“ሰማይ ተቀደደ ሰፊ ሽማግሌ መች ገደደ”

0
129

የኢትዮጵያ የእርቅ እና የግጭት አፈታት ታሪክ እንደ ሀገሪቱ ታሪክ ሁሉ ረጅም፣ ውስብስብ እና በባሕላዊ እሴቶች የተሞላ ነው። ሕግ እና  ዘመናዊ ስርዓት ከመመስረቱ በፊት ለዘመናት ባሕላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ጥቅም ላይ ውለዋል:: ለዛሬው ዘመናዊ የፍትሕ እና ፍርድ ቤቶች አመሰራረት እና አሠራር መሠረትም ሆነዋል:: ፍርድ ቤቶችም ለባሕላዊ እርቅ እና ሽምግልና የሕግ ድጋፍ እና እውቅና ሰጥተዋል::

ግጭቶች በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የመንጋት እና የመምሸት ያህል አይቀሬ አውነታዎች ናቸው:: አሁን ዓለም የያዘው ቅርጽ፣ ወርድ እና ቁመት የግጭት እና ጦርነት ውጤት ነው:: ሀገራት በጦርነት እና ግጭት ነው የተመሰረቱት:: ዳር ድንበራቸውን ያስቀጠሉት ወይም ግዛታቸውን ያሰፉትም እንዲሁ::

የፍላጎት ወይም የግቦች አለመጣጣም ያጋጫል:: ግጭት የሚቀጥል ክስተት ነው:: ከራስ ግንዛቤ ይነሳል:: ጥቅምም ጉዳትም አለው::

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ክፍል በኢትዮጵያ ቋንቋ እና ስነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ለኤም ሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ  በ ብርሃኑ  ሰሀሉ  የቀረበ ጥናት ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት በአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ ምን እንደሚመስል አስፍሯል:: በዚህም ጥናት ባሕላዊ የእርቅ እና ሽምግልና ስርዓቶች መግባባትን ያጠናክራሉ፤ ተሻጋሪ የሆኑትን አብሮነትን እና መግባባትን ያመጣሉ::

በሁለት ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት መካከል መተማመንን ይፈጥራሉ:: ባሕላዊ የግጭት አፈታት ከዘመናዊው የግጭት አፈታት ጋር ተቀራርቦ በጋራ የሚሰሩበትን መንገድ ያመቻቻል ይላል ጥናቱ:: ባህላዊ የግጭት መፍቻ ስልቶች በይቅርታ፣ በምሕረት እና በፍትህ አሰጣጥ ላይ የሚያተኩሩ በመሆናቸው ጠቀሜታቸው የጎላ ስለመሆኑ ጥናት አድራጊው ጽፈዋል::

ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ወገኖች (ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ድርጅቶች ወይም ሀገራት) ላይግባቡ፣ ሊጋጩ ወይም ሊጣሉ ይችላሉ:: ይህ ግጭት የሚመነጨው ወገኖቹ ያላቸው ፍላጎት፣ ግብ፣ እሴት ወይም ሀብት እርስ በርሱ የሚቃረን ወይም የማይጣጣም ከመሆኑ የተነሳ ነው::

ግጭት ቃላዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ስነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ መካረርን እና ውጥረትንም ይጨምራል። ከዚህ ሲያልፍ ግጭት አካላዊ ጥቃት ይሆናል::

አንድም ነገር ያለ ጉዳት እና ጥቅም አይሆንምና ግጭትም አዎንታዊ እና አሉታዊ ገጽታዎች አሉት:: ከአሉታዊ ገጽታዎች መካከል ግንኙነቶችን ያበላሻል፣ ጥላቻን፣ ጥርጣሬን እና በቀልን ይፈጥራል። ሀብትን ያወድማል፤ ጊዜንና ጉልበትን ያባክናል። አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳትም ያስከትላል።

ግጭቶች ካሉት አዎንታዊ ገጽታዎች መካከል ችግሮችን በግልጽ ለመነጋገር እድል ይፈጥራል። የተሻሉ መፍትሄዎችን እና አዳዲስ ሀሳቦችን ለማምጣት ያግዛል። ፈጠራን ያበረታታል። ማኅበራዊ ለውጥን ሊያመጣ ይችላል። የወገኖችን ማንነት እና አቋም ግልጽ ያደርጋል።

የዓለም ሕዝቦች ታሪክ እንደሚያሳየው ግጭት የሰው ልጅ ማኅበራዊ ህይወት አንዱ አካል ነው። ቁልፉ ጉዳይ ግጭት መኖሩ አይደለም። ግጭቱን በሰለጠነ እና በሰላማዊ መንገድ መፍታት ተችሏል ወይ  የሚለው ነው።

በሀገራችንም ግጭቶች የሕይወታች አካል ናቸው:: ኢትዮጵያ ዘመናዊ የሕግ ስርዓት ከመዘርጋቷ ከብዙ ዘመናት በፊት በማህበረሰቡ ውስጥ የተገነቡ ጠንካራ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ነበሯት። እነዚህ ስርዓቶች በዋናነት የሚያተኩሩት ቅጣትን በማስፈጸም ላይ ብቻ አልነበረም። የተበላሸውን ማህበራዊ ግንኙነት በመጠገን እና ዘላቂ ሰላምን በማምጣት ላይም ጭምር እንጂ።

ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ተደራሽነት ያላቸው መሆኑ ተመራጭ ያደርጋቸዋል:: ለማህበረሰቡ ቅርብ፣ ወጪ ቆጣቢ እና ፈጣን ናቸው። ማህበራዊ ሰላም የሚፈጥሩም  ናቸው::  ከቅጣት ይልቅ ግንኙነትን በመጠገን ላይ ስለሚያተኩሩ ዘላቂ ሰላምን ያመጣሉ። ተቀባይነትም ያላቸው ሆነው ይታያሉ:: በማህበረሰቡ ባህል እና እሴት ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው ውሳኔዎች በቀላሉ ተቀባይነት ያገኛሉ።

“ሽማግሌ አየ እግዜር አየ፤ ሰማይ ተቀደደ ሰፊ ሽማግሌ መች ገደደ” እና መሰል አባባሎች የትኛውም ግጭት ከማህበረሰቡ አስታራቂ ወገኖች በላይ እንዳልሆነ ያሳያል። የሀገር ሽማግሌዎችን አቅም እና ተሰሚነትም ይናገራል።

“ባህላዊ የደም ማድረቅ እርቅ ስርዓት በላሎ ማማ ምድር ወረዳ” በሚል ዓለሙ ካሳየ በአዲስ በአበባ ዩንቨርሲት ጥናት አድርገዋል::

በዚህ ጥናት መሰረትም  ሁለት ዓይነት የግጭቶች አሉ። የመጀመሪያው እውነተኛ እና ተጨባጭ ግጭት ይባላል:: ይህም ግጭት በሁለት ወገኖች መካከል ባሉ የተገደቡ ሀብቶች ላይ በሚኖር አለመግባባት የሚከሰት ነው::

ሁለተኛው የግጭት ዓይነት ውል-አልባ ወይም ጭብጥ የለሽ ግጭት ነው። ተቀናቃኞቹ ወገኖች የሚያነሡት እና የሚያቀርቧቸው ርዕሶች ተጨባጭ ምክንያት በሌለበት ሁኔታ በስሜት በመነሳሳት እና በግልፍተኝነት የሚፈጽሙ ናቸው።

“ግጭቶች በቤተሰብ፣ በጎረቤት እና በፍትሐ ነገሥት፣ በአካባቢ፣ በጎሳ ሽማግሌዎች፣ በሃገር ሽማግሌዎች፣ በኃይማኖት አባቶች፣ በብሔር አዛውንቶች፤ በፍርድ ቤት፤ በፖሊስ እና በመደበኛ ፍርድ ቤት አማካኝነት ይፈታሉ፡” ሲል ጥናቱ አስፍሯል።

ከፍርድ ቤት ውጪ ያሉ ግጭቶች ሊፈቱ የሚችሉባቸው መንገዶችን ሲያስቀምጥ ጥናቱ ድርድር፣ የግልግል ዳኝነት እና ሽምግልናን ይጠቅሳል።

ድርድር፤ የግልግል ዳኝነት፤ እና ሽምግልና ሦስቱም አማራጮች ግጭትን ለመቀነስ ወይም ለማስቆም ያግዛሉ። እርቅን በማውረድ ሰላምን እና መተመመንን ያመጣሉ። ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ዘላቂ መተማመንን አግኝተው በሰላም እንዲኖሩም መልካም አማራጮች መሆናቸውን ጥናቱ ይጠቅሳል።

ግጭቶችን በይቅርታ እና እርቅ መንፈስ መፍታት ቀጣይነት ካለው የደም መፋሰስ፣ ሰላም እጦት እና በቀል ያድናል። የግጭቶች  ሁኔታ እና ክብደት ታይቶ ማን እንደሚፈታቸውም ይወሰናል። የሚፈቱበት በተለያዩ መንገዶች ነው:: የሃገር ሽማግሌዎች የሚፈቷቸው ችግሮች አሉ። የሀይማኖት አባቶች የሚፈቷቸውም አሉ። የጎሳ መሪዎችም የሚፈቷቸው ይኖራሉ። የነፍስ አባቶች የሚፈቷቸው በባልና ሚስት መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች ይኖራሉ። በቤተሰብ እንደ አባት፣ በእናት፣ ታላቅ ወንድም፣ በአያት፣ በአማች እና በአክስት የሚፈታ  የዝምድና የሽምግልና  ዓይነትም አለ።

ለታሪክ ተሾመ “በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባሌ ኦሮሞ ባሕላዊ ግጭት አፈታት” በሚል ርእስ ጥናት አድርገዋል። በዚህም ማህበረሰባዊ የግጭት መፍቻ ስርዓቶች ባሉበት መቀጠል ቢችሉ ለአሁኑም ይሁን ለመጪው ትውልድ ፋይዳቸው የጎላ ነው ብለዋል። ሰላምና እርቅን ለማስፈን በነጻ የሚሰሩ የሀገር ሽማግሌዎች እና አስታራቂዎች የበለጠ እንዲሰሩ በመንግሥት በኩል ክፍያ ቢሰጣቸው መልካም ነው ሲሉ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል።

አዲሱ ትውልድ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን እንዲያውቅ ስርዓተ ትምህርት ውስጥ ማካተት ተገቢ ነው ሲሉም መክረዋል። የሀገር ሽማግሌዎች እና የመደበኛ ፍርድ ቤት ዳኞች በመቀራረብ ተረዳድተው መስራት ቢችሉ የሚል ምክረ ሐሳባቸውን በጥናቱ መጨረሻ ላይ አስፍረዋል።

ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ስርዓቶች ለዓመታት የሀገርን ሰላም አስጠብቀው ቀጥለዋል። በየአካባቢው በልዩ ልዩ መጠሪያዎች ጥቅም ላይ የሚውሉ የማስታረቂያ እና ሽምግልና ዘዴዎች አሉ። ባህላዊ ስርዓቶች በአብዛኛው ውጤታማ የሚሆኑት በማኅበረሰብ ወይም በግለሰቦች መካከል ለሚፈጠሩ ግጭቶች ነው። ሀገር አቀፍ እና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ውስብስብ ግጭቶች ለመፍታት አቅማቸው ውስን ሊሆን ይችላል።

የኢትዮጵያ የእርቅ እና የግጭት አፈታት ታሪክ ከህዝቦቿ ባህል፣ ማሕበራዊ አኗኗር እና ታሪክ ጋር የተቆራኘ ነው። ከጥንት ጀምሮ የነበሩት እንደ ሽምግልና ያሉ ባሕላዊ ስርዓቶች፣ ዛሬም ድረስ በማህበረሰቡ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው። ምንም እንኳን ዘመናዊው የሕግ ስርዓት ቢኖርም፣ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የእነዚህን ባሕላዊ ስርዓቶች ጠንካራ ጎኖች ከዘመናዊ አሠራሮች ጋር በማቀናጀት መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ታሪኳ ያስተምራል።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሐምሌ 7  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here