ብዙ ጊዜ አስከፊ ጦርነቶች በውይይት ሲቋጩ አይተናል፡፡ ነገር ግን ጦርነት ትቶት ከሚሄደው ዳፋ አንዱ ከአንዱ ትምህርት ባለመውሰዱ ሁሉም በዙር ዋጋ ይከፍላል፡፡
ይህን እያየን የንግግርን እና የሰላምን ዋጋ የምንረዳው እንደውኃ ሙላት እያሳሳቀ ከነበርንበት ወዳልነበርንበት ካደረሰን በኋላ መሆኑ የሚያሳዝን ነው፡፡ የሰላምን ዋጋ በማቅለል ለጦርነት ከምናወጣው ኃይል፣ በጀት እና አቅም ትንሹን ለሰላም ለማዋል ፍላጎት ባለማሳየታችን ዛሬም ድረስ ዋጋ እየከፈልን ነው፡፡
ምክንያቱም ሁልጊዜም ቢሆን ጦርነት ካለ ሞት፣ ጦርነት ካለ መፈናቀል፣ ጦርነት ካለ ስደት፣ ጦርነት ካለ ረሃብ አለ። ከቁሳዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ ባሻገር ጊዜያዊ ዘላቂ እና ቋሚ የሆነ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳትን አስከትሎ ማለፉ የምንጊዜም ሀቅ ነው።
የእኛም እጣ ፈንታ ይሄው ነው፡፡ ከሰሜኑ ጦርነት ሳናገግም ይኼው ዳግም በርስ በርስ ግጭት ውስጥ እንገኛለን፡፡ ብዙዎችን በሞት ከጎናችን አጥተናል፡፡ ብዙዎች ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው ለረሃብ እና ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል፡፡
እንደ ሩዋንዳ ዓይነት ሀገራት እኔን ያየ ይቀጣ እያሉ ዓለምን ለሰላም እየሰበኩ እና ወደልማት ገብተው-እንደኛ ዓይነት ሀገር ያውም ሀገር በቀል የእርቅ፤ የሽምግልና እና ችግርን የመፍቻ መንገድ ያለው ጥንታዊ እና ታሪካዊ ሀገር የራስን ጸብ በራስ ለማርገብ በእልፍ ዛሬም የበርካታ ህይወት በሚገበርበት ግጭት ውስጥ ገብተን ዋጋ እንከፍላለን፡፡
እንደኛ በችግር ውስጥ የነበሩት ሩዋንዳውያን ችግራቸውን ዳግም እንዳይመለስ በእርቅ እና በይቅር ባይነት ዘግተዋል፡፡ ነገር ግን ጥሎት ያለፈው ጠባሳ ዛሬም ድረስ አልሻረም፡፡ ለታሪክ የሚቀመጥ ጠባሳን ከማሳረፉ በፊት እኛም ችግራችንን በንግግር እና በውይይት ፈተን ወደሰላም እና ወደልማት መመለስ ይሻለናል፡፡ በጊዜ መፍትሔ ካልፈለግንለት የርስ በርስ ግጭት ውጤቱ ሁላችንንም ነው ሚበላን፡፡
ሰላምን እስካመጣ ድረስ ከግማሽ በላይ መንገድ እንኳ ቢሆን ሄደን ችግርን በስክነት፣ ከእልህ በዘለለ እና መፍትሔ ባለው መልኩ መነጋገር ትውልድን የማዳን ኃላፊነት መወጣት ለምን አቃተን? መልሱና መፍትሔው ዛሬም በእጃችን ነው፡፡
በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም