ሆርሙዝ – የባሕረ ሰላጤው እስትንፋስ

0
74

ኢራን በሰኔ ወር 2017 ዓ.ም ከእስራኤል ጋር አድርጋው በነበረው ጦርነት አሜሪካ ለእስራኤል በማገዝ በሦስት ቁልፍ የኢራን የኒውክሌር ተቋሞቿ ላይ ጥቃት መሰንዘሯ ይታወቃል፤ ይህን ተከትሎም ኢራን የሆርሙዝን ሰርጥ (ባሕርን) የመረከብ መተላለፊያውን  እንደምትዘጋ ዝታ ነበር።

ታዲያ ይህን  የኢራን ዛቻ ተከትሎ በሆርሙዝ የባሕር  ሰርጥ ዙሪያ ያሉ ስጋቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ነበሩ። ምክንያቱም የሆርሙዝ  ሰርጥ በዓለም ላይ  አስፈላጊ የኃይል ማስተላለፊያ  በመሆኑ ነው። ዘ ኢኮኖሚስት  እንዳስነበበው  አንድ   አምስተኛ ያህሉ  የዓለም የነዳጅ የዘይት ፍጆታ  እና ከሩብ በላይ የሚሆነው  ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ በዚህ ጠባብ መስመር  ውስጥ  ይጓጓዛል። የሁለቱ ሀገራት ጦርነት ከመቆሙ በፊት ነዳጅ ዘይት  በበርሜል 78 ነጥብ 50 ዶላር የነበረው ለአጭር ጊዜም ቢሆን ከፍ ብሎ ነበር።  በሲቪል አቪዬሽን ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር።

በባሕር ሰርጡ  ላይ የሚከሰት ማንኛውም ዓይነት መስተጓጎል  በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ አቅርቦት ላይ  ከፍተኛ መዘግየቶችን ሊያስከትል ይችላል፤

ታይም ድረገጽ (time.com) ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው “ወሳኝ የነዳጅ መስመር ” በማለት  የሆርሙዝ ባሕር ወሽመጥን የጠራው የአሜሪካ ኢነርጂ መረጃ አስተዳደር (ኢ አይ ኤ) እንደገለጸው 20 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ዘይት በየቀኑ በባሕር መስመሩ ይጓጓዛል።

ከኩዌት፣  ከኢራቅ፣ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከኳታር እና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚላኩ አብዛኛዎቹ የነዳጅ ምርቶች እንዲሁም ኢራን ወደ ውጭ የምትልካቸው ሌሎች ምርቶች የሚሸጋገሩበት ነው። 20 በመቶ የሚጠጋው የዓለም ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝም  (በአብዛኛው ከኳታር)  ወደ ውጭ የሚላከውም በሆርሙዝ ሰርጥ  በኩል ነው።  በዓመት ወደ ስድስት መቶ ቢሊዮን  ዶላር የሚገመት የነዳጅ ንግድ በባሕር መስመሩ ላይ ይጓጓዛል፡፡

ኢራን የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጡን ሰሜናዊ ክፍል ትቆጣጠራለች፡፡ ይህ መተላለፊያ በየቀኑ ጉልህ የሆነ ዓለም አቀፍ ንግድ ይሳለጥበታል (ያልፍበታል)፡፡ ኢራን መርከቦቹን እንዳያልፉ ልትከለክል ወይም በአካባቢው ያሉ የመርከብ “ኮንቴይነሮችን” እና የዘይት ወይም የጋዝ ታንከሮችን በመያዝ እና በማጥቃት ንግዱን ልታስተጓጉል ትችላለች። ይህም በዓለም የነዳጅ አቅርቦት ላይ ትልቅ ቀውስ ሊፈጥር   ይችላል።

እንደሚታወሰው እ.አ.አ በ2019 ሁለት መርከቦች አንዱ የማርሻል ደሴቶች ባንዲራ ሲውለበለብበት የነበረው እና ሌላኛው ከፓናማ ሲጓዙ ተመትተዋል። በወቅቱ አሜሪካ ለጥቃቱ ኢራንን ተጠያቂ ስታደርግ ቴህራን ግን አስተባብላለች። ከዚህ ጥቃት ከአንድ ወር በፊት ሌሎች አራት ታንከሮች ሁለቱ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ሌሎቹ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ከኖርዌይ የሆኑ በውኃ ውስጥ በተቀበሩ ፈንጂዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ ይህንን ጥቃትም አሜሪካ ከኢራን አያልፍም በሚል ወንጅላት ነበር።

በዋሽንግተን  የኢነርጂ እና የባሕር አደጋዎች ኤክስፐርት ኖአም ሬይዳን እንዳሉት እንደ ኢራቅ ያሉ አንዳንድ ሀገራት ነዳጅን የመሳሰሉ የኃይል ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ በዋናነት በሆርሙዝ ባሕር ሰርጥ  ላይ እንደሚተማመኑ እና ሌሎች ላኪዎች ግን አስተማማኝ አማራጮች እንዳሏቸው ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የባሕር ላይ ኤክስፐርቱ የመተላለፊያ መንገዱ ሙሉ በሙሉ መዘጋት በራሱ ኢራን ላይ ጉዳት ስለሚያደርስ መዘጋቱን የማይመስል ነገር ነው ብለው ያምናሉ።

የሆርሙዝ ባሕር ሰርጥ እንደ ቻይና ላሉ የኢራን አጋሮች በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው የኢራን ዘይት ወደ ቻይና የሚላከው በዚሁ መስመር ነውና፡፡ የባሕር መስመሩን መዝጋት በኢራን እና በባሕረ ሰላጤው ትብብር ምክር ቤት (ሀገራት) መካከል ያለውን ግንኙነትንም ያበላሻል።

ኢራን ኮሽ ባለ ቁጥር የባሕር ወሽመጡን እዘገዋለሁ ማለቷ አዲስ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም እ.አ.አ በ2011 ባሕሩን እንደምትዘጋ ስትዝት ነበር፡፡ በወቅቱ የኢራን ምክትል ፕሬዝዳንት መሀመድ ሬዛ ራሂሚ በምዕራቡ ዓለም በኢራን ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦች በመጨመራቸው ምክንያት ነዳጅ ዘይት በሆርሙዝ ውስጥ እንደማያልፍ ሲገልጹ ነበር። ማዕቀቡ የተካሄደው የኢራን የኒውክሌር አቅምን በተመለከተ ስጋት ስላጫረ ነበር፡፡

የነዳጅ ዘይት ላኪዎች እና አስመጪዎች ሰርጡ በመዘጋቱ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይደርስባቸዋል። እናም የሚፈጠረው የኢኮኖሚ መናጥ (ተጽዕኖው) በጣም ሩቅ እና ሰፊ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

እንደ ዶይቸ ባንክ (የጀርመን ኢንቨስትመንት ባንክ) መረጃ ኢራን የሆርሙዝ የባሕር መተላለፊያውን ከዘጋች ወይም የመርከብ መስመሮች ላይ መስተጓጎል ብትፈጥር የአንድ በርሜል ዘይት ዋጋ ወደ 120 ዶላር ጭማሪ ሊያሳይ ይችላል። የአንድ በርሜል ዋጋ በአሁኑ ጊዜ 75 ዶላር አካባቢ እንደሆነ ልብ ይሏል።

የጂ ካፕታይን የባሕር ላይ የዜና ጣቢያ  መሥራች ጆን ኮንራድ በአዳዲስ ታንከር ግንባታ ላይ ያሉ እንቅፋቶች እና ማናቸውም የምርት ሰንሰለቶች መስተጓጎል ትልቅ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ይናገራሉ።

ኢራን በሆርሙዝ የባሕር ዳርቻ በኩል የሚደረገውን የንግድ እንቅስቃሴ ከከለከለች የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ይጨምራል::  ይህም የተፈጥሮ የእህል ማዳበሪያ በሚፈለገው ፍጥነት ማምረት እንዳይቻል ያደርጋል፡፡

በሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት ምክንያት በጋዝ፣ በዘይት እና በአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ ላይ በሚኖረው ማንኛውም አይነት መስተጓጎል አሜሪካ እና አውሮፓ (በተለይ ሰሜን ምዕራብ አውሮፓ) ተጠቃሚዎች ተጽዕኖው ያርፍባቸዋል። ወሳኝ በሆነው የነዳጅ ማስተላለፊያ የሚከሰት የአቅርቦት ችግር  ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ነዳጅ የሚገዙ የአፍሪካ ሀገራትንም ሊጎዳ ይችላል።

የሰሞኑ የሆርሙዝ ጉዳይ እ.አ.አ በ1980ዎቹ ተካሂዶ ስለነበረው የታንከር ጦርነት ይወስደናል፡፡ በታንከር ጦርነት የነዳጅ ታንከር የጫኑ መርከቦች የኢራን ጦር ዒላማዎች ነበሩ። አሜሪካም በዓለም አቀፉ የባሕር ሕግ መሠረት ከኢራን የሚሰነዘሩ ታንከሮችን ስትከላከል ነበር፡፡ በተለይም የአሜሪካ ባንዲራ የሚያውለበልቡ መርከቦችን ለመጠበቅ ጣልቃ ገብታ ነበር።

ስትራውስ ሴንተር ኦርግ (strausscenter.org) ላይ ያገኘነው መረጃ በበኩሉ እንደሚያትተው እ.አ.አ ከ1980 እስከ 1988 በኢራን እና በኢራቅ መካከል በተደረገው  የታንከር ጦርነት ኢራቅ የኢራንን የመዋጋት አቅም ለማዳከም በመርከቦች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ጦርነቱን ጀመረች፡፡ መጀመሪያ ላይ ወታደራዊ ቁሶችን የጫኑ መርከቦች ላይ ብቻ ነበር ጥቃት የሰነዘረችው፡፡

በኋላ ግን ማንኛውንም የኢራንን ወደ ውጭ የሚላኩ መርከቦችን ማጥቃት ቀጠለች። ኢራንም የኢራቅ የንግድ አጋሮች የሆኑትን መርከቦችን ጨምሮ ኢራቅን ለመደገፍ ብድር የሰጡ ሀገራትን በማጥቃት አፀፋ መለሰች።

በታንከር ጦርነት ወቅት ከተጠቁት መርከቦች ውስጥ 61 በመቶው የነዳጅ ታንከሮች ነበሩ። መጀመሪያ ላይ የታንከር ጦርነት የንግድ መርከቦች 25 በመቶ እንዲቀንሱ አድርጓል፤ የድፍድፍ ዘይት ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪን አስከትሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የታንከር ጦርነት የነዳጅ ጭነትን በእጅጉ እንዳላስተጓጎለ የሚናገሩም አሉ። ጦርነቱ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚያልፉትን መርከቦች ከሁለት በመቶ በላይ ማደናቀፍም አልቻለም። በታንከር ጦርነት ወቅት ኢራን የሆርሙዝ ባሕርን ለመዝጋት በተደጋጋሚ ብትዝትም ዛቻዋን ተግባራዊ አላደረገችውም፡፡ ምክንያቱም ራሷም በባሕሩ ተጠቃሚ በመሆኗ አልዘጋችውም፡፡ ታዲያ መተላለፊያውን ሙሉ በሙሉ ባትዘጋውም መርከቦች ላይ ግን ልክ እንደ ታንከር ጦርነት ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች የሚል ስጋት ነበር፡፡

የባሕረ ሰላጤው ከዚያም አለፍ ሲል የዓለም የንግድ እስትንፋስ እንደሆነ የሚነገርለት የሆርሙዝ ሰርጥ አብዛኛው ታሪኩ ከግጭት ጋር የተቆራኘ ነው፤ የአካባቢው ሀገራት ኩርፊያ ውስጥ ሲገቡም ሰርጡን በመዝጋት ወይም በሰርጡ ላይ ጥቃት እናደርሳለን በሚል ነው የበላይነታቸውን ለማሳየት የሚጥሩት፡፡

ከሰሞኑ ለ12 ቀናት ተካሂዶ ከባድ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመትን ያስከተለው የእስራኤል እና ኢራን ጦርነትም የዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ጦርነቱ ከመጠናቀቁ ቀደም ብሎ ኢራን ሰርጡን እንደምትዘጋ ማስጠንቀቋ አይዘነጋም፡፡

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here