የማህበራዊ ሚዲያ ሚሊየነሮች ሚስጥር

0
68

ዩቱዩብ፣ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ኤክስ/ትዊተር፣ ስናፕቻት፣ ቲክቶክ፣ ትዊች፣ ኪክ እና ፒንተረስት ገንዘብ መስራት የሚያስችሉ የማህበራዊ ሚዲያ   መድረኮች ናቸው፡፡

ይህ ዘመን ከመቼውም በላይ ገንዘብ በማህበራዊ ሚዲያ የመስሪያ አማራጮች የበዙበት ነው፡፡ ብዙ የተደበቁ እውቀቶች፣ እድሎች፣ ሐሳቦች፣ ሀብቶች፣ ችሎታዎች ወደ ሕዝብ እየተዳረሱ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ እና ማህበራዊ ሚዲያ ተደምረው ገንዘብ መስራትን ቀላል አድርገውታል፡፡ በትንሽ በጀት፣ በጠባብ ቦታ፣ በአጭር ጊዜ እና አነስተኛ ጉልበት ሚሊዮን ዶላሮችን መስራት ዘመኑ የሰጠን ጸጋ ነው፡፡ የዓለም ሕዝብ  በኢንተርኔት ተሳስሯል። ያ መተሳሰር ደግሞ ገበያ ነው። ስራ ነው። ገንዘብ ነው።

በማህበራዊ ሚዲያ የይዘት ፈጣሪ ለመሆን ሲታሰብ ዋናው ጥያቄ በፈጠራ ችሎታየ ገቢ ማግኘት እችላለሁ  ወይ የሚለው ሳይሆን እንዴት የሚለው ነው።  ገንዘብ መስራት ተመልሶ ያደረ ጥያቄ ነውና፡፡ ፈጠራ እና ችሎታ ዋጋ የሚያወጣበት ዘመን ነው።

በተለይም ለቪዲዮ ይዘት ፈጣሪዎች እንደ ዩቲዩብ፣ ቲክቶክ እና ኢንስታግራም ያሉ መድረኮች ይዘትን ወደ ከፍተኛ ገቢ ለመቀየር በርካታ መንገዶችን አቅርበዋል፡፡ እነዚህን መድረኮች ብዙዎች ኢኒቨስትመንት አድርገዋቸዋል፡፡

አንድም ነገር ያለ ጉዳት አንድም ነገር ያለ ጥቅም አልተሰጠንም። ጎበዞች ይጠቀሙበታል። ደካሞች መጠቀሚያ ይሆናሉ። ዛሬ የጎበዞችን ታሪክ ነው የምነግራችሁ።

ሚስተር  ቢስት በመባል የሚታወቀው የዓለም ቁጥር አንድ ዩቱዩበር መደበኛ ስሙ ጂሚ ዶናልድሰን ነው፡፡

አሜሪካዊው ሚስተር ቢስት ዩቲዩበር፣ ስራ ፈጣሪ እና በጎ አድራጊ ነው። በዓለም ላይ ካሉ በጣም ስኬታማ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ የይዘት ፈጣሪዎች አንዱ ነው፡፡ በዩቲዩብ መድረክ  ከፍተኛ ተመዝጋቢ (ሰብስክራይበር) ያለው እሱ ነው።

ሚስተር ቢስት እውቅናው ዩቱዩብን ከስራነት ባሻገር ግዙፍ ኢንቨስትመንት በማድረጉ ነው፡፡ ውድ እና ግዙፍ የሆኑ ትርኢቶችን፣ አስገራሚ ፈተናዎችን  ሚሊዮን ዶላሮች በማውጣት ያዘጋጃል፡፡ ውድድሮችን አዘጋጅቶ ሰዎችን ይሸልማል፡፡ ሰፊ የበጎ አድራጎት ስራዎችን በሚያቀርብበት የዩቲዩብ ቪዲዮ ዘውግ ፈር ቀዳጅ ሆኗል። የማይደፈሩ ጨዋታዎች እና ለማሸነፍ ትንቅንቅ የሚደረግባቸውን ይዘቶች ያዘጋጃል፡፡

456 ሺህ ዶላር የሚሸልምበትን ጨዋታዎች አዘጋጅቷል፡፡ በዚህም ሳይገደብ እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚያስገኙ ሌሎች ውድድሮችን በቪዲዮ በማዘጋጀት ለተመልካቾች አሳይቷል፡፡

ሚስተር ቢስት ዩቲዩብን የጀመረው እ.አ.አ በ2012 በ13 ዓመቱ ነበር፡፡ የጌም ቪዲዮዎች እና አስተያየቶች በመስጠት የተለመዱ ቪዲዮዎችን ይሰራ ነበር።

በማህበራዊ ሚዲያ ትልቁ ነጥብ ትኩረት ውስጥ መግባት ነው፡፡ እ.አ.አ በ2017 ሚስተር ቢስት ከዜሮ ጀምሮ እስከ መቶ ሺህ ድረስ ሲቆጥር የሚያሳይ ቪዲዮ ሰርቶ ዓለምን አነጋገረ፡፡ ይህ ትርጉም የለሽ የሚመስል ዓይን ውስጥ የመግባት ሙከራ ከ40 ሰዓታት በላይ ፈጅቶበታል። ይህ ቪዲዮ ቁርጠኝነቱን እና የፈጠራ ሀሳቦችን አረዳድ አሳይቷል።

ከዚህ ቪዲዮ በኋላ ብዙ ሚሊዮን ዶላር ከብራንድ ድርጅቶች ስምምነት አገኘ። ገንዘቡን ለራሱ ከማድረግ ይልቅ ሁሉንም ገንዘብ ለቤት አልባ ሰው ሲሰጥ የሚያሳይ ቪዲዮ ሰራ። አሁንም የሰው ትኩረት ውስጥ ገባ፡፡

በቪዲዮ ኢንቨስት ያደርጋል፡፡ ገንዘብ ያገኛል፡፡ ያንን ገንዘብ በሙሉ ይበልጥ ትልቅ እና ውድ ቪዲዮ ለመስራት መልሶ ኢንቨስት ያደርገዋል። ያ ትልቅ  ቪዲዮ ብዙ እይታ ያገኛል፡፡ ይህም የበለጠ ገንዘብ ያስገኛል።

ይህንን ሂደት ነው የሚደጋግመው፡፡ መስራት፡ ገንዘብ ማግኘት፡፡ የተሻለ ገንዘብ ለማግኘት መልሶ ኢንቨስት ያደርጋል፡፡ ይህ ስትራቴጂ ከፍተኛ እድገት አስገኝቶለታል። በህዳር ወር እ.አ.አ 2022 ሁሉንም ዩቱዩበር  በመብለጥ በዩቱዩብ ላይ ከፍተኛ ተመዝጋቢ ያለው ግለሰብ ለመሆን በቃ፡፡ ዛሬም ድረስ በዚያው ቦታው እና ዝናው አለ፡፡

በአሁኑ ጊዜ 409 ሚሊዮን ተከታዮች አሉት፡፡ 880 ቪዲዮዎችን ሰርቷል፡፡ በዩቲዩብ ላይ ያለውን ጨዋታ ሙሉ በሙሉ የቀየረ የሚዲያ ግዙፍ ሰው ነው። አዎንታዊ ስራዎችን ይሰራል፡፡ ከፍተኛ ሽልማት ያለው እና የበጎ አድራጎት ስራዎችን ያካተተ አዲስ የይዘት ዘውግ ፈጥሯል። ስኬታማ ነጋዴ እና በጎ አድራጊም ነው።

የ27 ዓመቱ ወጣት ስራ ፈጣሪ በግንቦት ወር  1998 በፈረንጆች አቆጣጠር ነው የተወለደው፡፡ ሰለብሪቲ ኔትወርዝ ድረ ገጽ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሀብት አለው ይላል፡፡

ወደ ቲኪቶክ መንደር ጎራ ብለን ደግሞ ካቤ ላሜን እንመልከት፡፡ የሴኔጋሉ ተወላጅ ጣሊያናዊ የ25 ዓመት ወጣት የማህበራዊ ሚዲያ ታዋቂ ሰው ነው፡፡ በቲክቶክ ላይ በዓለም ላይ ከፍተኛ ተከታይ ያለው የቲክቶክ ንጉሥ  በመባል ይታወቃል።

ካቤ ላሜ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ከፋብሪካ ስራው መባረሩን ወደ ቲክቶክ ግዛት በመቀየር በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝናን ያተረፈ ሰው ነው። እሱ በይበልጥ የሚታወቀው የተለየ የህይወት ጠቀሜታ በሌላቸው ቪዲዮዎች ላይ በዝምታ በሚሰጣቸው ምላሾች ነው፡፡ ስራዎቹ ቀላል፣ ከብዙ ሰው ጋር የሚገናኙ እና በጣም አስቂኝና ውጤታማ ናቸው። ዝምተኛው ኮሜዲያን ሲሉም ይጠሩታል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከ162 ሚሊዮን በላይ የቲክቶክ ተከታዮችን በማፍራት የመድረኩ ከፍተኛ ተከታይ ያለው የይዘት ፈጣሪ ነው። አያወራም፡፡ አይጽፍም፡፡ ድርጊት ብቻ። በሰዎች ቪዲዮ ይገረማል፡፡ አንዳንድ ነገሮችን ሲያስተካክል ወይም ሲሰራ በዝምታ ይታያል፡፡

ምንም ቋንቋ አለመጠቀሙ ዓለም አቀፍ እውቅና እና አትራፊ የብራንድ ስምምነቶችን አስገኝቶለታል። ብዙዎች ዘንድ የመታየት እድል ፈጥሮለታል፡፡ ቪዲዮዎች በጣም ቀላል ናቸው፡፡ ይህም ለስኬቱ ቁልፍ ሚስጥር ነው።

አንድም ቃል አይናገርም። በቀላሉ ወደ ካሜራው ትርጉም በሌለው እና በተሰላቸ አይነት ስሜት ይመለከትና የእሱን ድርጊት በእጅ ምልክት ያሳያል። ይህም በሁለት እጆቹ ወደ ቀላሉ መፍትሄው ማመላከት ነው፡፡

የካቤ ላሜ ታሪክ ከችግር ወደ ስኬት የተደረገ ጉዞ  ነው፡፡ በመጋቢት 2020 እ.አ.አ በጣሊያን በኮሮና ወረርሽን ሲከሰት ከሚሰራበት ፋብሪካ ተባረረ፡፡ በድብርት እና በመሰልቸት ስሜት ከመኝታ ክፍሉ ሆኖ ቪዲዮዎችን በቲክቶክ ላይ መለጠፍ ጀመረ። መጀመሪያ ላይ እንደ ጭፈራ ያሉ የተለመዱ የቲክቶክ ቪዲዮዎችን ይለጥፍ ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙም ተቀባይነት አላገኘም። ብዙም ሳይቆይ  ቀላል ቪዲዮዎችን “ዱዩት” እና “ስቲች” በማድረግ የራሱን ልዩ ስልት አገኘ። ይህ አይነቱ አቀራረብ ወዲያውኑ ተወዳጅነትን አገኘ።

ቃላት የሌላቸው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀላሉ የሚገቡ ምላሾቹ፣ የቋንቋ እና የባህል እንቅፋቶችን በመስበር ይዘቶቹ ለዓለም አቀፍ ተመልካች ተዳረሱለት።

የተከታዮቹ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት አደገ። በሰኔ 2022 እ.አ.አ ቻርሊ ዳሚሊዮን በመብለጥ በመድረኩ ላይ ከፍተኛ ተከታይ ያለው ቲክቶከር ለመሆን በቃ፡፡ ይህንንም ቦታ እስካሁን ይዞ ይገኛል።

ለከፍተኛ ተወዳጅነቱ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ለሁሉም የሚገባ ቀልድ ማቅረቡ አንደኛው ምክንያት ነው፡፡ ስለማይናገር ቀልዱ ትርጉም አያስፈልገውም። በማንኛውም የዓለም ክፍል ያለ ማንኛውም ሰው ቀልዱን ሊረዳው ይችላል።

ቀላልነት እና እውነተኛነት ሁለተኛው ምክንያት ነው፡፡ በከፍተኛ ደረጃ በተቀነባበሩ ጭፈራዎች፣ ትሬንዶች (ሰሞንኛ ቪዲዮዎች) እና ፈተናዎች በተሞላ መድረክ ላይ የካቤ ቀላል እና ብዙ ልፋት የሌለበት ስልት እንደ አዲስ ነገር ይታያል። እውነተኛ እና ተግባቢ ሆኖ ይሰማል።

ካቤ በመጋቢት ወር 2000 እ.አ.አ በሴኔጋል ነው የተወለደ። አንድ ዓመት ሲሆነው ከቤተሰቡ ጋር ወደ ጣሊያን ተሰደደ። ከ162 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉት የቲክቶክ ንጉሥ ሆኗል። ከብዙ ሚሊዮን ሰዎች ጋር ለመገናኘት ትልቅ በጀትም ሆነ ድምጽ እንደማያስፈልግ ካቤ አረጋግጧል።

በአሁኑ ጊዜ ቅንጡ እና ዝነኛ  ምርቶችን በማስተዋወቅ ሚሊዮን ዶላሮችን የሚቀበል ሰው ነው። ባለሀብት ነው። ከሁሉም የዓለም ማዕዘናት የሚመጡ የብራንድ ምርቶችን ያስተዋውቃል።  በዝነኞች ዝግጅት ለመታደም ብቻ ብዙ ሚሊዮን ዶላሮች ይከፈሉታል።

ካቢ ሌሜ ለአንድ የቲክቶክ ፖስት እስከ 750 ሺሕ  ዶላር  ለአንድ የማስታወቂያ ቪዲዮ ብቻ ማስከፈል የጀመረው ገና ዝናው በጀመረበት እ.አ.አ በ2022 ነበር። በዚሁ ዓመት ብቻ  10 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል። ካቤ ከቲክቶክ ባሻገር በሪል እስቴት፣ በሬስቶራንት እና በሶፍትዌር ኩባንያዎች ላይ እያለማ  ነው።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የካቢ ላሜ የተጣራ ሀብት በግልጽ ጨምሯል። ፎርብስ መጽሔት “የዲጂታል ሚዲያው ቻርሊ ቻፕሊን” ብሎ የጠራው ካቤ ከፍተኛ ተከታይ ያለው የቲክቶክ ስሙን ከማስጠበቅ በተጨማሪ ከፎርትናይት እና ሶኒ ፒክቸርስ  ጋር አትራፊ የብራንድ ስምምነቶችን ማድረጉን ገልጿል።

በቅርቡ ቦስ የተሰኘው ኩባንያ በሚላን የፋሽን ሳምንት ዝግጅታቸው ላይ ለመራመድ እና ተያያዥ የቲክቶክ ፖስት ለመስራት ለካቤ ላሜ  450 ሺህ  ዶላር ከፍሎታል። ለፎርብስ መጽሔት “ህልሜ ወደ አሜሪካ ተዛውሬ በፊልሞች ላይ መተወን ነው” ሲል ተናግሯል።

“ህልሜ ኮሜዲ ተዋናይ መሆን፣ ከአርዓያዬ ዊል ስሚዝ ጋር ፊልም መስራት ነው። ከዚያም ማን ያውቃል፣ ምናልባት ኦስካርም ላሸንፍ እችላለሁ!” ሲልም አክሏል።

ለዛሬ  ሚስተርቢስትን እና ካቤ ላሜን ከዩቱዩብ እና ቲክቶክ መንደሮች በማሳያነት አነሳን እንጂ በዓለም ዙሪያ ያሉ ወጣቶች ማህበራዊ ሚዲያን የሚሊዮን ዶላሮች መስሪያ አድርገውታል። ዘርፉም ቢሊዮን ዶላሮች የሚታፈሱበት ነው። ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ምርቶች ማስታዎቂያዎችን በማህበራዊ ሚዲያ ማስተዋወቅን የመረጡበት ጊዜ ነው።

በሀገራችንም በዚህ ዘርፍ ብዙ ብር የሚሰሩ እና ትውልድን የሚለውጡ ሰዎች አሉ። ማህበራዊ ሚዲያ ገና ያልተጠቀምንበት የገንዘብ መስሪያ አማራጭ ነው። ቴክኖሎጂ ነውና ይህን ዘርፍ መቀላቀል እውቀትና ክህሎትን ይጠይቃል። ማህበራዊ ሚዲያ ማንም ሰው አምኖ ያልሰጣቸውን እድል ለብዙዎች ሰጥቷል። ያላሳፈሩት ብዙዎች ራሳቸውን እና ሀገራቸውን እየለወጡ ነው። ጉዞውን መቀላቀል ከኢትዮጵያዊያን ወጣቶች የሚጠበቅ ነው።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here