ብራዚል

0
162

በዛሬው ሽርሽራችን 99 በመቶ ዜጎቿ ስደተኞች የሆኑባትን፣ በእግር ኳስ ኮኮቦቿ እና በተፈጥሮ ሀብቷ ዝነኛ የሆነችውን ብራዚል እናስጎበኛችሁ:: ብራዚል ትልቅ ሀገር ናት:: መገኛዋ በደቡብ አሜሪካ ሲሆን ከአህጉሩ በሕዝብ ብዛት 50 ከመቶ በቆዳ ስፋት ደግሞ 47 ከመቶውን ትሸፍናለች:: በደቡብ አሜሪካ ከሚገኙ 12 ሀገራት ከ10ሩ ጋር ድንበር ትዋሰናለች:: ዋና ከተማዋ ብራዚሊያ ስትሆን ትልቋ ከተማዋ ደግሞ ሳኦ ፖሎ ናት::

ብራዚል በቆዳ ስፋቷ በዓለም አምስተኛ ሀገር ስትሆን ስምንት ነጥብ አምስት ሚለዮን ስኩየር ኪሎ ሜትር ትሰፋለች፤ ይህ ማለት ኢትዮጵያን ስምንት እጥፍ በቆዳ ስፋት ትበልጣታለች ማለት ነው፤ በሕዝብ ብዛቷ ደግሞ ከ212 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በመያዝ ሰባተኛ ደረጃን ይዛለች:: ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላኛው የሀገሪቱ ክፍል ለመንቀሳቀስ በስፋት አውሮፕላን ነው ጥቅም ላይ የሚውለው፤ በመሆኑም ብራዚል ከ4000 በላይ አውሮፕላን ማረፊያዎች አሏት:: ይህም ከአሜሪካ ቀጥሎ አያሌ አውሮፕላን ማረፊያ ያላት ሁለተኛዋ ሀገር ያደርጋታል:: በኢኮኖሚያዋም ቢሆን የምትናቅ አይደለችም:: በፈረንጆቹ 2025 አጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ ሁለት ነጥብ አንድ ትሪሊዮን ዶላር መሆኑን የሮይተርስ ዘገባ ያሳያል::

በብራዚል ሁሉም ዓይነት የዓለማችን ሰው ይገኛል ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል:: የተለያዩ ሀገር ዜጎች በብራዚል ይገኛሉ:: ለአብነት በብራዚል የሚኖሩ ሌባኖሳዊያን  እዛው ሌባኖስ ካሉት ቁጥር ይበልጣል:: ከብራዚል ዜጎች መካከል 45 ከመቶው ፓርዶ በመባል የሚታወቁት የነጭ እና የጥቁር እንዲሁም ሌሎች ነገዶች ቅልቅል የሆኑ ናቸው:: ነጮች ደግሞ 43 ከመቶውን ድርሻ ይይዛሉ::  ጥቁሮች 10 ከመቶውን ይሸፍናሉ:: ነባር ብራዚላውያን ደግሞ ዜሮ ነጥብ አራት ከመቶ ብቻ ናቸው:: የምሥራቅ እስያ ሰዎች ቁጥር ከነባር ብራዚላዊያን ቁጥር ይበልጣል:: በሀገሪቱ 85 ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ የክርስትና እምነት ተከታይ ነው:: ፖርቹጋልኛ የፖርቹጋል ብሔራዊ ቋንቋ ነው:: ይህን ቋንቋ የሚናገሩ ሕዝቦች በብዛት ያሉት ግን ፖርቹጋል ሳይሆን ብራዚል ነው:: ፖርቹጋል በተናጋሪዎች ብዛት በገዛ ቋንቋዋ በብራዚል በ20 እጥፍ ትበለጣለች::

የደቡብ አሜሪካ ሀገራት ከብራዚል በስተቀር በስፔን ቅኝ ግዛት ወድቀዋል:: ብራዚል ግን በፖርቱጋሎች ነው ቅኝ የተገዛችው:: ፖርቹጋሎች ብራዚል ከመድረሳቸው ከ1494 እ.አ.አ በፊት የተወሰኑ ነባር ጎሳዎች ይኖሩ ነበር፤ ቁጥራቸውም ወደ ሰባት ሚሊየን ገደማ  ይገመታለሰ:: ብራዚል የሚለው ስያሜ የተወሰደው ከፖርቹጋልኛ ቋንቋ ነው:: በፖርቹጋልኛ ፓው ብራዚል ወይም የብራዚል ዛፍ የሚባል በባሕር ዳርቻዎች የሚበቅል ተክል አለ፤ ከእሱ መነሻ በማድርግ ብራዚል የተሰኘውን መጠሪያዋን አገኘች::

ብራዚል በዓለማችን ላይ የሚገኙ በጎ ነገሮችን በመኮረጅ የራሷ ማድረግ እና አንደኛ መሆንን ታውቅበታለች:: ለአብነት እግር ኳስ የተወለደው በእንግሊዝ ቢሆንም ከእንግሊዝ በላይ በእግር ኳስ ስሟ የምትነሳው ብራዚል ናት:: ሌላው ደግሞ ቡና መገኛው ኢትዮጵያ ቢሆንም የዓለማችን ቁጥር አንድ ቡና አምራች ሀገር ብራዚል ናት:: የቡና መገኛ የሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዓለም የምታቀርበው የቡና መጠን አራት ከመቶ ብቻ ሲሆን ብራዚል ግን 40 ከመቶውን ታቀርባለች:: ከ300 ዓመታት በፊት ብራዚል አንድ ዘለላ የቡና ዛፍ አልነበራትም:: የፖርቹጋል ወታደራዊ መኮንን የነበረው ሌፍትናንት ጄኔራል ፍራንሲስኮ ቫሊኒ በ1719 እ.አ.አ ፍሬንች ጉያና የተባለች ሀገር ለዲፕሎማሲ ሥራ ሄዶ ሲመለስ በርክት ያሉ የቡና ፍሬዎችን እና ችግኞችን ይዞ ተመለሰ:: ያም ለብራዚል ገበሬዎች ተከፋፍሎ እንዲዘራ ተደረገ፤ በዚህም ዛሬ ብራዚል ቀዳሚ የቡና አምራች ሀገር መሆን ችላለች::

በብራዚል ጣሊያናዊያን በብዛት ይገኛሉ፤ አጠቃላይ ቁጥራቸውም 31 ሚሊዮን ይደርሳል:: ይህ የሕዝብ ቁጥር የብራዚልን 15 በመቶ ድርሻ ይይዛል:: የጣሊያናዊያን ቁጥር መብዛትም ለምን? የሚል ጥያቄ ሊያጭር ይችላል:: መልሱም እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1888 ባርነት በብራዚል በሕግ ታገደ:: በዚህ ጊዜ የብራዚል የቡና ማሳዎች ከፍተኛ የሰው ኃይል እጥረት ገጠማቸው:: ለዚህም እንደ መፍትሔ የተወሰደው ከአውሮፓ ወደ ብራዚል የጉልበት ሠራተኛ ማስገባት ነበር:: በዚህ ጊዜ የደቡብ ጣሊያን ሕዝብ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነበር፤ አያሌ ድሆች የሚገኙበትም ነበር:: እናም ብራዚል እዛው ሀገራቸው ድረስ ሄዳ የትራንስፖርት ችላ ብዙ ጉልበት ሠራተኞችን ወሰደች:: እነዚህ ጣሊያናዊያን በዝተው ተባዝተው ዛሬ ላይ በብራዚል ቀዳሚውን ቁጥር ይዘዋል ማለት ነው:: ሶሪያዊያን፣ ጀርመናዊያን እና ሊባኖሳዊያንም ለሥራ ወደ ብራዚል አቅንተው ቁጥራቸው በዝቷል::

የብራዚል ምግብ እንደየአካባቢው ይለያያል፣ ይህም የሀገሪቱን ተወላጆች እና የስደተኛ ህዝቦች መጋመድን ያሳያል። ይህም ክልላዊ ልዩነቶችን በመጠበቅ የሚታወቅ ብሔራዊ ምግብ ፈጥሯል። በጣም ከታወቁት የብራዚል ምግቦች መካከል የሀገሪቷ ብሔራዊ ምግብ ተብሎ የሚታሰበው ፌጆአዳ (ስጋ፣ የተቀቀለ ባቄላ የያዘ) እና ቹራስኮ (የተጠበሰ ስጋ) ይጠቀሳሉ:: ሌሎች የክልል ምግቦች ቤይጁ፣ ፌኢጃኦ ትሮፔሮ፣ ቫታፓ፣ ሞኬካ፣ ፖሌንታ (ከጣሊያን ምግብ) እና አካራጄ (ከአፍሪካ ምግብ) ይካተታሉ። ብሔራዊ መጠጣቸውም ቡና ነው:: ካቻካ የብራዚል የአልኮል መጠጥ ነው። ካቻካ ከሸንኮራ አገዳ ነው የሚሠራው።

በብራዚል ውስጥ በጣም ታዋቂው ስፖርት እግር ኳስ ነው። የብራዚል የወንዶች ብሄራዊ ቡድን በፊፋ የዓለም ደረጃ ከዓለም ምርጥ ከሚባሉት ተርታ የተቀመጠ ሲሆን በዓለም ዋንጫ ውድድር አምስት ጊዜ በተከታታይ ክብረወሰን በሆነ መልኩ አሸንፏል። በዘር የተለያዩ ብራዚላዊያን ጎሳዎችን አጣብቆ ከያዛቸው ነገር መካከል እግር ኳስ አንዱ ነው:: ብራዚላዊያን ብሔራዊ ቡድናቸው ጨዋታ ካለው በአንድ ላይ ቢጫ ማሊያቸውን (መለያቸውን) አድረገው በሕብረት ቡድናቸውን ይደግፋሉ:: እግረ ኳስ ለብራዚል በየዓመቱ ቢሊዮን ዶላሮችን ያስገኝላታል:: ወደ ውጪ የሚልኳቸው ተጫዋቾች፣ የብሮድካስት ስርጭቶች፣ ማስታወቂያዎች፣ የስፖርት ትጥቆች ሽያጭ እና ከሌሎች ገቢ ታገኛለች:: መረብ ኳስ፣ የቅርጫት ኳስ፣ የመኪና እሽቅድምድም እና ማርሻል አርት ብዙ ተመልካቾች አሏቸው።

የብራዚል ቱሪዝም እያደገ ያለ ዘርፍ እና ለበርካታ የሀገሪቱ ክልሎች ኢኮኖሚ ቁልፍ ነው። ሀገሪቱ በ2015 እ.አ.አ ስድስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ጎብኝዎች ነበሯት፤ ከዓለም አቀፍ ጎብኝዎች አንፃር በደቡብ አሜሪካ ዋና መዳረሻ ስትሆን በላቲን አሜሪካ ከሜክሲኮ ቀጥላ ሁለተኛ ናት። ከዓለም አቀፍ ቱሪስቶች የተገኘው ገቢ በ2010 እ.አ.አ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። እንደ እውሮፓዊያን አቆጣጠር  በ2011 አምስት ነጥብ አራት ሚሊየን ሕዝብ የጎበኛት ሲሆን ስድስት ነጥብ  ስምንት ቢሊየን ዶላርም አግኝታለች:: በዓለም የጎብኝዎች መዳረሻዎች ዝርዝር ውስጥ፣ በ2018 እ.አ.አ ብራዚል 48ኛዋ በብዛት የተጎበኘች ሀገር ነበረች።

የተፈጥሮ አካባቢዎቿ በዋነኛነት ጎብኝዎችን ይስባሉ:: መዳረሻዎቿ አካባቢ ጥበቃ መር እና ከመዝናናት ጋር የተያያዙ ናቸው:: በዋነኛነት ፀሐያማ የአየር ንብረቷ እና ባህር ዳርቻዎቿ እንዲሁም የጀብዱ ጉዞ እና የባህል ቱሪዝም ዋናዎቹ ጥቅሎች ናቸው። በጣም ተወዳጅ ከሆኑት መዳረሻዎች መካከል የአማዞን የዝናብ ደን፣ የባህር ዳርቻዎች እና ደኖች፡- በሰሜን ምስራቅ ክልል፣ በማዕከላዊ -ምዕራብ ክልል ውስጥ ያለው ፓንታናል፣ በሪዮ ዴጄኔሮ የባህር ዳርቻዎች እና ሳንታ ካታሪና ፣ የባሕል ቱሪዝም ሚናስ ጌራይስ እና ወደ ሳኦ ፓውሎ የንግድ ጉዞዎች ይጠቀሳሉ::

በ 2024 የጉዞ እና ቱሪዝም ውድድር መሠረት ለቱሪዝም እና ለንግድ ሥራ  ተፈላጊ ከሆኑ ሀገራት አንፃር ብራዚል በዓለም ደረጃ 26ኛ ደረጃን በመያዝ ከአሜሪካኖቹ (ሰሜን አሜሪካ እና ላቲን) ከካናዳ እና አሜሪካ ቀጥላ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች ሲል ቪዚት ብራዚል ድረ ገጽ አትቷል። የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ለብራዚል የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ቁልፍ የገበያ ክፍል ነው። እ.አ.አ. በ2005 51 ሚሊዮን የብራዚል ዜጎች ጉዞ አድርገዋል:: በ2023 ዋና የመዳረሻ ግዛቶች ሳኦ ፓውሎ፣ ሪዮ ዴ ጄኔሮ እና ሪዮ ግራንዴ ዶ ሱል ነበሩ። ከቱሪዝም ገቢ አንፃር በክፍለ ሀገር ከፍተኛ ገቢ ያስመዘገቡት ሳኦ ፓውሎ እና ባሂያ ነበሩ።

በብራዚል ከሕክምና ምክር ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የቀዶ ሕክምና ድረስ በነጻ ይሰጣል:: እነዚህን ሕክምናዎች ቤሳቤስቲን ሳያወጡ ማግኘት ይችላሉ፤ የመንግሥት ሆስፒታል ወይም ጤና ጣቢያ ከሆነ ደግሞ የብራዚል ዜጋ መሆን አይጠበቅብዎትም:: ገንዘብ ከተጠየቁ የግል ክሊኒክ ወይም ሆስፒታል ነዎት ማለት ነው::

ሰፊው የአማዞን ደን ክፍል (60 በመቶው) በብራዚል ይገኛል:: አማዞን ጫካ ውስጥ ብቻ 400 አይነት ጎሳዎች ይኖራሉ፤ ቁጥራቸውም አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሲሆን ከአጠቃላይ የሀገሪቱ የሕዝብ ቁጥር ዜሮ ነጥብ ስምንት ብቻ ነው:: የዓለም ሳንባ የተባለውን አማዞንን ጠብቀው እስከዛሬ ያቆዩልን 400ዎቹ የብራዚል ጎሳዎች ናቸው:: አማዞን 16 ሺህ ዝርያ ያላቸው 390 ሚሊየን ዛፎችን የያዘ ነው:: አማዞን ውስጥ ማናኦስ የሚባል የዘነጠች ከተማስ እንዳለች ያውቃሉ? ከተማዋ በ1969 እ.አ.አ ነው የተመሠረተችው:: ሁለት ሚሊዮን ሰዎች ይኖሩባታል:: የብራዚል ሽርሽራችንን በዚሁ እናብቃ:: ሰላም!

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here