መሀንዲሶችን ከስራ ያሳገደዉ የድልድይ ግንባታ

0
62

በህንድ ማዳይ ኘራዲሽ ግዛት፣ ቦፓል በተሰኘው ቀጣና በባቡር መጓጓዣ መስመር አናት ላይ የተሰራው 90 ዲግሪ የሚታጠፍ የተሽከርካሪ መሻገሪያ ድልድይ ለአደጋ አጋላጭ ነው የሚል ውዝግብ በማስነሳቱ ሰባት መሀንዲሶች ከስራ መታገዳቸውን አዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ከሰሞኑ አስነብቧል::

ቦፓል በተሰኘው ቀጣና የተሰራው 648 ሜትር የሚረዝመው ድልድይ ከ10 ዓመታት በፊት ሁለት ሚሊዮን ዶላር ወጥቶበት ከተጠናቀቀ በኋላ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን  ምስሉ በመታየቱ በተመልካቾች መካከል ውዝግብ አስነስቷል::

የድልድዩ ግንባታ የተጓዦችን ደህንነት ከግምት ያስገባ አይደለም በሚል በበርካቶች የነቀፌታ አስተያየት ተሰንዝሮበታል::

በግንባታው ላይ የተነሳውን ውዝግብ እና  ትችት ተንተርሶ የማዳይ ኘራዲሽ ግዛት የግንባታ ሚንስትር  ሞሐን   ያዳቪ በስራው ላይ የተሰማሩ ሁለት ዋና መሀንዲሶች፣ ግንባታውን የሚያከናውነው ድርጅት ኃላፊ፣ ቀያሾች፣ የንድፍ አማካሪ በድምሩ ሰባት ሃላፊ አና ባለሙያዎችን በግንባታ ጨረታ እንዳይሳተፉ መታገዳቸውን በቲዊተር ገጻቸው ማስታወቃቸው ነው ለንባብ የበቃው::

በኗሪዎች ለቀረበው አቤቱታ የግዛቱ ባለስልጣናት ለድልድዩ አሁን ከታየው ውጪ አማራጭ አለመኖሩን፣ ለግንባታው ሰፊ መፈናፈኛ መታጣቱ እንዲሁም የባቡር መስመሩ መገጣጠሚያ ቦታ ላይ መሆኑ ለችግሩ መንስኤ  መሆኑን እንደምክንያት አስረድተዋል::

የከተማዋ አመራሮች የግንባታ ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ ተጨማሪ የማስፋፊያ ቦታ አፈላልጐ እና አሸጋሽጐ 90 ዲግሪ የሚታጠፈውን በማስፋት  መፍትሄ ለመስጠት እንደሚተጉ ነው በማደማደሚያነት ያረጋገጡት::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here