ኔሬሬ ብሔራዊ ፓርክ በታንዛኒያ ደቡብ ምሥራቅ ቀጣና ነው የሚገኘው:: ፓርኩ በአፍሪካ በስፋቱ ቀዳሚ ሲሆን 30,893 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል:: ስፋቱም የአገሪቱን ሦስት ነጥብ ሁለት በመቶ ይሸፍናል::
ፓርኩ በ1982 እ.አ.አ በዓለም ዓቀፉ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና የባህል ድርጅት ቅርስነት ለመመዝገብም በቅቷል:: ስያሜውንም አገሪቱን ከነፃነት በኃላ በመሯት ጁሊዬስ ኔሬሬ መታሰቢያ አድርጐ ነው የተቋቋመው::
የፓርኩ መገኛ ዝቅተኛው 35 ከፍተኛው 1450 ሜትር ከባህር ወለል በላይ ተለክቷል:: የዝናብ መጠኑ በአማካይ ምስራቃዊው ቀጣና 750 ምእራባዊው 1250 ሚሊሜትር ያገኛል::
የዓየር ንብረቱ ዝቅተኛው 21 ከፍተኛው ወይም ሞቃቱ 29 ዲግሪ ሴልሺየስ በአማካይ ተመዝግቧል::
በፓርኩ 2000 የእፅዋት 440 የዓእዋፍ እንዲሁም 60 አጥቢ እንስሳት እንደሚገኙም ድረገፆች አስነብበዋል::
በአካል ግዙፍ ከሆኑት የዱር እንስሳት ዝሆን፣ አንበሳ፣ ኦቦ ሸማኔ፣ ጐሽ፣ ጉማሬ፣ ቀጭኔ፣ የሜዳ አህያ፣ የዱር ውሻ ወ.ዘ.ተ ይገኛሉ::
ኃይቆች እና ወንዞቹም አስፈሪ የዓዞ ዝርያን በጉያቸው ይዘዋል:: በአየር ንብረቱ ከሀምሌ እስከ ጥቅምት ያሉት ደረቅ፤ ዝናብ ያማይበዛባቸው ወራት ናቸው:: በነዚህ ወራት የዱር አራዊቱ ውኃ ለመጠጣት ሲሰባሰቡ በቀላሉ ስለሚታዩ ለጐብኚዎች ተመራጭ ወራት ናቸው::
ከህዳር እስከ ግንቦት ዝናብ የሚበዛበት ወቅት ነው:: በቀጣናው የሚዘዋዋሩ የአእዋፍ ዝርያዎችም በልምላሜው ተስበው እንዳሻቸው የሚርመሰመሱበት ወራት ናቸው::
ፓርኩ የተመሰረተው እና እውቅና ያገኘው በ1982 እ.አ.አ ነው- በበላይነት የሚያስተዳድረውም የአገሪቱ የብሔራዊ ፓርክ ባለስልጣን ነው:: ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ኔሬሬናሽናል ፓርክ፣ ሰንሴት አፍሪካ ሳፊሪ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም