በጠላቂ ባለሙያ  የተገኘዉ

0
51

በአሜሪካ ቴክሳስ ውስጥ በሚገኝ “ፖሰምኪንግደም” በተሰኘ ሰው ሰራሽ ኃይቅ ዳር ሲዝናኑ ከነበሩ ሴት ከጣታቸው ሾልኮ የጠፋው  የጋብቻ የአልማዝ ቀለበት ከሶስት ቀናት በኋላ በጠላቂ ባሙያዎች አሰሳ መገኘቱን ከሳምንት በፊት ዩፒአይ ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::

ጃኮሊን ፔጅ የተሰኙት ሴት በፖሎ ፒንቶ ግዛት “ፖሰም ኪንግደም” በተሰኘው ሰውሰራሽ ኃይቅ ዳርቻ ልጃቸው ከሚጫወትበት “የቤዝቦል” ቡድን አባላት ጋር እየተዝናኑ በነበሩበት ወቅት  ነው በቤተሰቡ የዘር ሃረግ 105 ዓመታት ያስቆጠረው ከአልማዝ የተሰራው የጋብቻ ቀለበት ሾልኮ የጠፋባቸው::

“ፖሳም ኪንግደም” ኃይቅ 65 “ማይል” ርዝመት እና በሺህ የሚቆጠር ሄክታር ስፋት  34 ሜትር ጥልቀት  ይዞ የተንጣለለ ነው:: በእዚህ ውስጥ የገባን የጣት ቀለበት ፈልጐ ማግኘት ከሳር ክምር ውስጥ መርፌ የመፈለግ ያክል ቢሆንም ጃኮሊን ፔጅ ግን  በዋዛ አልተዉትም::

የአልማዝ ቀለበቱ አርብ እለት ነው የጠፋው:: በዚሁ እለት እና በማግስቱ ልጃቸው እና ጓደኞቹ ሞክረው አልተሳካላቸውም:: እናም የቀለበቱ ባለቤት ባህር ጠላቂ አሳሽ ባለሙያ ይቀጥራሉ::

ራያን ፒግሞር የተሰኘ ጠላቂ ባለሙያ ተፈልጐም በቀለበቱ እሰሳ ላይ ይሰማራል::  ለሁለት ቀናት ያደረገው ጥረት ያልተሳካላት ራያን ለሦስተኛ ቀን አሰሳውን ይያያዘዋል::

ጠላቂው ባሙያ ራያን ፒግሞር ከነበረው ልምድ በመነሳት ኃይቁ ጥልቅ እና ሰፊ ቢሆንም ፈልጐ እንደሚያገኘው ቃል በገባው መሰረት በኃይቁ የታችኛው ወለል ላይ በመተንፈሻ መሳሪያው የያዘው “ኦክስጂን” እስከሚያቆየው ጊዜ ድረስ ሲያስስ ቆይቶ ወደ ኃይቁ የላይኛው ገጽ ወጥቶ ይታያቸዋል- በጉጉት ለሚጠብቁት ሰዎች::

ራያን በተደጋጋሚ ከጠለቀበት የኃይቁ የታችኛው ወለል ወደ ላይ እየወጣ አለማግኘቱን ሲያሳያቸው እና ለተጨማሪ አሳሳ ሲጠልቅ የተመለከቱ በውጪ በጉጉት የሚጠብቁት በተሰላቹበት ቅፅበት ለሦስተኛ ጊዜ መተንፈሻ መሣሪያውን  “ኦክስጂን” ሞልቶ ይጠልቃል::

በማእበል፣ በቀለበቱ መጠን ማነስ እና በኃይቁ ስፋት እና ጥልቀት የተፈተነው አሳሹ ራያን በሦስተኛው ቀን በእለተ ሰኞ የአልማዝ ቀለበቱን በእጁ እያሳየ ከኃይቁ ውኃ በላይ መታየቱን ድረገጹ አስነብቧል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here