ለኢትዮጵያ የሺዎች ዘመናት የሀገረ መንግሥት ታሪክ የሃይማኖት ተቋማት ድርሻ የላቀ መሆኑ ተጠቁማል። 3ኛው የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ከሰሞኑ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በዚሁ የሰላም ኮንፈረንስ ሰላምን ለማጽናት በዋናነት የሃይማኖት ተቋማትን ሚና የተመለከቱ ሁለት የመወያያ ጽሑፎች ቀርበዋል። ‘ሰላማዊ ውይይት ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ የሃይማኖት ተቋማት ሚና’ በሚል የቀረበው ጽሑፍ አንደኛው ነበር።
የመወያያ ጽሑፉን ያቀረቡት የአማራ ክልል ፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ደሴ ጥላሁን የኢትዮጵያን የሺህ ዘመናት የሀገረ መንግሥት ታሪክ እና የታላቅነት ዘመን አንስተዋል። በአሁኑ ወቅት የገባንበትን ችግር በመጥቀስም “ከችግሮቻችን ተምረን፣ የረዥም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪካችንን ቀምረን ወደ ታላቅነታችን፣ ወደ ድሮ ጥንተ ስልጣኔ ዘመናችን መመለስ አለብን” ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት ሚና አይተኬ ስለመሆኑ ነው የተናገሩት።
ዶክተር ደሴ በጽሑፋቸው ችግር ገጥሟቸው፣ በዚህም ጉስቁልና የገቡ እና በኋላም ከችግራቸው ተምረው ወደ ኃያልነት የተመለሱ ሀገራትን ተሞክሮ አቅርበዋል። ለዚህ ደግሞ ቻይና ዋና አብነት ነበረች።
በጽሑፉ እንደተመላከተው ቻይናዊያን ከ20 በላይ የርስ በርስ ጦርነት ፈትኗቸዋል። በኋላ ግን ከገጠማቸው ችግር ተምረው አንድነታቸውን አጠናክረው ተአምራዊ ለውጥ ማስመዝገብ ችለዋል። በአሁኑ ወቅትም የዓለማችን 2ኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ሆነዋል።
በተመሳሳይ ናይጄሪያውያን ከገጠማቸው የእርስ በርስ ጦርነት ፈተና የወጡት በሃይማኖት ተቋማት እና በአባቶች ግንባር ቀደም ሚና መሆኑን ነው ያብራሩት።
የሀገራችንን በርካታ ዕሴቶች የጠቀሱት አቅራቢው በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር አንድ ሆነን በመምከር ሰላምን ማጽናት እንደሚገባ አሳስበዋል፤ ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት እና አባቶች ከፍ ያለ ድርሻ አላቸው ነው ያሉት፡፡
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም