ግብርን ባግባቡ መሰብሰብ እና ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

0
107

ግብር የመንግሥት የልማት እና የማኅብራዊ አገልግሎት ዕቅዶች ማስፈጸሚያ፣ የሀገር ሉዓላዊነት ማስከበሪያ፣ የመንግሥት ጥንካሬ መለኪያ፣ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ እና የኅብረተሰቡን ችግሮች መፍቻ ቁልፍ መሣሪያ ነው። ግብር ሀገርን እና ሕዝብን የሚያስቀጥል እስትንፋስ ነው።

አማራ ክልል 408 ሺህ 171 የደረጃ “ሀ”፣ “ለ”፣ እና “ሐ” ግብር ከፋዮች አሉት። 116 ሺህ የሚሆኑ ደግሞ የኪራይ ገቢ የሚከፍሉ የማኅብረሰብ ክፍሎች እንዳሉ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ መረጃ ያመለክታል። 92 ሺህ የሚሆኑት የሊዝ ገቢ ከፋዮች እንደሆኑም ተገልጿል።

ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ግብር ከፋይ አርሶ አደሮች እንዳሉም ነው የቢሮው መረጃ የሚያሳየው። በአጠቃላይ በአማራ ክልል ከአራት ሚሊዮን 800 ሺህ በላይ ግብር ከፋይ መኖሩን ቢሮው አመልክቷል።

ይሁን እንጂ ክልሉ ለሀገር ከሚያበረክተው የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ አንጻር የሚሰበሰበው የግብር ገቢ አነስተኛ መሆኑን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ክብረት ሙሀሙድ ተናግረዋል።

ቢሮው በ2017 በጀት ዓመት ከመደበኛ ግብር 56 ነጥብ 15  ቢሊዮን ብር እና ከከተማ አገልግሎት ከ15 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በድምሩ 71 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እንደነበር የቢሮው ኃላፊ ገልጸዋል። እስካሁንም 58 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡ ተነግሯል።

በገቢ አሰባሰብ ዙሪያ ያለውን አቅም አሟጦ ከመሰብሰብ አኳያ አሁንም ችግሮች እንዳሉ የተናገሩት አቶ ክብረት ሙሀሙድ ባለፈው ዓመት በጸጥታ ችግር ምክንያት ከዕቅድ በታች መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡ አመራሮች እና ባለሙያዎች ጥቃቶችን በመፍራት ደፍሮ ግብር ለመሰብሰብ ውስንነቶች እንደነበሩም አስታውሰዋል።

የገቢ አሰባሰቡን የተሻለ ለማድረግ አሠራርን ማዘመን፣ የታክስ ማስከፈያ ምጣኔን ማሻሻል፣ ግብር ከፋዮችን በደረጃቸው ማስከፈል፣ ያልተዳሰሱ የገቢ መሠረቶችን ማስፋት እና ከልማት ድርጅቶች ገቢ በመሰብሰብ ዕቅዱን እንደሚያሳኩ አቶ ክብረት ተናግረዋል። የታክስ አሠራሩን ለማዘመን የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ቤታቸው ሆነው ግብራቸውን እንዲከፍሉ የኤሌክትሮኒክስ ታክስ አስተዳደር ዘዴ(ኢ-ታስ የዲጂታል አሠራር) ዘርግቷል።

አዲሱ አሠራር የመደበኛ እና የከተማ አገልግሎት ገቢ አሰባሰብ ሂደትን በማዘመን የሕግ ተገዥነትን ያሳድጋል፤ የአገልግሎት አሰጣጥንም ያሻሽላል ነው የተባለው።

የአማራ ክልል የገንዘብ ፍላጎት በተለያዩ ድርጅቶች ልገሳ (ብድርን ጨምሮ) እና ድጋፍ (በዋናነት በፌዴራል መንግሥት ድጎማ) የተንጠለጠለ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ተናግረዋል። በአማራ ክልል ከጠቅላላ ምርቱ ያነሰ የግብር ገቢ እየተሰበሰበ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

ከችግር አዙሪት መውጣት ያልቻልንበት ምክንያትም ተገቢውን የግብር ገቢ በወቅቱ ባለመሰብሰቡ ነው ተብሏል።

ችግሮች የሚፈቱት ግብርን በፍትሐዊነት መሰብሰብ ሲቻል መሆኑን አቶ አረጋ ጠቁመዋል። ግብር ኢንቨስትመንትን ያበረታታል፤ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የምንፈታበት መሳሪያ ነው ብለዋል አቶ አረጋ ከበደ።

ዕቅዱን ለማሳካት ጠንካራ የመንግሥት አስተዳደር፣ የታክስ አስተዳደር እና የሕግ ማስከበር መኖር አለበት፤  ግብር የማይሰውር እና የማያጭበረብር ግብር ከፋይ መኖር እንዳለበትም ርዕሰ መስተዳደሩ አስገንዝበዋል።

የመንግሥት ጥንካሬ ከሚለካባቸው ዋነኛ ጉዳዮች መካከል ሰላምን ማስከበር፣ ግብርን ማስከፈል እና ማስተዳደር መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳደሩ ከግብር በሚገኘው ገቢ የልማት ፍላጎታችንን እናሳካለን ብለዋል አቶ አረጋ።

ግብር ቁልፍ የገንዘብ ምንጭ እና የሁል ጊዜ ሥራ በመሆኑ ሁሉም ትኩረት አድርጎ መሥራት እንዳለበትም ተነግሯል።

ማኅብረሰቡም ግብር ለሀገር ግንባታ እና ለሕዝብ ሰላም መሆኑን በመረዳት ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ጭምር አሳስበዋል – ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ።

የ2017 የግብር ዘመን የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች አከፋፈል ከሐምሌ 01/2017 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም ይቆያል። የንግድ ሥራ እና የኪራይ ግብር ከፋዮች ደግሞ እስከ ጥቅምት 30/2018 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here