መጥፎ የአፍ ጠረን መንስኤ እና መፍትሔው

0
156

“መጥፎ የአፍ ጠረን  ሰላም የሚነሳና በዕለት ተዕለት ሕይዎት ከሰዎች ጋር በምናደርገው መስተጋብር ምቾት እንዳይሰማን የሚያደርግ ትልቅ ችግር ነው”፡፡  ይህን ያሉን በባሕር ዳር ከተማ በዶ/ር ፍስሀ ስፔሻሊቲ የጥርስ ሕክምና ክሊኒክ ቺፍ ዴንታል ሰርጅን ዶ/ር ፍስሀ አምበሉ ናቸው። መጥፎ የአፍ ጠረን መንስኤዎቹ እና መፍትሔዎቹ መንድን ናቸው? የሚለውን ለእንናንተ ለአንባቢያን ግንዛቤ ለመፍጠር ከዶ/ር ፍስሀ አምበሉ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

 

ዶ/ር ፍስሀ አምበሉ እንደገለጹት መጥፎ የአፍ ጠረን በእንግሊዝኛው /halitosis or bad breath/ የሚባል ሲሆን  የሚከሰተውም በሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው እና 90 በመቶ አካባቢ የሚሆነው መንስኤ  የአፍ እና የአፍ ውስጥ አካላት ጤና መዛባት ሲኖር ነው። ይህ ማለት ከአፋችን ከውጨኛው ክፍል ከከንፈር እስከ ጉሮሮ የታችኛው ክፍል ድረስ ባሉት መዋቅሮች ላይ  የጤና መዛባቶች ሲኖር ነው፡፡

 

ለአብነትም የድድ ኢንፌክሽን፣ የላንቃ መሰንጠቅ፣ በአንድም በሌላ ምክንያት በትክክል ያልተገጠሙ ሰው ሠራሽ ጥርሶች ሲኖሩ በመካከል ምግብ እና ባክቴሪያ ሊይዝ ስለሚችል የመጥፎ ጠረን መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡ የተቦረቦሩ እና  በጥርሶቻችን መካከል የሚፈጠሩ ክፍተቶች በውስጣቸው ምግብ መያዝ የሚችል ክፍተት ሲኖራው፣  የድድ ቦታውን መልቀቅ (periodontal pocket)  በሚፈጠርበት ጊዜ የምግብ ቅሪት (ቁርጥራጭ) ወይም ልመት ይሰገሰጋል፡፡ በዚህ ወቅት  አፋችን ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ባክቴሪያዎች ይኖራሉ፤ ጎጅ ባክቴሪያዎችም ከምራቅ ጋር በመዋሀድ እነዚህን የምግብ ቅሪቶች እንዲሰባበሩ ያደርጋሉ፡፡ ይህም ሂደት በሚከናዎንበት ጊዜ  የሰልፈር ጋዝ ይለቀቃል። ይህ ሳልፈር የተባለው ንጥረ ነገር አፋችን ውስጥ መጥፎ የአፍ ጠረን (የተበላሸ እንቁላል አይነት ጠረን)  እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡

 

እንደ ጥርስ  ሁሉ ምላስም በአግባቡ ፅዳቱ ካልተጠበቀ ብዙ ሸካራ አና ወጣ ገባ ያሉ ቦታዎች ስላሉት የምግብ ቅሪት እና ባክቴሪያዎች በቀላሉ አጠራቅሞ መጥፎ የአፍ ጠረን ሊፈጥር ይችላል፡፡

ባለሙያው አክለው እንደገለጹት ለአፋችን ንፅህና ምራቅም አስተዋፅኦ አለው። ማለትም ምራቅ በበቂ መጠን አፋችን ውስጥ ካለ ያሉትን የባክቴሪያ እና የምግብ ቅሪቶች በማንሸራተት ወደ ውስጥ በመላክ ጠረን እንዳይፈጥሩ ይከላከላል፡፡ ሆኖም ምራቅ በተገቢው መንገድ ሳይመነጭ ቀርቶ  አፍ ከደረቀ ለባክቴሪያ ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር መጥፎ የአፍ ጠረን ሊያመጣ ይችላል፡፡

 

በተጨማሪም ዶ/ር ፍስሀ እንዳሉት የጉሮሮ፣ የእንጥል፣ የድድ፣ እንዲሁም የምላስ መቁሰል ወይም ኢንፌክሽን ካለ  መጥፎ የአፍ ጠረን መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡ ሲጋራ ማጨስና መጠኑ የበዛ አልኮል ማዘውተርም መጥፎ የአፍ ጠረንን ሊያመጣ ይችላል፡፡ እንዲሁም ምንም እንኳ የሚያመጡት መጥፎ ጠረን ከተወሰኑ ሰዓታት በኋላ በራሱ የሚጠፋ ቢሆንም በተፈጥሮ ከባድ ሽታ ያላቸው ምግቦች ለምሳሌ እንደ ቀይ እና ነጭ ሽንኩርት ያሉትን ምግቦች መጠቀም ጊዚያዊ የሆነ የአፍ ጠረን ለውጥ ሊያስከትል ይችላል፡፡

 

ከዚህ ውጪ 10 በመቶ (ሁለተኛው መንስኤ) ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው ውስጣዊ የሆነ የጤና መዛባት ሲኖር ነው፡፡ በአግባቡ ቁጥጥር ያልተደረገበት የስኳር ሕመም ሲኖር፣ የኩላሊት፣ የሳንባ፣ የጉበት እንፌክሽኖች ለመጥፎ የአፍ ጠረን መኖር የራሳቸው አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ በተጨማሪም የጨጓራ ሕመም ሲኖር ከፍተኛ አሲድ ስለሚመነጭ   ማፋቅ ወይም ማግሳት ይኖራል፤ በዚህ ጊዜ የሚመነጨው አሲድ ወደ ምላሳችን መጨረሻ ክፍል በመምጣት ይከማቻል፡፡ በሚከማችበት ጊዜም መጥፎ የአፍ ጠረን ይኖራል፡፡

 

በሌላ በኩል መጥፎ የአፍ ጠረን አለ ማለት ውስጣዊ የጤና ችግር አለ ማለት እንዳልሆነ መገንዘብ እንደሚገባ ባለሙያው አብራርተዋል፡፡ ትክክለኛውን መንስኤ ለማወቅ ምርመራ አስፈላጊ እንደሆነ ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡

ዶ/ር ፍስሀ እንዳብራሩት መጥፎ የአፍ ጠረን ከጥርስ መቦርቦር እና ከጥርስ አቃፊ ችግሮች በመቀጠል ወደ ጥርስ ሕክምና ክሊኒኮች በሦስተኛ ደረጃ የሰውን ልጅ  በማመላለስ ይታወቃል፤ ቀላል ችግር ቢመስልም ተገቢው ክትትል ተደርጎ ካልተወገደ ግን ትዳርን እስከማናጋት ሊደርስ  እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡ ባለሙያው  “በጥርስ ሕክምና ሙያ ውስጥ ካሳለፍኳቸው የተወሰኑ ዓመታት ችግሩ የበርካቶችና አሳሳቢ መሆኑን ለመረዳት ችያለሁ” ሲሉ ነው የችግሩን አሳሳቢነት የገለጹት፡፡

 

እንደ ባለሙያው ገለጻ አንድ ሰው መጥፎ የአፍ ጠረን እንዳለበት እና እንደሌለበት በዋናነት በተለያዩ ቀላል መንገዶች በራሱ ሊያረጋገጥ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው ንፁህ ማንኪያ ወይም ጠቋሚ ጣትን በመጠቀም ወደ ምላስ የመጨረሻ ክፍል በመላክ ከላይ ያለውን ነጭ ምራቅ መሰል ዝልግልግ ነገር በመፋቅ እና በማሽተት ለሌሎች ሰዎች ሊሸት የሚችለውን እራሱ ማወቅ ይችላል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ምንም እንኳ ከላይ እንደተጠቀሰው ዘዴ ሙሉ በሙሉ ትክክለኛዉን ሽታ ሊያሳይ ባይችልም አፍን በመጠኑ በእጅ መዳፍ በማፈን ትንፋሽን ወደ አፍንጫ እንዲሄድ በማድረግ ያለውን ጠረን በማሽተት  ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

 

ሌላው  የቅርብ ወዳጆችን በመጠየቅ  መጥፎ የአፍ ጠረን እንዳለ እና እንደሌለ   ማወቅ ይቻላል፡፡ “እዚህ ላይ ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ” በማለት ባለሙያው አጽንኦት የሰጡት መጠፎ የአፍ ጠረን ችግር ያለበትን የቅርብ ሰው ችግሩን ከመንገር ወደ ኋላ ማለት እንደማይገባ ነው፡፡ ምንም እንኳን በቀጥታ “አፍህ ይሸታል” ብሎ መናገር ቢከብድም ነገሩን አቅልሎ ወደ ሕክምና በመሄድ መፍትሄ ሊያገኝ እንደሚችል መምከር የተሻለ እንደሆነ ነው የጠቆሙት፡፡

 

ዶ/ር ፍስሀ እንደሚሉት መጥፎ የአፍ ጠረን በትክክል መፍትሔ ሊሰጠው የሚችለው የጠረኑ መንስኤ በአግባቡ ተለይቶና ታውቆ ተገቢው ሕክምና ሲሰጥ ብቻ ነዉ፡፡  ማለትም የተቦረቦረ ጥርስ ካለ በመሙላት፣ የተከማቸ ቆሻሻ ካለ በማንሳት፣ የአፍ ውስጥ ቁስለት (ኢንፌክሽን) ካለ በተገቢው መንገድ በማከም መፍትሔ ማግኘት ይቻላል፡፡

ይሁንና የአፍ ውስጥ አካላት ችግሮች ተቀርፈው ጠረኑ ቀጣይነት ካለው  ከውስጣዊ ችግሮች ጋር በተያየዘ ሊሆን ስለሚችል ውስጣዊ አካላት ላይ ምርመራ አካሂዶ መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግ ነው  የጠቆሙት።

 

በተጨማሪም በሰጡት ሙያዊ ማብራሪያ ጧትና ማታ የምንጠቀምበትን የጥርስ ሳሙና የአገልግሎት ዘመኑ አለማለፉን ማጤን ያስፈልጋል። ሁሉንም የጥርስ ቦታዎች በለስላሳ ቡርሽ ከድድ ወደ ጥርስ መቦረሽ፣ ጥርስ ተጸድቶ ካለቀ በኋላ ምላስን ከኋላ ወደ ፊት በደንብ ማጽዳት፣ ከቡርሽ በተጨማሪ የጥርስ ማጽጃ ክር (dental floss) ተጠቅሞ ጥርስን ማፅዳት፣ በጥርሶች መካከል  የተከማቸ ሽህላ (ጠጠር መሰል በጥርሶች መካከል የሚኖር ቆሻሻ) ካለ የጥርስ ሐኪም ዘንድ ቀርቦ  ማስጸዳት፣ በሐኪም የታዘዘ የአፍ መጉመጥመጫ ፈሳሽ ካለ በአግባቡ መጠቀም፣ ከስኳር ነጻ የሆኑ ማስቲካዎችን ማኘክ (የምራቅ መመንጨትን ስለሚያበረታታ አፍን ጽዱ የማድረግ አቅም አለው) ተገቢ ነው። እንዲሁም በቂ ውኃ መጠጣት፣ ምግብ ከተመገብን በኋላ አፍን በንጹህ ውኃ መጉመጥመጥ፣ የጥርስ ቡርሹ አናት ላይ ያሉ ክብ ለስላሳ ጫፎች ከረገፉ ቡርሹን መቀየር (አንድን ቡርሽ ከሦስት ወር በላይ ባንጠቀምበት ይመከራል)፣ ጥርስ ከተጸዳ በኋላ ቡርሹን በንጹህ ውኃ አለቅልቆ ደረቅ ቦታ ላይ ማስቀመጥ፣ የጥርስ ቡርሽና ሳሙና ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ካለ ጥርስና ድድን ሊጎዱ በማይችሉ ንፁህ የእንጨት መፋቂያዎች መጠቀም መልካም ነዉ፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here