ከውጋጅ ኘላስቲክ – የህመም ማስታገሻ

0
46

ተመራማሪዎች ውጋጅ ኘላስቲክን  ወደ ህመም ማስታገሻ “ፖራሲታሞል” መቀየር የሚያስችል ስልት ማግኘታቸውን ሳይንስ ኒውስ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡

በእንግሊዝ የኤደንበርግ ዩንቨርሲቲ ተመራማሪዎች ለውጤት የበቃው የኘላስቲክ  ውጋጅን ወደ “ፓራሲታሞል”  እና “አሲታሚኖፊን” ማስታገሻ የመቀየር ሂደት ነው፡፡ ቀደም ብሎ ከድፍድፍ ነዳጅ ማስታገሻ ይመረት የነበረውን መተካት ብቻ ሳይሆን ውጋጅን ለጠቃሚ ማስታገሻነት መቀየር መቻሉ ስርነቀል ለውጥ  አሰኝቶታል፡፡

ተመራማሪዎቹ በስነህይወታዊ ዘዴ ጉዳት የሌለው  ባክቴሪያን በመጠቀም በኘላስቲክ ጠርሙሶች ውስጥ የሚገኘውን “ቴሬኘታሊክ አሲድ” ወደ ህመም ማስታገሻ “ፓራሲታሞል” የመቀየር ስልትን እውን ለማድረግ ሁለት ተጨማሪ  “ጂን” ዘረመሎችን    ከእንጉዳይ እና ከአፈር ውስጥ ባክቴሪያ  ወደ ሂደቱ አስገብተዋል፡፡

ውጋጅ ኘላስቲክን ወደ ጠቃሚ ውጤት መቀየር መቻሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጋጅን ለማጥፋት፣  ለመቀነስ እና በሌላ በሚበሰብስ ጥሬ እቃ ለመቀየር እየተደረገ ያለውን ጥረት ለውጤት ያበቃል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

እስከአሁን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ውጋጅ ኘላስቲክ የሚያስከትለውን ብክለት ለመቀነስ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ውጋጅን አቅልጦ ወደ ሌላ ምርት መቀየር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ውጋጁ ቅርጹን መቀየሩ እንጂ በአካባቢ ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖን አለመቀረፉን ነው ያረጋገጡት- ተመራማሪዎቹ፡፡

በኤደንበርግ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረው ከኘላስቲክ ውጋጅ “ፓራሲታሞል” ወይም የህመም ማስታገሻ የማምረት ሂደትን የመሩት ኘሮፌሰር እስቴፈን ዋላስ የተመራማሪዎቹ ጥረት እና የተገኘው ውጤት ከነበረው የተለየ አዲስ መሆኑን ነው ያሰመሩበት፡፡

ኘሮፌሰር እስቴፈን ዋላስ እንዳብራሩት አዲሱ  ስነህይወታዊ ዘዴን ከኬሚስትሪ ጋር በማጣመር ከብክለት የፀዳ መድሃኒት የማምረት ስርዓትን ለመገንባት፣ በከባቢ ዓየር ውስጥ የሚለቀቅን ሙቀት አማቂ ጋዝ  ለመቀነስ እና በቅሪት አካል ነዳጅ ላይ ከሚደረገው ጥገኝነት ለመላቀቅ ሁነኛ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here