያሉት አቶ ባይህ አካባቢ ፅዱ እና ምቹ ካልሆነ ቱሪስቶችን መሳብ አይቻልም ይህም ምጣኔ ሀብቱን ይጎዳዋል ብለዋል። ዋነኛ የአካባቢ በካይ የሆነውን የፕላስቲክ ምርት ከመጠቀም መቆጠብ፣ ከተጠቀምን ደግሞ ጤናማ የአወጋገድ ዘዴን መከተል እንደሚገባ አሳስበዋል። በከተሞች በቂ የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎችን ማዘጋጀት፣ ፍብሪካዎችም ከኘላስቲክ ምርት ወደ ሌላ ምርት በመቀየር ኘላስቲክን ሊተኩ የሚችሉ እና በቀላሉ ሊበሰብሱ የሚችሉ የዕቃ መያዣዎችን እንዲያመርቱ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል። ኘላስቲክ ወይም ፌስታል በተገቢው መንገድ ካልተወገደ የገፀ ምድርን ውኃ፣ አፈርን፣ እንስሳትን ጨምሮ በከፋ ሁኔታ ይጎዳል። በሰዎች ጤናም ካንሰርን፣ የሕፃናት እድገትን እና የሥነ ተዋልዶ ሥርዓት መዛባትን ያስከትላሉ።

የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ፣ ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ፣ መልሶ መጠቀም፣ የወጡ ሕጎችን ተግባራዊ ማድረግ ብክለትን ለመከላከል የተቀመጡ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ናቸው።።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here