በተከታታይ ለ10 ዓመታት አንድ ፔርሙስን ለተለያዩ መጠጦች መያዣነት የተገለገለው ታይዋናዊ በዝገት ተመርዞ ህይወቱ ማለፉን ዴይሊ ሜይ ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት ለንባብ አብቅቶታል፡፡
የታይዋን መገናኛ ብዙሃን እንደዘገበው ግለሰቡ ሳምባው በዝገት በመመረዙ በጤና ድርጅት ከተመረመረ ከአንድ ዓመት በኋላ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሶ ለሞት ተዳርጓል፡፡
ግለሰቡን የመረመሩት ሀኪሞች የመመረዙን መንስኤ ለማወቅ የኃላ ታሪኩን በማጠያየቅ ጥረት አድረገዋል፡፡
በዚህም ግለሰቡ ለተከታታይ 10 ዓመታት እለት በእለት በአንደ ፔርሙስ የተለያዩ ሙቅ እና ቀዝቃዛ መጠጦች መያዣ ቁስ አድርጐ መገልገሉን አረጋግጠዋል፡፡
የግለሰቡ ፔርሙስ የላይኛው ሽፋን ጉዳት ያልደረሰበት በመሆኑ ለመጠጥ መያዣነት ከመጠቀም አለመገታቱን ነው የተረዱት ሀኪሞቹ፡፡ ሆኖም የፔርሙስን የውስጠኛውን ክፍል ሲፈትሹ ዝገት መፈጠሩን አስተውለዋል፡፡
ባለሙያዎቹ ታይዋናዊው ፔርሙሱ ዝገትን ከሚቋቋም ቁስ አለመሰራቱን ቢያውቅም ለዓመታት ውስጡን በማጠብ ብቻ ይገለገል እንደበር ነው ከቅድመ ታሪኩ ጠይቀው የተረዱት፡፡ በፔርሙሱ የውስጠኛው ክፍል የተፈጠረው ዝገት እየተጠራቀመ ወደ ፈሳሽ መያዣው ተቀላቅሎ በመግባቱ ጤናው ተስተጓጉሎ ለከፋ ህመም እንደዳረገው ካደረጉት ምርመራ እና ከግለሰቡ ምላሽ አረጋግጠዋል፡፡
ግለሰቡ በደረሰበት ህመም ወደ ህክምና ጣቢያ ዘግይቶ መድረሱን የተረዱት የጤና ባለሙያዎች የደረሰበት የመመረዝ በሽታ የመከላከል ዓቅሙን በእጅጉ እንደጐዳውም ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ በዚሁ መንስኤ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ የግለሰቡ ህይወት ማለፉን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
የጤና ባለሙያዎቹ በሰጡት የጥንቃቄ የምክር ማንኛውም ሰው የሚገለገልባቸውን ሙቅ እና ቀዝቃዛ መጠጥ መያዣዎች ቢቻል ከማይዝግ ቁስ የተሰሩ መሆናቸውን፣ ይህ ካልሆነ አዘውትሮ በተገቢ ሁኔታ ቁሶችን ማጽዳት፣ ደህንነቱን መፈተሽ ግድ መሆኑን ነው በማደማደሚያ ምክረ ሀሳብነት ያሰፈሩት – ተመራማሪዎቹ፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም