የተሻሻለዉ አዋጁ የሕዝብን ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ  ተጠቆመ

0
158

የተሻሻለው የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 1324/2016 ከነባሩ ሕግ በተሻለ የመሬት ባለይዞታዎችን መብት ያጎናፀፈ መሆኑ ተገለፀ።

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ በተሻሻለው የመሬት ረቂቅ አዋጅ ላይ ከከተማ ልማት ክላስተር መሪዎች ጋር ውይይት አድርጓል። በውይይቱ የተሻሻሉ ሃሳቦችን ያቀረቡት የአማራ ክልል መሬት ቢሮ የሕግ ባለሙያ አዲሱ ሞላ እንዳሉት   ረቂቅ ሕጉ የፌዴራል የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅን ባልተቃረነ፣ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ ያገናዘቡ ጉዳዮችን ያካተተ  በተለይም ለመሬት ባለቤቶች ተጠቃሚነትን  ያረጋገጠ፣ ለተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ለሴቶች እና ለአካባቢ ጥበቃም  ተገቢውን ትኩረት የሠጠ መሆኑን  ገልጸዋል።

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኃላፊ ሲሳይ ዳምጤ   አዲሱ ረቂቅ አዋጅ የክልሉን የወደፊት አቅጣጫ የሚያመላክት መሆኑን ገልፀው በከተማ ዙሪያ ያሉ መሬቶችን መንግሥት ለተለያዩ የልማት ሥራዎች በማንኛውም ጊዜ ከፈለገ ተመጣጣኝ ካሳ ከፍሎ የማንሳት ሥልጣን ስላለው አዋጁ በከተሞች ዕድገት እና በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ ችግር እንደማያመጣ ገልጸዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ/ር) ረቂቅ አዋጁ ከነባሩ አዋጅ በርካታ የተለዩ ነገሮችን የያዘ መሆኑን ጠቁመዋል።

አዋጁ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት ዕቅዱን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ እና ረቂቅ አዋጁ የሕዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ፣ የቴክኖሎጅ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ፣ የመሬት አጠቃቀምን የሚያሻሽል መሆኑንም ገልጸዋል።

አዋጁ በየጊዜው በሚወጡ ደንቦች እና መመሪያዎች እንዲሻሻሉ ዕድል የሚሠጥ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል  ያሉት አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ/ር) በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተለያዩ ተቋማት እና የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይቶች እንደተደረገበት እና ግብዓቶችም እንደተሰበሰቡ ጠቁመዋል። በመሆኑም ረቂቅ አዋጁ የሕዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ  እንደሚሆን ነው የገለፁት።

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here