ወባ

0
83

የወባ በሽታ  በደረቅ (ሐሩር) እና ሞቃታማ አካባቢዎች የተለመደ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው እ.አ.አ በ2023 በዓለም አቀፍ ደረጃ በ83 ሀገራት 263 ሚሊዮን ሰዎች በወባ በሽታ ሲያዙ 597 ሺህ ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል። አፍሪካ ወባ በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰራጭባት እና ከፍተኛ የሞት መጠን የሚመዘገብባት አህጉር ናት። እ.አ.አ በ 2023 በአፍሪካ 246 ሚሊዮን ሰዎች በወባ ሲታመሙ 569 ሺህ ሰዎች ሞተዋል። 76 በመቶ የሚሆነው ሞት የተመዘገበው  ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ሕጻናት ነው።

ከአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባገኘነው መረጃ መሠረት  ወባ የሚከሰተው በዓይን በማይታይ ፕሮቶዝዋ በሚባል የፕላዝሞዲየም ጥገኛ ተኅዋሲያን ምክንያት  ነው። በጥገኛ ተህዋሲያኑ በተያዘች “አኖፊለስ ሞስኪቶ” በምትባል ሴት የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኝ ንክሻ አማካኝነትም ወደ ሰዎች ይተላለፋል።

አብዛኛውን ጊዜ የወባ ትንኟ የምትነክሰው በምሽት እና ጠዋት ሊነጋ ሲል ነው፡፡ በሽታውን በወባ ከተጠቃ ሰው በመንከስ ወደ ጤነኛ ሰው ታስተላልፋለች፡፡ የተበከለች ትንኝ ስትነከስ ጥገኛ ተውሳክ ወደ ደም ውስጥ ይገባል፣ ወደ ጉበትም ይሄዳል።  በጉበት ውስጥም እንደገና ወደ ደም ከመግባቱ በፊት ለቀናት እስከ ሳምንታት ያድጋል። ይህ ምልክቶች የሚታዩበት እና አስቸኳይ ሕክምና የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው።

በሰዎች ላይ የወባ በሽታን የሚያስከትሉ አምስት የፕላዝሞዲየም ተኅዋሲያን  ዓይነቶች አሉ፤ እነሱም፡- ፕላዝሞዲየም ቫይቫክስ፣  ፕላዝሞዲም ፋልሲፐረም፣ ፕላዝሞዲየም ማላሪዬ፣ ፕላዝሞዲየም ኦቫሊ እና ፕላዝሞዲየም ኖሊስ ይባላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ፕላዝሞዲየም ቫይቫክስ እና ፕላዝሞዲየም ፋልሲፐረም ናቸው፡፡ ቀደም ሲል 70 በመቶ የፋልሲፐረም እና 30 በመቶ የቫይቫክስ ስርጭት የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ስርጭታቸው ተቀራራቢ እየሆኑ እንደሆነ ነው በአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ ባለሙያ (Malaria Officer) አቶ ዘላለም ደሴ የገለጹት፡፡

በፕላዝሞዲየም ፋልሲፐረም ተኅዋስ የተነከሰ ሰው ምልክቶቹን ማሳየት የሚጀምረው ከሰባት እስከ 14 ባሉት ቀናት ነው፡፡ ይህ የወባ ተኅዋስ ከፍተኛ ሕመም እና አለፍ ሲልም ሞት የሚያስከትል ነው፡፡ በፕላዝሞዲየም ቫይቫክስ ተኅዋስ በተያዘች ትንኝ የተነከሰ ሰው ደግሞ ከ12 እስከ 18 ቀን ድረስ ምልክቶቹ ይቆያሉ፡፡

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ የወባ በሽታ ሁሉንም ሰው የሚያጠቃ ሲሆን  በተለይም ጨቅላ ሕጻናትን፣ ነፍሰ ጡሮችን፣ አረጋዊያንን እና በሽታ የመከላከል አቅማቸው የተዳከመ ሰዎች ላይ ሲከሰት ሕመሙ ይበረታል፤ ለሞትም ያበቃል። ሁሉም የወባ ተኅዋሲያን  ተመሳሳይ ምልክቶችን የሚያመጡ እና አፋጣኝ የሕክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ በምልክቶች ብቻ በየትኛው የወባ አይነት እንደተያዙ ማወቅ ስለማይቻል የወባ በሽታን ለማወቅ ምርመራ ማድረግ ግዴታ ነው፡፡

አቶ ዘላለም እንደሚሉት አንድ ሰው የሚከተሉት ምልክቶች ከታዩበት በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ ይኖርበታል፡፡

ትኩሳት (ዋናው ምልክት)፣

ብርድ ብርድ ማለት፣

ራስ ምታት፣

ላብ፣

ማስታወክ፣

ተቅማጥ፣

የሆድ ሕመም

የጡንቻ ወይም የመገጣጠሚያ ሕመም፣

ድካም፣

ፈጣን የሆነ አተነፋፈስ፣

ፈጣን የልብ ምት፣

ሳል እና ጤንነት አለመሰማት ተጠቃሾች ናቸው፤ እንዲሁም በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ የዓይን ቢጫ መሆን እና ራስ መሳትንም እንደሚያስከትል ባለሙያው አስገንዝበዋል፡፡

ፕላዝሞዲየም ቫይቫክስ የተገኘበት አንድ ሰው “ክሎሮኪን” የሚባል የሚዋጥ መድኃኒት ይወስዳል፡፡ ነገር ግን “ፕሪማኪዩን” የሚባል ተጨማሪ መድኃኒትም ለ14 ቀናት ይታዘዝለታል፡፡ ፕላዝሞዲየም ፋልሲፐረም ከሆነ ደግሞ “ኳርተም” የሚባል መድኃኒት እና “ፕሪማኪዩን” የሚባል መድኃኒት ለአንድ ጊዜ ብቻ እደሚሰጠው ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ አንድ ሰው በፋልሲፐረም የወባ ተኅዋስ ከተጠቃ እና በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋም ካልሄደ ወደ ተወሳሰበ የወባ ደረጃ ይሸጋገራል፡፡ በዚህ ጊዜም  በጤና ተቋማት ተኝቶ መታከም ግድ ይለዋል፡፡ መድኃኒቱም በደም ሥር (በመርፌ) የሚሰጥ ይሆናል፡፡

የተወሳሰበ ወባ የሚባለው ብዙ የሰውነት ክፍሎች በተኅዋሱ  ሲጠቁ ነው፡፡ ሰውየው ራሱን ሊስት ይችላል፡፡ በተደጋጋሚ ማስመለስ ይኖረዋል፡፡ ማስመለሱ የሚዋጥ መድኃኒት ቢሰጠውም አይቆምም፡፡ በዚህ ጊዜ ነው በደም ሥር መድኃኒት የሚሰጠው፡፡

የተወሳሰበ የወባ ደረጃ ላይ ከደረሰ ጉበትን ይጎዳል፡፡ ምክንያቱም ወባ ቀይ የደም ኅዋሳትን የሚያጠቃ በሽታ ነው፡፡  የደም ግፊት ይቀንሳል የስኳር መጠንም ሊወርድ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ በሕክምና ተቋማት ተኝቶ መታከም ግዴታ ይሆናል፡፡  ታዲያ ከዚህ ውስብስብ የወባ በሽታ ውስጥ ላለመግብት ምልክቶቹ ሲታዩ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት መሄድ ግድ ይላል፡፡ አለበለዚያ ሞት ሊከሰት እንደሚችል ነው የጤና ባለሙያው የሚያስጠነቅቁት፡፡

ከሐምሌ 01 ቀን 2016 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ በክልሉ ሁለት ሚሊዮን 78 ሺህ 872 ሰዎች በወባ ተይዘዋል፡፡ 98 ሰዎችም ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡ ይህ አኃዝ ከዚህ ጊዜ ቀደም ካለው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ዘላለም በ2016 ዓ.ም የነበረው አንድ ሚሊዮን 511 ሺህ 906 እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የሟቾች ቁጥር ደግሞ 32 ነበር፡፡  ይህም የወባ ወረርሽ በክልሉ እንዳለ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ የወባ በሽታ ከ2010 ጀምሮ እየጨመረ እንደሚገኝ የጠቆሙት ባለሙያው ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት በክልሉ  ባለው ጦርነት  እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ግብዓቶችን በሚፈለገው ቦታ እና ፍጥነት ለማድረስ ግጭቱ እንቅፋት ሆኗል ነው ያሉት፡፡ ሌላው በየአካባቢው  የሕብረተሰቡ ወባን ለመከላከል የነበረው ተሳታፎ መቀነሱም ተጠቃሽ  ነው፡፡

ቀደም ሲል ሕብረተሰቡ በየመኖሪያ አካባቢው የሚገኝ ተፋሰስን የማፋሰስ ተግባር ያከናውን ነበር፡፡ አሁን ግን ተዳክሟል፡፡ ሌላው ከፌደራል መንግሥት የሚቀርበው የፀረ ወባ ኬሚካል እና የአጎበር ብዛት ከዓመት ዓመት እየቀነሰ መምጣቱ ለወረርሽኙ መስፋፋት እና መጨመር ምክንያት መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የፀረ ወባ  መከላከያ ኬሚካሎች እና አጎበሮች በእርዳታ የሚመጡ መሆናቸው እና አሁን ላይ ብዙዎቹ ለጋሾች እርዳታ  በማቋረጣቸውም በቂ ግብዓት ማቅረብ አልተቻለም፡፡

በኢትዮጵያ 222 ወረዳዎች ከፍተኛ የወባ ስርጭት እንዳለባቸው መረጃዎችን ዋቢ አድርገው ባለሙያው ተናግረዋል፤ ከዚህ ውስጥ 40 ወረዳዎች በአማራ ክልል ሲሆኑ 70 በመቶ የክልሉን የወባ በሽታ ጫና ይወስዳሉ፡፡

በሌሎች ወረዳዎች የወባ በሽታ የለም ማለት እንዳልሆነ የሚናገሩት አቶ ዘላለም  የመከላከል ሥራዎች ተጠናክረው እየተሠሩ ነው ብለዋል። በተለይም የአርብ እጆች የወባ ወረርሽኝን ይገታሉ በሚል  መሪ ሀሳብ ዘወትር አርብ ጧት ጧት የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡ በተመረጡ ቦታዎች ላይ የወባ ምርመራ እና ሕክምና ይሰጣል፡፡ ወባን መከላከል የሚያስችሉ ግብዓቶች እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

የድጋፍ ማስገኛ ሰነድ (ፕሮፖዛል) በማቅረብ (በቂ ባይሆንም) ለእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በማቅረብ መድኃኒቶችን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶችን ማግኝት እንደተቻለ ነው የገለጹት፡፡ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሠራተኞችም በተለያዩ ከፍተኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው ቦታዎች በአካል እና በስልክ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ የሞት እና የሥርጭቱ መጠን ከዚህ በላይ ይሆን እንደነበር ነው አቶ ዘላለም የተናገሩት።

ባለሙያው እንዳሉት ከፍተኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው 26 ወረዳዎች ለሚኖሩ ለ479 ሺህ 192 አባዎራዎች አንድ ሚሊዮን 126 ሺህ 109 አጎበሮች በመሰራጨት ላይ ይገኛሉ፤ (አንድ አጎበርም ለሦስት ዓመት ብቻ ማገልገሉን ልብ ይሏል)፡፡ 204 ሺህ 539 ከረጢት የፀረ ወባ ኬሚካል ሊሠራጪ ታስቧል፡፡ በዚህም በ16 ወረዳዎች ለሚገኙ የ536 ሺህ 601 አባዎራዎች 804 ሺህ 902 ቤቶች ይረጫሉ ተብሎ ዕቅድ ተይዟል፡፡

የክረምቱን ማብቃት ተከትሎ  በሚመጡት ወራት ማለትም መስከረም፣ ጥቅምት፣ ሕዳር እና ታኃሳስ ዋና የወባ መተላለፊያ  ወራት በመሆናቸው ክረምት ላይ እነዚህ ሥራዎች መሠራታቸው በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ይረዳል ነው ያሉት፡፡

በመጨረሻም አቶ ዘላለም ሕብረተሰቡ መንግሥት ከሚሠራቸው ሥራዎች በተጓዳኝ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራዎችን መሥራት እንደሚኖርበት እና በተለይም ውኃ  ያቆሩ ቦታዎችን ማፋሰስ እና ማዳረቅ እንደሚገባ፣ እንዲሁም አጎበርን በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here