ያለፈው እንዳይደገም…

0
128

ባለፋት ዓመታት በክልሉ በተካሄደ ግጭት ከስድስት ሺህ 154 በላይ ትምህርት ቤቶች ለጉዳት መዳረጋቸውን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ በትምህርት ዘርፉ ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ከአጋር አካላት ጋር ምክክር ባካሄደበት ወቅት አስታውቋል፡፡ ይህም በክልሉ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል የ57 በመቶ ድርሻን ይይዛል፡፡

በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን ብቻ እንኳ ከአራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤታቸው አልመጡም፡፡  ከአራት ሺህ 821 በላይ ትምህርት ቤቶች አልተከፈቱም፡፡

ዘንድሮ ከትምህር ገበታ ውጪ ሆነው የከረሙት ተማሪዎች ቁጥር ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ከፍ ያለ ነው፡፡ ይህም ሰፊ ሥራን የሚጠይቅ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮም በእስካሁን ሂደት በትምህርት ዘርፉ ላይ አጋጥሞ የነበረው ችግር በቀጣይ ዓመትም እንዳይደገም ከወዲሁ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ ባለድርሻ አካላትም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ መድረኮችን እያዘጋጀ ምክክር በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ አንዳንድ አካባቢዎችም ያለፉ ዓመታት ችግሮችን እየለዩ፣ ለቀጣይ ዓመት መውጫ መንገድ ይሆናሉ ባሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከዲሁ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ ውስጥ ባጋጠመው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ተስተጓጉሎ የቆየው የትምህርት እንቅስቃሴ በቀጣይ ዓመት እንዳይቀጥል ቀድመው እየሠሩ ካሉ አካባቢዎች መካከል የሰሜን ሸዋ ዞን ይገኝበታል፡፡ በአዲስ የትምህርት ዓመት የትምህርት ተቋማትን በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ማስገባት የዞኑ ትምህርት መምሪያ ቁልፍ ተግባር መሆኑን የ2017 ዓ.ም የአፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 ዓ.ም የዕቅድ ትውውቅ ፕሮግራሙን በደብረ ብርሐን ከተማ ባካሄደበት ወቅት አስታውቋል፡፡

በዞኑ ከ400 በላይ ትምህርት ቤቶች በ2017 ዓ.ም ተዘግተው መቆየታቸውን ለተጽእኖው ማሳያ አድርገው ያነሱት ደግሞ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ፀጋዬ እንግዳወርቅ ናቸው፡፡ 238 ትምህርት ቤቶችም በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች መውደማቸውን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ችግሮችን መለየት እና ለቀጣይ የትምህርት ዘመን ማኅበረሰቡን ባለቤት የማድረግ ሥራ ከወዲሁ ለመሥራት ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ  ደስታው ዓለሙ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ የትምህርት ሥራው በእጅጉ እንዲስተጓጎል ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ደስታው ገለጻ ከ200 በላይ በሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ጉዳት ደርሷል፡፡ የደረሰው ጉዳት ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመትም አስታውቀዋል፡፡ ኅብረተሰቡ በትምህርት ዘመኑ ለተጎዱ ትምህርት ቤቶች ጥገና፣ ግንባታ እና ግብዓት ለማሟላት ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እና የጉልበት ድጋፍ ማድረጉን የሕዝቡ የትምህርት ፈላጊነት ማሳያ አድርገው አንስተዋል፡፡

በ2017  የትምህርት ዘመን ከ50 በመቶ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ሆነው መክረማቸውን አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡ በትምህርት መዋቅሩ፣ በኅብረተሰቡ፣ በመሪዎች እና በጸጥታ መዋቅሩ የጋራ ጥረት ግን ከ163 ሺህ በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ በማድረግ የመማር ማስተማር ሥራ መከናወኑን አረጋግጠዋል፡፡

በ2018 የትምህርት ዘመን ሁሉንም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ ሕዝቡን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከብዙኃን መገናኛ መሪዎች እና ባለሙያዎች ጋር ምክክር አካሂዷል። በውይይቱ በክልሉ ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙ ችግሮች የትምህርት ዘርፉን ክፉኛ እንደፈተኑት በውይይቱ የተሳተፉ አካላት ተናግረዋል፡፡ ግጭቱ ሚሊዮኖችን ከትምህርት ገበታ በማራቅ እየፈጠረ ካለው የትውልድ ክፍተት ለመውጣት በትብብር እና በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ግጭቱ የፈጠረውን ያልተገባ አመለካከት ማረም እንደሚገባም ተናግረዋል።

“መምህራን ታግተው በገንዘብ ተለቅቀዋል፤ ከክብራቸው ተዋርደው ተንበርክከው ተገርፈዋል፤ ተማሪዎች እና መምህራን ተሸማቅቀው እየኖሩ ነው፡፡ በመሆኑም የትምህርት ተቋማትን ደኅንነት ማስጠበቅ ጊዜው የሚጠይቀው ከትውልድ ክፍተት የመዳኛ ዋነኛው መንገድ ሊሆን ይገባል” በማለትም ተሳታፊዎች አስገንዝበዋል፡፡

የተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አለመምጣት ሁሉንም ሊያሳስብ ይገባል ያሉት ተሳታፊዎቹ፤ በቀጣይ የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍሎ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ማምጣት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የተፈጥሮ እና የሰው ሠራሽ ችግሮች በትምህርት ተሳትፎ፣ ተደራሽነት እና ፍትሐዊነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን ያስታወቁት የትምህርት ቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጌታቸው ቢያዝን ናቸው፡፡

ትምህርቱ ያጋጠመው ችግር በትውልድ ላይ ብክነት እየፈጠረ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ የባከነውን ለማካካስ ንቅናቄ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ የሚደረጉ የትምህርት ንቅናቄዎችን ብዙኃን መገናኛዎች በተደራሽነታቸው ልክ በመሥራት እንዲደግፉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

መሠረተ ልማትን ማሟላት፣ ትምህርት ቤቶችን መጠገን፣ በትምህርት ቁሳቁስ ችግር ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዳይርቁ መሥራት እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ለአንድ ተማሪ የትምህርት ቁሳቁስ እንዲያሟላ የንቅናቄ ሥራ መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የተጀመሩ የትምህርት ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ እና ለተማሪዎች ምገባ የግንዛቤ ፈጠራ እና የሃብት ማሠባሠብ ሥራ ከብዙኃን መገናኛዎች እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።

በትምህርት ዘርፉ ላይ የገጠመው ችግር እንዲያበቃ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እና ወጣቶች የበኩላቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊዋ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ትምህርትን የሕዝብ አጀንዳ በማድረግ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን  ሚና ከፍተኛ እንደ ነበር ተናግረዋል፡፡ ትምህርት የልጆቻችንን እና የሀገር እጣ ፈንታን የሚወስን መሆኑን ለኅብረተሰቡ ማሳየት የሚዲያዎች ቀዳሚው ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ኅብረተሰቡ “ትምህርትን የሚቃወም ሁሉ ጠላቴ ነው!” ብሎ እንዲታገል መሥራት እንደሚገባው ጠይቀዋል፡፡ አሁንም የትምህርት ሥራ የሌላ ዓላማ ማስፈፀሚያ እንዳይሆን በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በክረምቱ ወራት የተጎዱ የትምህርት ተቋማት መልሶ ግንባታ ማከናወን፣ የመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት ላለባቸው  ተማሪዎች ድጋፍ ማሰባሰብ እና በርካታ   የበጎ ፈቃድ ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here