መምህርት ታምራለች ባዬ በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረ ታቦር ከተማ በአቡነ ጎርጎሪዮስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪ ናቸው:: መምህርቷ ሁለተኛ ክፍል ከሚያስተምሯቸው ተማሪዎች መካከል አራት ልጆች የፊደል አጣጣል ክህሎታቸው ዝቅተኛ መሆኑን ተረድተዋል:: የክፍል እና የቤት ሥራ ሰጥተው ሲመለከቱ የሚምታቱባቸው ፊደላት እንዳሉም ነው የተገነዘቡት:: ተማሪዎቹ ሦስት ዓመት ቅድመ መደበኛ እንዲሁም አንደኛ ክፍል የአጻጻፍ ክህሎት ትምህርት ወስደዋል:: ነገር ግን ትምህርቱ በደንብ የጽሕፈት ክህሎታቸውን አላበቃውም:: ይህን ችግር ለመቅረፍ ሳይንሳዊ የምርምር ዘዴ መጠቀም ዋነኛው መፍትሔ መሆኑን መምህርቷ ያውቃሉ:: በመሆኑም ስድስት ወራት የፈጀ ጥናት እና የመፍትሔ ተግባራትን አዘጋጅተው አቀረቡ:: ውጤቱንም በተግባር ሞከሩ፤ አራቱም ተማሪዎች የፊደል አጣጣል ክህሎታቸው ተሻሽሏል::
ተማሪዎቹ ፈ፣ የ፣ ኘ እና ሌሎች ፊደላትን ይሳሳቱ እንደነበር መምህርት ታምራለች በጥናታቸው ለይተዋል:: በተለይ የተወሰነ የቅርጽ ልዩነት ያላቸውን ፊደላት ልጆቹ እንደሚሳሳቱ አረጋግጠዋል:: መሠረታዊ የጽሕፈት መሥመሮችን በሚገባ አለመለየትም ሌላው የልጆቹ ክፍተት ነበር:: ልጆቹ በዚሁ ከቀጠሉ በትምህርታቸው ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው እና የተግባቦት ችግር ሊያመጣባቸው ይችል እንደነበር መምህርቷ አንስተዋል::
መምህርት ታምራለች ችግሩን ከለዩ በኋላ ወደ መፍትሔ ትግበራው ነው ያመሩት:: በዚህም በሳምንት ለሦስት ቀናት ለ20 ደቂቃ ለአራቱ ተማሪዎች ተጨማሪ ክፍለ ጊዜ በመመደብ የፊደል ልየታ ትምህርት መስጠት ጀመሩ:: የፊደሎቹን ቅርጽ እና ድምጸት ማስጠናት፤ የፊደል አጣጣልን ደጋግሞ በመሞከር መፍትሔ ማምጣት ተችሏል::
የመምህርት ታምራለች ጥናት እና የመፍትሔ ትግበራ በጽሑፍ ተሰንዶ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከሰሞኑ ባዘጋጀው የምርምር እና ጥናት ሲምፖዚየም ላይ ቀርቧል:: መምህርት ታምራለች እንደነገሩን መሰል ሲምፖዚየሞች በቀጣይነት ቢዘጋጁ መምህራን ልምድ እና ትምህርት ይቀስማሉ:: የእሳቸውን የጥናት ውጤት እና የመፍትሔ ትግበራ ለሌሎች ትምህርት ቤቶች መሰል ችግሮችን ለመፍታት ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችልም ገልጸዋል:: በእለቱ ከቀረቡት ሥራዎችም አንደኛ ወጥቷል::
መምህር አቤሜሌክ ሞገስ የተማሪዎች ሥነ ምግባር ለትምህርት ጥራት ባለው አበርክቶ ላይ ጥናት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። መምህራን በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ ተግባራዊ ጥናት እና ምርምር ማድረጋቸው የትምህርት ችግሮችን ለይቶ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ሁነኛ መንገድ መሆኑን ነው መምህር አቤሜሌክ የገለጹት። ጥናት እና ምርምሩ የተደበቁ ችግሮችን በማውጣት፣ ለፖሊሲ አውጭዎች በማመላከት እና ሥነ ምግባር የተላበሰ ትውልድ በመቅረጽ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ሌላዋ ጥናት አቅራቢ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በደንቢያ ወረዳ በመምህርነት ሙያ እያገለገሉ ያሉት መምህርት ሙሉወርቅ ሲሳይ ናቸው:: ጥናት በትምህርት ቤቶች ላይ መሠራት ያለበት ትልቅ ተግባር መሆኑን አንስተዋል። ለዚህም በትምህርት ሥራ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መምህራን በየደረጃው ከሚገኙ መሪዎች ጋር ተቀናጅተው ችግር ከሚፈቱበት መንገድ አንዱ መሆኑንም ገልጸዋል።
መምህርት ሙሉወርቅ “መምህራን የተግባር ላይ ጥናት እና ምርምር ማድረጋቸው ሥርዓተ ትምህርቱን ከላይ ያሉ አካላት በመሰላቸው መንገድ ከሚያዘጋጁት በተግባር ላይ ከሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች ግብዓት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል:: ሴቶች በጥናታዊ ዘዴም ሆነ በሌሎች ሥራዎች ላይ መሳተፋቸውም ሊበረታቱ ይገባል”በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል::
መምህር ያሬድ አስናቀው በደሴ ከተማ ሆጤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር ናቸው:: እሳቸውም በ12ኛ ክፍል ተማሪዎቻቸው ላይ የተቀናጀ እና የተደራጀ ጽሑፍ የመጻፍ ክህሎት ማነስ እና ፍላጎት ማጣት በማስተዋላቸው ጥናቱን ለመሥራት ተነሳስተዋል:: በዚህም ልጆቹ ፍሰቱ የተስተካከለ፣ የሰዋሰው ሕግን የጠበቀ እና ሳቢ ጽሑፍ እንዲጽፉ ተግባራዊ መፍትሔዎችን አስቀምጠዋል:: በዚህም ተማሪዎቻቸው የመጻፍ ክህሎታቸው እንዳደገ ገልጸዋል:: ይህን ጥናታቸውንም ሲምፖዚየሙ ላይ አቅርበዋል::
ሲምፖዚየሙን በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እየሩስ መንግሥቱ ጥናት እና ምርምር ለትምህርት ተቋም ያለውን ከፍተኛ ጠቀሜታ ገልጸዋል። ሕይወትን ለማቅለል ጥናት፣ ምርምር እና ፈጠራ ወሳኝ መሆኑንም ምክትል ኃላፊዋ ጠቁመዋል:: አጥኚ እና ተመራማሪዎችንም ማበረታታት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል። ትምህርት ቢሮውም ለጥናት እና ምርምር ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱን የጠቆሙት ምክትል ኃላፊዋ፤ በትምህርት ሥርዓቱ ጥናት እና ምርምር ማድረግ የተለመደ ቢሆንም የዘንድሮው ልዩ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሲምፖዚየሙ በአዲስ የተጀመረውን ሥርዓተ ትምህርት መማር ማስተማሩን ውጤታማ ለማድረግ፣ በክልሉ በተፈጠሩ ችግሮች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው የቆዩ ተማሪዎችን ለማስተማር ስለሚያስፈልገው ዝግጅት፣ ጥናት እና ምርምሮች ተስፋፍተው ወደ ተግባር እንዲገባባቸው ተሞክሮ ለመለዋወጥ አስቻይ መሆኑን ገልጸዋል።
ከአብዛኞቹ ዞኖች ጥናት እና ምርምሮች መቅረባቸውን ያነሱት ወይዘሮ እየሩስ አጥኚዎች እና ተመራማሪዎች ለቀጣይ ዓመታትም ትምህርት የሚወስዱበት እና የሚበረታቱበት መሆኑንም ጠቁመዋል። ሲምፖዚየሙን በማዘጋጀት አስተዋጽኦ ያበረከቱትንም አመስግነዋል።
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ምዘና እና ጥናት ቡድን መሪ ዝጋለ ማሩ በሲምፖዚየሙ ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ እየተጣሩ ክልል ላይ ከደረሱ 72 ጥናቶች ውስጥ 24ቱ ለውድድር እንደቀረቡ ገልጸዋል። በውድድሩ የተመረጡት ሦስት የተግባር እና ሦስት መሠረታዊ ጥናቶችን ያቀረቡ ተሸልመዋል:: ለሁሉም የጥናት እና ምርምር ተሳታፊዎች ደግሞ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
የሁሉም ጥናቶች መዳረሻ የተማሪዎች ሥነ ምግባር እና ውጤትን ለማሻሻል መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዝጋለ መምህራን ለችግሮች መፍትሔ በማፈላለግ ወደ ውጤት መቀየር ዋናው ዓላማ መሆኑንም ገልጸዋል። የተመረጡ ጥናቶች ታትመው ለትምህርት ተቋማት እንደሚደርሱም ገልጸዋል።
በሲምፖዚየሙ ተገኝተው የማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የአብክመ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) የትምህርት ሥርዓታችን መዛነፍ፣ በሁሉም ማኅበራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ገፆቻችን ችግሮች እንዲፈጠሩ አድርጓል ብለዋል። “ሀገራችን ኢትዮጵያ በትምህርቱ ዓለም በጀግኖች አባቶቻችን ቀድማ ሥልጣኔን የጀመረች ናት፤ ይሁን እንጅ ከኋላዋ የተነሱ በርካታ ሀገራት በእድገታቸው መገስገስ የቻሉት የትምህርት ሥርዓታቸው በኢኮኖሚ ሥርዓት የተቃኘ በመሆኑ ነው፤ ጥራት ያለው ትምህርት ለዜጎች ማዳረስ ጥራት ያለው ሰብዓዊ ሀብትን መገንባት ያስችላል” ብለዋል።
“በየትኛውም የዓለም ክፍል ችግሮች ይፈጠራሉ፤ ጦርነቶችም አሉ፣ ይሁን እንጅ ችግሮቻችንን የምንፈታበት መንገድ አሁን ቆመን ለምንገኝበት ሁናቴ ምስክር ነው:: የትምህርት ሥራ በጦርነት ሒደት ሊታወክ አይገባም:: በክልላችን በተፈጠረ የፀጥታ ችግር በርካታ የትምህርት ተቋማት ተዘግተዋል፤ ከአራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ቀርተዋል፤ ይህም የሆነው በራሱ ልጆች ነውና ትምህርት በጦርነት ምክንያት መቋረጥ የለበትም፤ ልጆቻችንን ወደ ትምህርት ገበታቸው ልንመልሳቸው ይገባል!” በማለት አስገንዝበዋል::
ምርምር ለትምህርት ጥራት ዓይነተኛ መፍትሔ እንደሆነ የገለጹት ቢሮ ኃላፊዋ ይህን ለማድረግም መማር ማስተማሩ በጥናት እና ምርምሮች መደገፍ ስለሚገባው በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል:: በዚህ ዓመት የተካሔደው የጥናትና ምርምር አውደ ርዕይ በትምህርት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚቀርፍ፣ ሥርዓተ ትምህርቱን የሚደግፍ እንደነበር አስረድተዋል::
የአማራ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ታጀበ አቻምየለህ በበኩላቸው ጥናት እና ምርምሮችን መሥራትና ለችግሮቻችን ቁልፍ መፍትሔ የሚሆኑ ሒደቶችን ማስቀመጥ ከመማር ማስተማር ሥራችን በተጓዳኝ የተሰጠ ተግባር ነው ብለዋል:: መምህራን አሁን የገጠመንን ችግር ጨምሮ በርካታ የትምህርት ሥራዎችን ለሚያስተጓጉሉ ችግሮች መፍትሔ የሚሆኑ ጥናት እና ምርምሮችን በክልል ደረጃ ማቅረባቸው በጣም የሚበረታታና ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ ሥራ እንደሆነ ገልጸዋል። የተሠሩት ጥናት እና ምርምሮች ለጥናት አውደርዕይ መቅረባቸው ብቻውን በቂ አይደለም ያሉት አቶ ታጀበ፤ ምርምሮቹ ከየመጡበት የትምህርት ተቋም አንፃር በቀጥታ ወደ ተግባር ተለውጠው የመማር ማስተማሩን ሊደግፉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል::
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም