የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ

0
76

ከሃምሳ ዓመታት በላይ የፖለቲካ ህይወት አሳልፏል፤ ከዚህ ውስጥ 47 ዓመቱን ሁሉንም የዓለም ሃገራትን የማንበርከክ አቅም አለኝ ለምትለው አሜሪካ ደጇ ላይ ሆኖ እጅ ባለመስጠት ሃገሩን አስከብሯል። ለሃገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ የቁርጥ ቀን ባለውለታ ነው። ይህ ጽሑፍ በዚህ ሰው የህይወት ታሪክ እና ባበረከታቸው ዓበይት ተግባራት ዙሪያ ትኩረት ያደርጋል።

ባለታሪካችን የኩባዉ ፊደል ካስትሮ ሩዝ ነው። ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አስደናቂ ሰዎች መካከል አንዱ እንደነበርም ይገለጻል። ካስትሮ የተወለደው በደሴቲቱ ሀገር ኩባ፣ ኦሬንቴ ግዛት፣ ቢራን በተባለች መንደር  ነው። ወላጆቹ የተማሩ ባይሆኑም ልጆቻቸውን ለማስተማር የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት አድርገዋል። ከልጅነቱ ጀምሮ ጥሩ የማስታወስ ችሎታ ስለነበረውም ምርጥ ተማሪ ለመሆን በቃ። በፅናት የማመፅ ፍላጎት ያሳየውም ልጅ ሆኖ ነበር። በአሥራ ሦስት ዓመቱ በሠራተኞች አመፅ ተሳትፏል፤ በውስጡ ከነበሩት መሪዎችም አንዱ ነበር።

እ.አ.አ. በ1950 በሃቫና ዮኒቨርስቲ በሕግ በድግሪ ተመርቋል። ከዚያም ብዙም ሳይቆይ በሕግ ባለሙያነት በግል መሥራት ጀመረ። ድሆችን በነፃ ይከላከል ስለነበርም ወሰን የሌለው የሕዝብ ፍቅር እና አክብሮት አገኘ። የአብዮት መንፈስ በካስትሮ ነፍስ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጣ።

እ.አ.አ በ1953 በፉልገንሲዮ ባቲስታ ገዥ ላይ ሴራ አደራጀ። ሴራው ሳይሳካ ቀረ። ብዙ ተሳታፊዎች ተገደሉ። ፊደል ካስትሮ ግን አሥራ አምስት ዓመት ተፈርዶበት ዘብጥያ ወረደ። ከሀያ ሁለት ወራት እስር በኋላ በምሕረት ተለቆ ወደ ሜክሲኮ ተሰደደ።

ዓለም በሁለት ሃያላን መንደር ማለትም በሶቭየት ሶሻሊስት እና በአሜሪካ ኢምፔሪያሊስት ጎራ ተከፍላ በነበረችበት በነዛ ቀውጢ ዓመታት ውስጥ አብዮተኛው ፊደል ካስትሮ እንደነ ቼ ጉቬራ ከመሳሰሉ ጓደኞቹ እና ከታናሽ ወንድሙ ጋር በመሆን እ.አ.አ በ1953 የትጥቅ ትግል ጀመረ።

በወቅቱ ከአንድ መቶ ሃምሳ ኪሎ ሜትር በላይ ለአሜሪካ የማትርቀው ኩባ ለአሜሪካኖች አሸሸ ገዳሜ ማቅለጫ፣ በወሲብ የመቅበጫ፣ የመጠጥ መራጫ እና የሃሺሽ ማጨሻ ሃገር ነበረች። ከዚህ ነፃ አውጥቶ የስልጣን እርካቡን ለመርገጥ ሲጣደፍ ፊደል ካስትሮ ገና የ32 ዓመት አፍላ ጎረምሳ ነበር።

ፊደል ካስትሮ የወቅቱን አፍቃሬ አሜሪካ የሆነውን የባፕቲስታ ሥርዓት ገርስሶ እ.አ.አ በ1959 የተቆናጠጠውን ሥልጣን እስከ 2006 እ.አ.አ ድረስ አስቀጠለ፡፡ ሆኖም  በደረሰበት የአንጀት ህመም ምክንያት ስልጣኑን ለታናሽ ወንድሙ እና ለትግል አጋሩ ለራውል ካስትሮ  ለማስተላለፍ ተገደደ።

ፊደል ካስትሮ አጅግ አወዛጋቢ እና አስገራሚ ሰው ነበር። አሜሪካ ፊደል ካስትሮን ለመግደል ያልቧጠጠችው ገደል፣ ያልቆፈረችው ጉድጓድ፣ ያልበጠሰችው ቅጠል፣ ያልማሰችው ስር አልነበረም። ለዚህም ዓላማዋ የተመረዘ የጥርስ ቡሩሽ፣ የተበከለ ሲጃራ፣ በመርዝ ጭስ የታፈነ ስቱዲዮ፣ ስልጡንና ገዳይ ቡድኖችን እና የመሳሰሉትን በማሰማራት ለ638 ጊዜ ልትገድለው ብትሞክርም ሳይሳካላት ቀርቷል።

ካስትሮ ለ47 ዓመታት በሥልጣን ላይ ሲቆይ አሥራ አንድ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ተፈራርቀዋል። ፊደል ካስትሮ ሃያኛው ክፍለ ዘመን ካፈራቸው ታላላቅ መሪዎች ውስጥ ሁልጊዜም ፍትሕ እና ነጻነት ከሚሹት ጋር በመቆም፤ ሁሌም በትክክለኛው የታሪክ ገጽ በመገኘት ግንባር ቀደም ስለመሆኑ ታሪክ መዝግቦለታል። ከኒካራጓ እና ቺሊ እስከ ቬትናም፣ ከፍልስጤም እስከ አልጀሪያ ብሎም ደቡባዊ አፍሪካ ነጻነት ለናፈቃቸው ሁሉ የካስትሮን ያህል ታላቅ ድጋፍ ያደረገ ሌላ መሪ  የለም። በተለይ የአፍሪካ ሀገራት ከኢምፔሪያሊስቶች ጋር ባደረጉት ትንቅንቅ የካስትሮ እና የኩባ ቁርጠኝነት ከጉዳዩ ባለቤቶች ያልተለየ ነበር። ኩባ ለአንጎላ ያደረገችው እጅግ መጠነ ሰፊ እና ከአሥር ዓመት በላይ የዘለቀ ድጋፍ ለዚህ አይነተኛ ማሳያ ነው። ካስትሮ አንጎላ ከፖርቹጋል ቅኝ ግዛት ነፃ ለመውጣት ካደረገችው ተጋድሎ ጀምሮ  ለእነ ናሚቢያ ከአፓርታይድ ተፅዕኖ ነጻ መውጣት ጉልህ እና ቀጥተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። የደቡብ አፍሪካው ታጋይ ማንዴላም ከእስር ሲፈታ ቅድሚያ ከሰጣቸው ጉዳዮች ኩባ ተጉዞ ካስትሮን ማመስገን አንዱ ነበር።

ካስትሮ ለኢትዮጵያም የቁርጥ ቀን ባለውለታ ነው። የኢትዮ — ሶማሊያ ጦርነት እስኪጀመር ድረስ ኩባ እንደ ሶቭየት ሁሉ የሶማሊያ ወዳጅ ነበረች። አሜሪካ ደግሞ በቃኘው ጣቢያ ላይ ያላት ፍላጎት እስኪቀዘቅዝ ድረስ መጠነኛ ርዳታ ለኢትዮጵያ ትሰጥ ነበር። በመሃል የኢትዮጵያ አብዮት ፈነዳ። አብዮቱን ተከትሎ ግን የሃገራችን የወቅቱ መሪዎች ሶሻሊስት ነን ሲሉ አወጁ። ያኔ አሜሪካ እና እንግሊዝ ሶማሊያን ማስታጠቅ ይጀምራሉ። ሶቭየት እና የፊደል ካስትሮዋ ሃገር ኩባ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ዞረው ደርግን ከማስታጠቅ አልፈው ሶቭየት በርካታ የጦር መሣሪያ እና  አማካሪዎች፤  ኩባ ደግሞ ሰራዊት ልካ  ኢትዮጵያን ከሶማሌ ወረራ ታድገዋል።

የካስትሮ እና የኢትዮጵያ ቁርኝት የጀመረው በሚከተለው መልኩ ነበር። መጋቢት 14 ቀን 1969 ዓ.ም ሶማሊያን ለሦስት ቀን የጎበኘው ፊደል ካስትሮ አዲስ አበባ ገባ። አዲስ አበባን ሲጎበኝ ሁለተኛ ጊዜው ነበር። ዓላማውም ያኔ በጦር ሃይል የደረጀችው የጄኔራል ዚያድ ባሬዋ ሶሻሊስታዊት ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሶማሊያ በአብዮት የምትናጠዋን እና በጦር ሃይል ደካማዋን የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ህብረተሰባዊት ኢትዮጵያን እንዳትወር ለማግባባት ነበር።

ካስትሮ ከአዲስ አበባ ወደ ሦስተኛዋ የአካባቢው ሶሻሊስታዊት ሃገር ደቡብ የመን መጋቢት አሥራ አምስት ተጓዘ። በሊቀ መንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት የመልዕክተኞች ጓድ ደግሞ ማምሻውን ተከተለው።

“የደረስነው ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ግድም ነበር። የሶማሊያ መልዕክተኞች ቀድመውን ደርሰዋል” ይላሉ ኮሎኔል መንግሥቱ “ትግላችን” ባሉት መጽሐፍ። ፊደል ካስትሮ እና ምክትላቸው፣ የየመኑ ሶሻሊስታዊ ፓርቲ መሪ አብዱልፈታህ ዑስማኤል እንዲሁም ተከታዮቻቸው  የሸመገሉት ድርድር ያለ ውጤት አበቃ።

ይህ ሁኔታ ቀጣዩ ጦርነት የኢትዮ-ሶማሊያ ብቻ ሳይሆን የኩባ እና የሶማሊያ፤ የደቡብ የመን እና የሶማሊያ ጭምር መሆኑን አረጋገጠ።

ኩባ እና የመን ወታደሮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ሲያዘምቱ ሶቪየት ህብረት ዘመናዊ የጦር መሣሪያዋን አሰብ ላይ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ቋንቋ “ዘረገፈችው።” የኢትዮጵያ እና የኩባ፤ የኢትዮጵያ እና የየመን ወዳጅነት በደም ተሳሰረ።

የሶማሊያ ጦርነት በኢትዮጵያ ፍጹም አሸናፊነት በተጠናቀቀበት ወቅት ቁጥራቸው ወደ 15 ሺህ የሚጠጉ የኩባ ወታደሮች የጦርነቱ ተሳታፊ በመሆን ደማቸውን አፍስሰዋል። ለዚህ መስዋዕትነት እና ወዳጅነት ሲባል ነዉ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አጠገብ የሚገኘው ባለ ቀይ ኮከብ የ”ትግላችን” ሃውልት ለመታሰቢያነት የቆመው።

ካስትሮ እና ኩባ ለኢትዮጵያ የዋሉት ሌላኛው ተጠቃሽ ውለታ የትምህርት እና ስልጠና ዕድል መስጠት ነበር። በዚህም መሰረት በወቅቱ መስፈርቱን ያሟሉ እንዲሁም ወላጆቻቸውን በጦርነቱ ያጡ ከስድስት ሺህ የማያንሱ ኢትዮጵያውያን ወደ ኩባ ሄደው በተለያዬ የሙያ መስክ የመማር እድልን እንዲያገኙ ሆኗል። በርካታ የህክምና ዶክተሮችን ማሰልጠኗ ደግሞ ከሚጠቀሱት አንዱ ነው፡፡ ይህንም ዛሬ ድረስ የያኔዎቹ የኩባ ተማሪዎች ማህበር መስርተው ድላችን ሀውልትን እየጎበኙ ኩባን እና መሪዋን  ያስታውሷቸዋል፤ ያመሰግኗቸዋልም። ልጆቻቸዉ ኩባ ሄደው ተምረዉ ለቁም ነገር ስለበቁላቸው ጥጥ ፈትለው፣ ጋቢ አሠርተው ኩባ ድረስ ዘልቀዉ ለፊደል ካስትሮ ገፀ በረከት ያበረከቱት አንዲት ኢትዮጵያዊት እናት ለዚህ ድንቅ ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ወረራ ነፃ ከወጣች በኋላም ሀገሪቱን ከሌላ ጦርነት የሚታደግ የተማረ እና የሰለጠነ ወታደራዊ መኮንን ይፈለግ ነበርና ፊደል ካስትሮ 500 መኮንኖችን ኩባ ወስዶ የኬሚካል ጦር መሳሪያ መከላከልን ጨምሮ በርካታ ወታደራዊ ስልጠና እንዲያገኙ አድርጓል።

ቁመተ ለግላጋ፣ ፊቱ የማይፈታ ቆፍጣና፣ ደረተ ሰፊ፣ ወንዳ ወንድ፣ መነፅር ከዓይኑ፣ ኋላ ላይ አክ እንትፍ ብሎ የጣለዉ ተስካኖ ሲጃራ ከአፉ የማይለየው ፊደል ካስትሮ አሜሪካ “አምባገነን” እንዳለችው ለጣለችበት ማዕቀብ ሁሉ ሳይንበረከክ እና እጅ ሳይሰጥ ኩባን በክብር መርቷል፤ አይበገሬዉ ፊደል በገጠመው የአንጀት ህመም ምክንያት ለወንድሙ ራውል ካስትሮ ሥልጣኑን ለማዛወር እስከተገደደበት 2006 ድረስ። ከዚያም እ.አ.አ ህዳር 25 ቀን 2016  በ90 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፤ ድንቅ ተግባራቱ ግን ዛሬም፣ ነገም፣ መቼም ድረስ ሲወደሱ ይኖራሉ።

አበቃን፤ ቸር ይግጠመን!

 

ምንጭ፦       -travelerscoffee.ru

-am.hobbygalety.com

-am.sewasew.com።

 

(ጥላሁን ወንዴ)

በኲር የሐምሌ 7  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here