በክረምት ወራት ከጸጋቸው ባለፈ ድንገተኛ አደጋዎችም በብዛት ይከሰታሉ፤ የቅድመ መከላከል ተግባራት ቀድመው ስለማይሠሩ ከፍ ያለ ጉዳትን ሊያስከትሉም ይችላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ባለፉት ዓመታት በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የደረሰው ጉዳት (በዋናነት ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት) አብነት ነው፤ ይህን መነሻ በማድረግ ታዲያ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየሠራ ስለመሆኑ ነው ያስታወቀው፤ ኮሚሽኑ በአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ ያልተማከለ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ሥራ አመራርን ማጠናከር የሁለተኛ ዙር ኘሮጀክት ትውውቅ በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል። የቅድመ አደጋ መከላከል ጉዳይ ደግሞ ትኩረት የተሰጠው ነው።
በአማራ ክልል የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በአውሮፓ ኅብረት ገንዘብ ድጋፍ ያልተማከለ የአደጋ ሥጋት ቅነሣ ሥራ አመራር የማጠናከር ፕሮጀክት ሥራ አሥኪያጅ አዝመራው ምንላርግህ ለበኩር እንደተናገሩት በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ ምክንያቶች የተለያዩ አደጋዎች ይከሰታሉ። ማኅበረሰቡ ከአደጋዎች በራሱ አቅም መወጣት ሳይችል ሲቀር ደግሞ መንግሥት ከተለያዩ ሀገራት ጋር ትብብር በመፍጠር ችግሮችን ለመታደግ ጥረት ያደርጋል። በሀገራችን ለሚከሰቱ አደጋዎች ምላሽ በመስጠት ጉልህ ሚናን ከሚጫወቱት አጋር አካላት መካከል የአውሮፓ ኅብረት አንዱ ስለመሆኑም አንስተዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ ባለፉት ዓመታት በክልሉ በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋ ምክንያት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን የተጋላጭነት መጠናቸውን ለይቶ የአደጋ ሥጋትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎች ሲተገበሩ ቆይተዋል። በተለይም በሰው፣ በመሬት፣ በእንስሳት፣ በሰብል፣ በእፅዋት እና በንብረት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስ ሲሠራ ቆይቷል። የአደጋ ሥጋት የዕቅድ ዝግጅት፣ ትግበራ፣ የቀውስ ምላሽ እና ማቋቋም፣ የአቅም ግንባታ ክፍተት መለየት እና መሙላት እንዲሁም በአደጋ የማይበገር ማኅበረሰብ መገንባት በዋናነት ሲከናወኑ የቆዩ ተግባራት ናቸው።
እንደ አቶ አዝመራው ማብራሪያ ፕሮጀክቱ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ በሆኑ በክልሉ 11 ዞኖች ከ70 በላይ ወረዳዎች የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። በሰሜን ሸዋ በረኸት፣ በደቡብ ወሎ ወረባቦ፣ በሰሜን ወሎ ሀብሩ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ባቲ ወረዳዎች ላይ የበረሃ አንበጣ ተከስቶ በነበረበት ወቅት ለጠፋው የሰብል ውድመት መድረሱ ይታወሳል፤ ለዚህም ፕሮጀክቱ የተተኪ ዘር መግዣ ድጋፍ አድርጓል። በዋግኸምራ፣ በሰሜን ወሎ ሀብሩ፣ በሰሜን ሸዋ ኤፍራታና ግድም፣ ቀወት፣ አንፆኪያ ገምዛ፣ በደቡብ ወሎ አምባሰል እና ተሁለደሬ ወረዳዎች 50 ሺህ 714 የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሚያካትት ሰፋፊ የጎርፍ መቀልበሻ (ማፋሰሻ) ቦይ በማዘጋጀት አደጋዎችን (በዋናነት የጎርፍ) መከላከል እንደተቻለ አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ድጋፍ አድርጓል። ለአብነትም በደባርቅ ወረዳ ትምህርት ቤት ገንብቶ ለማኅበረሰቡ አስረክቧል። በሁለተኛው ዙር ፕሮጀክትም ካለፈው በመማር ጥንካሬዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የአቅም እና የግንዛቤ ክፍተቶችን በመሙላት የተሻለ ሥራ በመሥራት ማኅበረሰቡ ከአደጋ ሥጋት ነፃ እንዲሆን ይሠራል ብለዋል። በቀጣይም የዳሰሳ ጥናት በማድረግ እና በመረጃ ላይ በመመሥረት የአደጋ ስጋት ቅነሳ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ በኮሚሽኑ የአውሮፓ ኅብረት ፕሮጀክት የቴክኒክ አማካሪ አያጣም ፈንታሁን እንዳሉት የሚደርሱ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቀነስ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል። ሂደቱም ያልተማከለ የአደጋ ቅነሳ ሥራ መሆኑን በማንሳት ይህም የአደጋ ስጋት ቅነሳ ሥራው በፌዴራል፣ በክልል፣ በዞን፣ በወረዳ እና በቀበሌ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር እስከ ታችኛው ማኅበረሰብ ድረስ ወርዶ መሥራትን የሚጠይቅ ነው።
ኅብረተሰቡ ለምን በአደጋ ይጠቃል? ምን ስለጎደለው ነው? ምንስ ያስፈልገዋል? የሚሉ ፅንስ ሀሳቦችን በማመንጨት ለኅብረተሰቡ የመፍትሄ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። ከማኅበረሰብ እስከ ቤተሰብ ድረስ የተለያዩ የተጋላጭነት ቅነሳ እና የአይበገሬነት አቅም ግንባታ ሥራዎች እንደሚሠሩም ጠቅሰዋል። በአንደኛው ዙር አራት ሚሊዮን 825 ሺህ ዩሮ (730 ሚሊዮን ብር ገደማ) ተመድቦ በተለይም በክልሉ የምሥራቁ አካባቢዎች በጎርፍ እና በድርቅ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች በርካታ ተግባራት መሠራታቸውን ገልፀዋል። ፕሮጀክቱ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ለክልሉ ሦሥት ሚሊዮን ዩሮ (450 ሚሊዮን ብር) መመደቡን አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሰርካዲስ አታሌ ባለፉት 30 ዓመታት በሀገራችን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ሥራ አደጋው ከደረሰ በኋላ እርዳታ የማድረስ ወይም እሳት የማጥፋት እንደነበር አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት ግን የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ አደጋዎችን መንስኤ ቀድሞ መተንበይ፣ ማወቅ፣ መከላከል እና መቀነስ ላይ ያተኮረ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ሥርዓትን በመዘርጋት አደጋን የሚቋቋም ኅብረተሰብ መገንባት የመንግሥት ዋና ዓላማ ነው ብለዋል።
የሕዝብን የአደጋ ተጋላጭነት ለመቀነስ እና የመቋቋም አቅምን ከፍ ለማድረግ ታሳቢ ያደረጉ ፕሮጀክቶች ሲፈፀሙ መቆየታቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህ መካከልም በአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ ለአምስት ዓመታት ሲከናወን የቆየው ያልተማከለ የአደጋ ስጋት ቅነሳ አሥተዳደር ችግሮችን ሲፈታ ስለመቆየቱ ነው በአብነት ያነሱት።
በክልሉ ዋና ዋና አደጋዎች ምንድን ናቸው? ምን ሲሆን ምን ይከሰታል? ችግሩን ቀድሞ መከላከል ይቻላል? ከተከሰተስ እንዴት እንከላከል? ከአቅም በላይ ሲሆን እንዴት ምላሽ ይሰጥ? የሚሉትን መሠረታዊ ጉዳዮች ቀድሞ መለየት የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው። እንደ ምክትል ኮሚሽነሯ ማብራሪያ የፕሮጀክቱን የመጀመሪያ ዙር አፈፃፀምን በመገምገም እጥረቶችን በማስተካከል፣ ጥንካሬዎችን ደግሞ ለማስቀጠል ይሠራል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በክረምት ወቅት በክልሉ የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊከሰትባቸው የሚችሉ ቦታዎችን በመለየት የቅድመ መከላከል ሥራ መሥራቱን አስታውቋል፡፡
የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ዳይሬክተር ብርሐኑ ዘውዱ ለበኩር ጋዜጣ እንደተናገሩት በክረምት ወቅት በዝናብ መብዛት ምክንያት በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ሊከሰቱ ይችላሉ። አደጋዎችን ለመከላከል ቀድሞ የማጥናት እና መረጃ የማሰባሰብ ተግባራት ተከናውነዋል። በዚህም ለኅብረተሰቡ በቂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ከመስጠት ጀምሮ የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የሚረዱ ሥራዎች መሠራታቸውን አብራርተዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት በክልሉ በጎርፍ አደጋ እና በመሬት መንሸራተት አደጋዎች ተጋላጭ የሆኑ 35 አካባቢዎች ተለይተዋል። በተለይም በጣና ሐይቅ ዙሪያ ያሉ አካባቢዎች በትኩረት ክትትል የሚደረግባቸው ናቸው። በተጨማሪም በርብ እና ጉማራ ወንዞች ላይ ትኩረት ይሰጣል። በእነዚህ አካባቢዎች የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ቢከሰት ሊያደርስ የሚችለውን የጉዳት መጠን በመለየት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የቅድመ መከላከል ሥራ መከናወኑን ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።
በቅድመ ዝግጅት ሥራው መሠረት ተጋላጭ የሆኑ ግለሰቦች ለችግሩ ሰለባ እንዳይሆኑ ቀድሞ ከቦታው የማውጣት ሥራም ይከናወናል። የመረጃ ልውውጡን የሚያሳልጡ ተግባራትም ይከናወናሉ።
የመሬት መንሸራተት እና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰትባቸው በሚችሉ አካባቢዎች ለመጠለያነት የሚያገለግሉ ቤት እና ድንኳን መዘጋጀታቸውን የተናገሩት አቶ ብርሐኑ ከእነዚህ በተጨማሪም በየአካባቢው ባሉ ትምህርት ቤቶች በጊዚያዊነት እንዲያርፉ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ ክረምቱን ተከትሎ የሚመጣ የጎርፍ አደጋን ለመከላከል 145 ሚሊዮን ብር በመመደብ የተለያዩ ቅድመ መከላከል ሥራዎችን እያከናወነ ነው። የጤና፣ ምግብ፣ ውኃ፣ አልባሳት፣ መጠለያ እና መሰል ግብዓቶች እንዲሟሉ ሀብት የማሰባሰብ ሥራም ተከናውኗል።
በዚህ ዓመት ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የሜቲዎሮሎጂ መረጃ ትንበያዎች ያሳያሉ፤ ይህንን መረጃ መሠረት አድርገው ሐሳባቸውን ያካፈሉን አቶ ብርሐኑ ድንገተኛ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ሲከሰት አደጋው በተከሰተበት አካባቢ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ጉዳቱ የከፋ እንዳይሆን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የክረምት ወቅት አደጋዎች ቅጽበታዊ በመሆናቸው ኅብረተሰቡ ሁሌም አደጋው ሊከሰት እንደሚችል አስቦ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም