ጦርነት አሸናፊውንም ሆነ ተሸናፊውን ወገን ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም፡፡ ማንኛውም ጦርነት ወይም ግጭት ውድ የሆነውን የሰውን ልጅ ሕይዎት ከመቅጠፉ ባለፈ የሚያደርሰው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ሀገራቱን ወደ ድህነት ቁልቁል ይመራል፡፡
በዓለማችን ትልቁ ኪሳራን ያስከተለው ጦርነት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲሆን በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ እና ሰፊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ይህም ከፍተኛ ውድመትን እና የኢኮኖሚ መዋዠቅን አስከትሏል። ሦስት ዓመታትን የተሻገረው የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነትም ሆነ ሌሎች የንግድ ጦርነቶች እና ግጭቶች ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ መዘዝ ቢያስከትሉም የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያስከተለው ውድመት ግን ወደር አልነበረውም።
እንዲሁም ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች በመኖራቸው በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሚካሄዱ ጦርነቶች ይበልጥ አውዳሚ ከመሆናቸውም በላይ እጅግ ውድ ዋጋ የሚያስከፍሉ ሆነዋል። ኢራንና እስራኤልም በቀላሉ የማይተገበር የሚመስለውን የተኩስ አቁም ካደረጉ በኋላ ሁለቱም ሀገራት አሁን ላይ የደረሰባቸውን በቢሊዮን ዶላር የተሸጋገረውን ኪሳራ እየቆጠሩ ነው።
የ12 ቀናቱ ጦርነት በኢራንም ሆነ በእስራኤል ላይ ከባድ የኢኮኖሚ ጉዳት እንዳደረሰ ግልጽ ነው። ከዓመታት የማዕቀብ ቅጣቶች ጋር እየታገለ ያለው የኢራን ኢኮኖሚ ለኑክሌር ፕሮግራሟ መሰናክል እና በነዳጅ ምርቷ ላይ እንቅፋት ሆኖባታል።
ታዲያ እስራኤል አሁን ላይ እስከ ዛሬ ከተሞከሩ የመልሶ ግንባታ ዘዴዎች ሁሉ እጅግ ውድ የሆነ እርምጃ በመውሰድ ላይ ትገኛለች፡፡ ጦርነቱ ካደረሰው የገንዘብ ተፅዕኖ ባሻገር የጂኦፖለቲካዊ (ቀጣናዊ) ትብብርንና የአካባቢ ደኅንነት ሁኔታ ለውጧል።
ሀገራቱ አንዱ ሌላኛውን ለማጥቃት የሚልኳቸው ሚሳኤሎች መብረራቸዉን አቁመው ሊሆን ቢችልም ጦርነቱ ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለበርካታ ዓመታት ይቀጥላል፤ ይህም በበጀት፣ በፖሊሲ እና ምናልባትም በምዕራብ እስያ ያለውን የሥልጣን ሚዛን ይቀይራል።
ቲ አር ቲ ወርልድ እንደዘገበው ኢራን በጦርነቱ ሳቢያ ከስድስት እስከ ዘጠኝ በመቶ ያህሉን ምጣኔ ሀብቷን አጥታለች። በተጨማሪም የአሜሪካ እና የእስራኤል ጥቃት በኢራን የኑክሌር ተቋማት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። ሙሉ በሙሉ ለማገገምም የተወሰነ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። የኢራን የነዳጅ ምርትም በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎቿ ላይ በደረሰው ጥቃት በነዳጅ ምርት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያደርሳል፡፡ በመሆኑም የሀገሪቱን ዕድገት ይበልጥ ሊያዳክመው ይችላል።
ታይምስ ናው ኒውስ (timesnownews.com) እንደዘገበው ኢራን ከእስራኤል ጋር ባደረገችው የ12 ቀናት ጦርነት ወደ ውጭ የሚላከው የነዳጅ ምርት በ94 በመቶ በመቀነሱ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሶባታል። አራት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት 591 ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን የተኮሰች ሲሆን የእስራኤል ጥቃት ግን የኑክሌር ተቋማቷን በመጉዳት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕንፃዎቿን አወድሟል። የኢራን ፓርላማ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አባል የሆኑት ሁሴን ሳምሳሚ እንዳሉት “የተኩስ አቁምን የምንቀበልበት ምክንያት ከጠላት ጋር ሲወዳደር ወታደራዊ ድክመታችን ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያችን ወሳኙን ጦርነት የመቋቋም አቅም ስለሌለው ነው” ብለዋል።
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ኢራን በየቀኑ ወደ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ዘይት ወደ ውጭ ትልክ ነበር፡፡ በአብዛኛው መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለቻይና በቅናሽ ዋጋ ትሸጣለች። የእስራኤል የአየር ድብደባ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ግን ወደ ውጭ የሚላከው ምርት በቀን ወደ 102 ሺህ በርሜል ወርዷል።
ኢራን በግጭቱ ወቅት በግምት 591 የሚገመቱ የባላስቲክ ሚሳኤሎች እና ከ100 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በእስራኤል እና በኳታር ላይ ለጥቃት አሰማርታለች። ኢራን በጣም ርካሽ ሚሳኤሎችን ለመተኮስ እያንዳንዳቸው 250 ሺህ ዶላር ዋጋ አስወጥተዋታል፡፡ በጣም ውድ የሆኑት ሖራምሻህር የተባሉ ሚሳኤሎች ደግሞ ወደ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎባቸዋል።
ኢራን በወታደራዊ ሃብትም ሆነ በኢኮኖሚ ከፍተኛ ችግር እንደገጠማት ነው አሁን ላይ እተደረገ ያለው የኢኮኖሚ ግምገማ የሚያመላክተው። ለዓመታት በምዕራባውያን ማዕቀብ ቅጣቶችን የተሸከመችው ሀገር በ12 ቀናቱ ጦርነት ምክንያት ተጨማሪ መከራዎች ደርሰውባታል፤ ይህም የኢኮኖሚ ዕድገቷን ያደናቅፋል። በሦስቱም የኑክሌር ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱ ለሀገሪቷ ትልቅ መሰናክል ነው። በኢራን 12 ሳይንቲስቶችንና 20 ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ጨምሮ ከ620 የሚበልጡ ግለሰቦች ሲሞቱ ሌሎች ከአራት ሺህ 870 የሚበልጡ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ነው ኒውስ 24 ኦንላይን (news24online.com) ላይ ያገኘነው መረጃ የሚያትተው፡፡
በለንደን የኪንግ ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር እና የሜና አናሊቲካ ዳይሬክተር የሆኑት አንድሪያስ ክሪይ ከቲ አርቲ ግሎባል ጋር ባደረጉት ቃለ -ምልልስ የኢራን አጠቃላይ ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ የፋይናንስ ኪሳራው ከ24 ቢሊዮን ዶላር እስከ 35 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ገምተዋል። ይህም ከስድስት ነጥብ ሦስት በመቶ እስከ ዘጠኝ ነጥብ ሁለት በመቶ የሚሆነው የኢራን የ380 ቢሊዮን ዶላር ምጣኔ ሀብት ነው። በተጨማሪም አሜሪካ እና እስራኤል ያደረሱባት ጥቃት የኢራንን የኑክሌር መሠረተ ልማት ያበላሸ ከመሆኑም በላይ የቴህራን የነዳጅ ምርት በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል።
ከቲ አር ቲ ግሎባል የተገኙ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት በኃይል ማመንጫ እና በወታደራዊ ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት የኢራንን መዋቅራዊ አደጋ በማባባስ ከግጭቱ በኋላ ያለውን የማገገም አደጋን ያስከትላል።
የእስራኤል ጥቃቶች ወታደራዊ ተቋማትን፣ አየር ማረፊያዎችን፣ የትዕዛዝ ማዕከሎችን እና እንደ ማጣሪያ ፋብሪካዎች ያሉ የሲቪል መሠረተ ልማቶችን ጨምሮ ወሳኝ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ። የቴህራን መንግሥት እንዳስታወቀው በዋና ከተማዋ ብቻ 120 የመኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡ ከ500 በላይ ክፍሎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከጦርነቱ በፊትም ቢሆን ኢራን ከ500 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት የሚፈልግ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ችግር ነበረባት። ጥቃቶቹ ታዲያ ይህንን ሁኔታ አባብሰውታል፡፡
ስታቲስታ የዳታ ትንታኔ ድርጅት እንዳሳወቀው በጦርነቱ ወቅት ለአንድ ሳምንት የዘለቀው የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ብቻ ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ አድርሷል።
“በሳይበር አታክ” ጠላፊዎች የኢራንን ትልቁን ዲጂታል ምንዛሪ ኖቢቴክስ በመምታት ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሰዎችን ገንዘብ ዘርፈዋል። ጦርነቱ ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢራናዊያንን የምግብ ዋስትና እጦት አባብሷል።
የዓለም ባንክ ዘገባ እንደሚያመለክተው ጦርነቱ የኢራንን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ከ10 በመቶ በላይ እንደሚቀንስ፣ ሥራ አጥነትን እና የዋጋ ንረትን እንደሚያባብስ፣ የምርት እና ማሕበራዊ መሠረተ ልማቶችን ሽባ እንደሚያደርግ አስጠንቅቋል።
አንድሪያስ ክሪይ እንደገለጹት እስራኤልም በኢራን ላይ ባካሄደችው የመጀመሪያው ሳምንት ጦርነት ብቻ አምስት ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አውጥታ የነበረ ሲሆን በየእለቱም የጦርነት ወጪዋ ከ725 ሚሊየን ዶላር እስከ 593 ሚሊየን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡ ለማጥቃት፣ ለመከላከል እና ለማሰባሰብ 132 ሚሊየን ዶላር አውጥታለች።
ቲ አር ቲ ግሎባል እንደዘገበው እስራኤል ከኢራን ጋር ባካሄደችው የ12 ቀናት ጦርነት 12 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ቀጥተኛ ኪሳራ ደርሶባታል፡፡
የእስራኤል ብዙኃን መገናኛዎች እና የኢኮኖሚ ዘገባዎችም ይህንኑ ነው ያረጋገጡት። አሃዙ ወታደራዊ ወጪን፣ በሚሳኤል ጥቃት የደረሰውን ጉዳት፣ ለግለሰቦች እና ንግድ ድርጅቶች የሚከፈለውን ካሳ እና የመልሶ ግንባታ ወጪዎችን ያጠቃልላል። ተንታኞች ቀጥተኛ ያልሆነ ጉዳት እና የሲቪል ካሳ ሙሉ በሙሉ ከተገመገሙ በኋላ አጠቃላይ ድምሩ ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ሊል ይችላል ብለው ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ዎል ስትሪት ጆርናል በበኩሉ እንደዘገበው እስራኤል ከኢራን ጋር ባደረገችው ጦርነት ሀገሪቱን በቀን 200 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ወጪ አስወጥቷታል፡፡ በየቀኑ ከኢራን የሚወነጨፉ ሚሳኤሎችን እያንዳንዱን ለመጥለፍ ከ 700ሺህ እስከ አራት ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች፡፡
ኒውስ 24 ኦን ላይን በበኩሉ እንደዘገበው የጦርነቱ ወጪ እስራኤል ቀደም ሲል በጋዛ ላይ በተካሄደው ጦርነት የተነሳውን ብሔራዊ የበጀት ጉድለት ወደ ስድስት በመቶ ገደማ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ደግሞ ቢያንስ በዜሮ ነጥብ ሁለት በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገቷን ይገታል፡፡ ይህም የታክስ ገቢ ቅበላን ይቀንሳል።
እስራኤል ለወታደራዊ ወጪ ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር፣ ለንግድ ድርጅቶች፣ ለሠራተኞች እና ለ15 ሺህ ተፈናቃዮች ካሳ ለመክፈል አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል፡፡ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ደግሞ በኢራን የሚሳኤል ጥቃት በሕንፃዎቿ እና በመሠረተ ልማት ላይ ለደረሰ ጉዳት መልሶ ግንባታ ማውጣት ይጠበቅባታል፡፡
እስራኤል በጦርነቱ የወጡ ወጪዎችን ለማካካስ እና አስቸኳይ የመከላከያ ፍላጎቶችን ለመቅረፍ በቀጥታ እርዳታ ወይም የብድር ዋስትና ከአሜሪካ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ልትጠይቅ ትችላለች።
የእስራኤል የሠራተኛ ፌዴሬሽን ምክትል የኢኮኖሚ ዳይሬክተር አዳም ብሉምበርግ በእስራኤል ለሚገኘው ማሪቭ ለተባለው የዜና ጣቢያ እንደተናገሩት በጦርነቱ ምክንያት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ተስተጓጉሎ ስለነበር የንግዱ ማኅበረሰብ ከሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አጥቷል።
በእስራኤል በቤቶች ላይ፣ በተሽከርካሪዎች እና የግል ንብረቶች ላይ የደረሰ የንብረት ውድመት 810 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ይገመታል። ይህ አሃዝ ታዲያ የኩባንያ ማካካሻውን እና የሀገሪቱን አጠቃላይ ምርትን (ቀጥተኛ ያልሆኑ ኪሳራዎችን) አያካትትም።
የእስራኤል ግብር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሻይ አሃሮኖቪች ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ “ይህ የገጠመን ትልቁ ፈተና ነው፤ በእስራኤል ታሪክ ውስጥ እንዲህ ያለ ጉዳት ደርሶ አያውቅም” ብለዋል።
የእስራኤል የፋይናንስ ሚኒስቴር ለመከላከያ የሚሆን 857 ሚሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ ጠይቋል። በተመሳሳይ እንደ ጤና፣ ትምህርትና ማኅበራዊ ደኅንነት ካሉ አስፈላጊ ዘርፎች 200 ሚሊዮን ዶላር ለመቀነስ ሐሳብ ቀርቧል፤ እርምጃው ግን ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል።
አሜሪካ በኢራን የኑክሌር ጣቢያዎች ላይ ባደረሰችው ጥቃትም ከአንድ እስከ ሁለት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንዳወጣች ይታመናል።
(ሳባ ሙሉጌታ )
በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም