የጥርስ አፈጣጠር እና ጤና አጠባበቅ

0
253

“ሕጻናት ጥርስ ሲያበቅሉ በነጭ ሽንኩርት ድዳቸውን ማሸት ጥሩ ነው፤ ድድ ለሚደማበት ሰው ንቅሳት ጥሩ ነው፤ የጥርስ ሳሙና የሚሠራበት ኬሚካል ይጎዳል፤ ጥርስ ማሳጠብ የጥርስ ሽፋንን ያሳሳል …” እነዚህን እና መሰል በውስጥ ንባብ  የምታገኟቸው ምክረ ሐሳቦች ስለ ጥርስ ጤና አጠባበቅ ሲወሳ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በአንዳንድ ሰዎች በተደጋጋሚ የሚነሱ (የሚባሉ)ናቸው::

ታዲያ እኛም በጉዳዩ ዙሪያ የሚመለከተው ባለሙያ ምላሽ ይስጥበት በሚል በባሕር ዳር ከተማ ከዶ/ር ፍስሃ ስፔሻሊቲ የጥርስ ሕክምና ክሊኒክ ቺፍ ዴንታል ሰርጅን ከሆኑት ዶ/ር ፍስሃ አምብሉ ጋር ቆይታ አድርገናል::

ባለሙያውም “ስለ ጥርስ አጠቃላይ አፈጣጠር ግንዛቤ ቢሰጥ ጥሩ ነው” በማለት ነበር ሐሳባቸውን የጀመሩልን:: ዶ/ር ፍስሃ እንዳሉት የሰው ልጅ ጥርስ በአማካይ በእርግዝና ሰዓት ከስድስተኛው ሳምንት ጀምሮ የመፈጠር ሂደቱ ይጀምራል፤ ከተወለድን በኋላ ደግሞ በትክክለኛው በአማካይ ጊዜው ከስድስት ወር ጀምሮ የታችኛው የፊት ለፊቱ ጥርስ መብቀል ይጀምራል::

 

እንስሳትን ጨምሮ የጥርስ አበቃቀል ሂደት በሦስት ይከፈላል:: በጥርስ አበቃቀል ሂደት በሕይዎት ዘመናቸው አንድ ጊዜ ጥርስ አብቅለው ያንን ጥርስ እስኪሞቱ ድረስ የሚጠቀሙ አንዳንድ እንስሳት ያሉ ሲሆን ‘ሞኖ ፋይደንት’ ይባላሉ:: አንድ ጊዜ አብቅለው ያንን ያበቀሉትን ጥርስ ቀይረው በሌላ በሁለተኛ የሚጠቀሙ የሰው ልጅ የሚካተቱበት ‘ባዮ ፋይደንት’ የሚባል የአበቃቀል ሂደት አለ::  ሦስተኛው ደግሞ  በየጊዜው አዳዲስ ጥርስ የሚያበቅሉት ‘ፖሊ ፋይደንት’ የሚባሉ እንስሳት ናቸው::

የሰው ልጅ በሁለት ዙር (ባዮ ፋይደንት) ጥርስ ያበቅላል:: የምናበቅለው የመጀመሪያው ጥርስ የወተት ጥርስ ወይም የሕጻናት ጥርስ ይባላል:: ይህ በጤናማ ሁኔታ ከስድስት ወር ጀምሮ የሚበቅል ሲሆን አንዳንዴ እንደየሕጻናቱ የዕድገት ሁኔታ ከፈጠነ ከአራት ወር ጀምሮ ይበቅላል:: እንደ ሕጻናቱ የዕድገት ውስንነት ደግሞ አንዳንዴ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ሳያበቅሉ ሊቆዩ ይችላሉ::

 

የወተት ጥርስ ሙሉ በሙሉ በቅሎ የሚያልቀው ሁለት ዓመት ተኩል ዕድሜ ላይ ሲደረስ ነው:: ስለዚህ አንድ ሕጻን ልጅ በሁለት ዓመት ተኩል ዕድሜው ከላይኛው 10  ከታችኛው 10 በአጠቃላይ ሃያ የወተት ጥርሶች ሊኖሩት ይገባል:: ይህ የሚሆነው ታዲያ ጤነኛ የአበቃቀል ሂደት ሲኖር ነው:: እነዚህ የወተት ጥርሶች ሳይወልቁ ይቆዩና ከስድስት ዓመት ጀምሮ በአዲስ በቋሚ ጥርስ መተካት ይጀምራሉ:: ይህ ቋሚ ጥርስ የምንለው ከስድስት ዓመት ጀምሮ መብቀል ይጀምርና እስከ 13 ወይም እስከ 14 ዓመት(ዕድሜ) ድረስ ያሉት ሃያዎቹ የወተት ጥርሶች ተቀይረው በሌላ አዲስ  ጥርስ ይተካሉ::

የመጨረሻዎቹ  ̋ዊዝደም ̋ ጥርስ የሚባሉት ደግሞ ከ17 እስከ 25 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ይበቅላሉ:: በመሆኑም የሰው ልጅ በሕይዎት ዘመኑ ሃያ የወተት ጥርስ  እና ቋሚ 32 ጥርሶችን ያበቅላል:: በአጠቃላይ የሰው ልጅ በዘመኑ በጤነኛ አፈጣጠር  52 ጥርሶች ይኖሩታል ማለት ነው::

ከዚያ ውጪ በጤና እክል ምክንያት የማነስ እና የመብዛት ነገር ሊኖር እንደሚችል የጠቆሙት ዶክተር ፍስሃ ለአብነትም በ25 ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሰው ከጤነኛ የጥርስ አበቃቀል ሲወጣ 33 ወይም 34 ጥርሶች ሊኖሩት እንደሚችል ገልጸዋል::

 

ዶ/ር ፍስሃ እንዳሉት  በአንዳንድ ሁኔታ ሕጻናት ጥርስ አብቅለው ሊወለዱ ወይም ደግሞ በተወለዱ በአንድ ወር ውስጥ ጥርስ ሊያበቅሉ ይችላሉ:: በመሆኑም ወላጆች ይህ ነገር ሲያጋጥማቸው መደንገጥ እንደሌለባቸው እና በሕክምናው ዓለም የተለመደ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል::

ወላጆችም ሆኑ ማሕበረሰቡ ሕጻናት ጥርስ አብቅለው ሲወለዱ ወይም በተወለዱ በፍጥነት ጥርስ ማብቀል ሲጀምሩ  ከመጥፎ ዕድል ጋር ማገናኘት የለባቸውም:: ይህን ተከትሎ ከሚፈጸም የግግ ማስፈልፈል ተግባር መታቀብ አለባቸው:: ግግ ማስፈልፈል በፍጹም ሊተገበር የማይገባ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊት ነው::

ባለሙያው እንዳስገነዘቡት ሕጻኑ በአንድ ወሩ ውስጥ ጥርስ አብቅሎ  የእናቱን ጡት የማይነክስ፣ እንዲሁም ድዱ ጋር ጠበቅ ብሎ የበቀለና  የማያስቸግር ከሆነ የሕክምና ባለሙያ አይቶት ሳይነቅል ሊተወው ይችላል:: ከዚያ ውጪ ስለት ሆኖ የእናቱን ጡት የሚነክስ እና የላላ አይነት ከሆነ ሊነቀል እንደሚችል በመጠቆም ለዚህም ባለሙያን ማማከር እንደሚገባ ተናግረዋል::

 

ሕጻናት ጥርስ ማብቀል ሲጀምሩ ለምን ይታመማሉ? እንዳያማቸውስ ድዳቸውን በነጭ ሽንኩርት ማሸት  አለብን ወይ? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም ሲመልሱ፡- ከጥርስ ማብቀል ሂደቱ ጋር ተያይዞ ጥርሱ ድዳቸውን በስቶ በሚወጣበት ጊዜ የሚፈጠር ግፊት ይኖራል:: ይህም ድዳቸው ላይ ሕመም ሊፈጥር ስለሚችል  እጃቸውን እና የሚያገኙትን ዕቃ ወደ አፋቸው ሊልኩ ይችላሉ:: በሚነካኩት ጊዜም ምራቃቸውና ለሃጫቸው ይዝረበረባል፤ እንዲሁም ድዳቸው ደም መቋጠር ይታይበታል:: በዚህ ጊዜ በቀላሉ ብክለት ይፈጠርና  ለኢንፌክሽን (ለቁስለት) ይዳረጋሉ:: ኢንፌክሽን ከተፈጠረ ደግሞ የሰውነታቸው ሙቀት ጨምሮ ሕመም ይኖራቸዋል ማለት ነው::  ታዲያ የሕመም ስሜቶቹ የሚጨምሩ ከሆነ ባለሙያ ጋር ወስዶ ማሳየት ይገባል፤ ከዚያ ውጪ  እንዳያማቸው በሚል ድዳቸውን በነጭ ሽንኩርት ማሸት የሚባለው በሕክምናው ስለማይደገፍ ከዚህ ድርጊት መቆጠብ እንደሚገባ ነው የገለጹት::

ለባለሙያው የጥርስ ሕመም እንዴት ይከሰታል ብለንም ጥያቄ አንስተንላቸዋል፤ እርሳቸውም ጥርሳችን በመሠረታዊነት ሦስት ክፍሎች እንዳሉት በማብራራት ይጀምራሉ:: የመጀመሪያው ውጫዊው እና በዓይናችን የምናየው ነጩ ክፍል ኢናሜል (enamel) ይባላል:: ይህም ከአጥንታችን በላይ ጠንካራው የሰውነታችን መዋቅር ነው:: ለመቦርቦርም ረዥም ጊዜ ነው የሚወስድበት::

 

ሌላው በዓይናችን የማናየው ከኢናሜል  ሥር ያለው የጥርሳችን ክፍል   ̋ዴንታይን ̋(dentine) የሚባለው ክፍል ሲሆን ጠንካራ ቢሆንም ጥንካሬው እንደ ኢናሜል አይደለም:: ሦስተኛው የጥርስ ክፍል  ቱዝ ፐልፕ (tooth pulp)  የሚባል ሲሆን የጥርሳችን የውስጠኛው ሽፋን ነው፤ በውስጡም ነርቮች፣ የደም ሥሮች እና ተያያዥ ህዋሳት (ሴሎች) አሉት::

ታዲያ ጥርሳችን መቦርቦር ሲጀምር መጀመሪያ የሚቦረቦረው ኢናሜሉ ሊሆን ይችላል:: ኢናሜሉ ሲቦረቦር ብዙ ጊዜ የሕመም ስሜት አይኖረውም:: የሕመም ስሜት የሚጀምረው ሁለተኛው ክፍል ሲቦረቦር ነው:: መቦርቦሩ ወደ ላይኛው የዴንታይን ክፍል ሲገባ ቀዝቃዛ፣ ትኩስ፣ ጣፋጭ እና ሎሚን የመሳሰሉ ነገሮች ሲያርፉበት በቀላሉ የሕመም ስሜት (ሴንሴቲቭ) ይፈጠራል::

 

ዴንታይን የተባለው የጥርስ ክፍል ከኢናሜሉ ጋር ሲወዳደር በአንጻራዊነት ጥንካሬው ደካማ ስለሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይቦረቦራል:: በመሆኑም እዚህ ቦታ ላይ እያለ የተቦረቦረው ጥርሳችን ቢሞላ በቀላሉ መመለስ ይቻላል::  ይህ ካልተደረገ ግን ባክቴሪያው ወደ ሦስተኛው የጥርስ ክፍል ይገባና የነርቭን እና የደም ሥርን እንዲሁም የጥርሳችንን የመጨረሻ ሥር በማጥቃት ይጎዳናል:: ኢንፌክሽንም ይፈጠራል:: በዚህ ጊዜ የሕክምና አማራጩም ይቀየራል ማለት ነው:: የተቦረቦረውን ከመሙላት ወደ መነቀል ይሸጋገራል::

 

ጥርስ የሚቦረቦረው በተገቢው መንገድ ሳይጸዳ ሲቀር ነው:: አፋችን ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ጎጂና ጠቃሚ ባክቴሪያዎች ስለሚኖሩ ጎጂ ባክቴሪያዎች በጥርሳችን መካከል ያሉ የምግብ ልመቶችን በመጠቀም አሲድ ይለቃሉ:: የሚለቀቀው አሲድም  ጥርሳችን ላይ በሚለጠፍበት ጊዜ የጥርሳችንን ሽፋን  (ሌየር) አሳስቶ ጥርሳችን እንዲቦረቦር ያደርገዋል::

ስለዚህ የጥርስ ሕመምን የምንሰማው በሁለተኛው የጥርሳችን ክፍል ላይ ነው:: ሁለተኛው ላይ እያለ በፍጥነት ካልታከመ ወደ ሦስተኛው ተሸጋግሮ ነርቭን ስለሚጎዳ የማያቋርጥ ሕመም ይኖራል ማለት ነው::

መፍትሔው የጥርሳችን ኢናሜል እየተቦረቦረ  ከሆነ በቀላሉ በመሙላት የመቦርቦር ሂደቱ ባለበት እንዲቆም ማድረግ ይቻላል:: ዴንታይኑ ጋር ከደረሰ አሁንም በመሙላት ማስተካከል ይቻላል:: ወደ ሦስተኛው ክፍል ከሄደ ግን ሕመሙን በቀላሉ ሙሌት ብቻ ላያስቆመው ይችላል:: ሥሩ መታከም እና መሸፈን እንዲሁም ማስነቀልም ሊኖር ይችላል::

 

ዶክተር ፍስሃ እንዳብራሩት በተቻለ መንገድ ጥርሱ የማይወለቅበትን መንገድ መሞከር ያስፈልጋል:: አንድ የተቦረቦረ ጥርስ ካለ በዚያ በውስጡ ምግብ ገብቶ ይከማቻል:: ምግቡን ባክቴሪያው ይጠቀምና አሲድ ይለቃል:: አሲዱም ወደ ጎን ካለው ጥርስ የመዛመት ዕድል ይኖረዋል:: በዚህ ወቅት በአንድ ጊዜ ሦስት አራት ጥርሶች የመቦርቦር ዕድል ይኖራቸዋል:: ስለዚህ የትኛውንም መጠን ይሁን የተቦረቦረ ጥርስ ይዞ ዝም ማለት ጉዳት ያመጣል::

በተመሳሳይ ሕጻናት ጥርሳቸው ሲቦረቦር የወተት ጥርስ በመሆኑ በራሱ ይወልቃል ተብሎ መተው የለበትም፤ በየደረጃው የራሱ የሕክምና አማራጭ ስለሚኖረው የተቦረቦረ ጥርስ በሚታይበት ጊዜ  ወደ ሕክምና ወስዶ ማሳየት ተገቢ ነው:: ከተሞላ በኋላ በራሱ እስኪወልቅ ድረስ በጤናማ መንገድ መቆየት እንዳለበትም መክረዋል::

 

ዶክተር ፍስሃ እንደሚሉት በመንጋጋ ስፋት፣ በጥርስ መጠን፣ እና ጥንካሬ … ጥርስ ከቤተሰብ ዘር ውርስ ጋር ሊያያዝ ይችላል፤ ከዚህ ውጪ ግን መቦርቦር (የጥርስ ሕመም) በዘር የሚፈጠር እንዳልሆነ ነው የተናገሩት::

በተያያዘም ባለሙያው ስለ ጥርስ ማስነቀል በሰጡን መረጃ ጥርስ ማስነቀል በጥርስ ሕክምና የመጨረሻው አማራጭ ነው:: ይህ ማለት ከአቅም በላይ የሆነና ታክሞ ሊስተካከል የማይችል ጥርስ ሲኖር ነው ማስነቀል የሚመጣው:: በእኛ ሀገር ሁኔታ ባለው የግንዛቤ እጥረት የተነሳ የጥርስ ችግር ያለበት ሰው ወደ ሐኪም የሚሄደው ጥርሱ የመነቀል ሂደት ላይ ከደረሰ በኋላ ነው::  ስለዚህ ከመነቀል በፊት ያሉ አማራጮችን መጠቀም ተገቢ ነው::

 

ጥርስ ማስነቀል ለጊዜው ሕመምን ቢያስታግስም የጎንዮሽ ጉዳት አለው::  ለአብነትም በተደጋጋሚ  ጥርስ በሚነቀልበት ጊዜ የጥርስን ጥቅም ያሳጣል:: የጥርስ ሥራ ምግብን በሚገባው መንገድ አድቅቆ ወደ ጨጓራ መላክ ነው:: እናም አንድ ሰው ምግብ ሊያደቅ፣ ሊሰብር፣ ሊሰነጥቅ የሚያስችል ጥርስ ከሌለው በአግባቡ በጥርስ መድቀቅ የሚገባው ምግብ ሳይደቅ ወደ ጨጓራ በመሔድ  ጨጓራ ላይ ጫና ይፈጥራል:: ይህ ማለት ጨጓራ የጥርስን ሥራ ተክቶ ለመሥራት ሲሞክር ብዙ አሲድ ያመነጫል:: ብዙ አሲድ መመንጨቱ ደግሞ ለጨጓራ ሕመም ይዳርጋል::  ከዚያ በተጨማሪም ብዙ ጥርስ ሲወልቅ የፊት ቅርጽ ይቀየራል:: በጎንና በጎን ያሉ  ጥርሶች ወደ ተነቀለበት ቦታ  ያጋድላሉ::  በዚህም ጥርሳችን አቀማመጡ ይዛባል::

በሀገራችን የድድ መድማትን ለማስቆም እንዲሁም ለውበት በሚል ብዙ ጠቃሚ ያልሆኑ ባሕላዊ ልምዶች  እንደሚፈጸሙ የተናገሩት ባለሙያው ከነዚህ ውስጥ አንዱ የጥርስ ንቅሳት መሆኑን ያነሳሉ:: ንቅሳት ውበትን ሊሰጥ ቢችልም ነገር ግን በሕክምናው ዓለም እንደማይመከር ነው የተናገሩት:: ንቅሳት የጥርስ አቃፊ አካላትን ጤንነት እንደሚጎዳም ነው የተናሩት::

 

የተቦረቦረ ጥርስ የሚሞላው  በጊዚያዊ እና በቋሚነት እንደሆነ የተናገሩት ዶ/ር ፍስሃ በጊዚያዊነት የሚሞሉት እንደየጥርሱ አይነት እና መጠን በጊዜያዊነት ተሞልተው በኋላ ላይ በቋሚ ግብዓቶች ይቀየራሉ:: ሌላው በቋሚነት የሚሞሉት ከጥርስ ቀለም (ከለር) ጋር የሚመሳሰሉ ናቸው:: መሞላቱ እንዳይለይ ተደርጎ የተሻለ ጥንካሬና  የማገልገል አቅም ያላቸውን ግብዓቶች በመጠቀም ይሞላል::

ሌላው ከጥርስ ሕመም ጋር የሚያያዘው በእርግዝና ጊዜ የሚፈጠር የጥርስ ሕመም ነው፤ ባሙያው ይህን በተመለከተ በሰጡን መረጃ  በእርግዝና ወቅት በሚመረተው ሆርሞን ምክንያት የድድ ቅርጽ ይለወጣል፣ ያብጣል፣ ጥርስ በፊት የነበረውን ጥንካሬ ያጣል፣  የተነቃነቀም ይመስላል:: ሆኖም እርግዝናው ካለቀ በኋላ ወደነበረበት ስለሚመለስ ብዙ አሰሳቢ አይደለም ነው ያሉት::

 

የአፋችንንና የጥርሳችንን ጤና ለመጠበቅ የምንጠቀማቸው የጥርስ ሳሙናዎች ምን ያህል ጤናማ ናቸው ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም ሳሙናዎቹ የተለያዬ ጥቅምን ታሳቢ አድርገው እንደሚሠሩ ነው ዶ/ር ፍሰሃ የነገሩን:: ለአብነትም ጥርስን ነጭ የሚያደርጉ፣ የጥርስን ጥንካሬ የሚጠብቁ፣ ለአፍ ውስጥ ጠረን ልዩ ማዕዛ የሚሰጡ ተብለው በየሀገራቱ የጤና ማዕከላት ፍተሻ ተደርጎባቸው የሚገቡ ወይም የሚመረቱ በመሆኑ የጥርስ ማጽጃ ሳሙናዎች ጎጂ አለመሆናቸውን አስገንዝበዋል:: ቀለማቸው (ከለራቸው) የሚለያየውም በያዙት ንጥረ ነገር እና ለምን ታሳቢ ተደርገው እንደተሠሩ ለማመላከት ነው::

 

ጥርሳቸውን ሲቦርሹ ድዳቸው ለሚደማባቸው ሰዎች ባስተላለፉት መልዕክትም ሰዎች በትክክለኛው የጥርስ ሳሙና እና የጥርስ አቦራረሽ ሂደትን ተከትለው ከቦረሹ ችግሩ አያጋጥማቸውም:: ሆኖም ድድ ጤነኛ ካልሆነ ግን በሚቦረሽበት ጊዜ ሊደማ ይችላል::

ጤነኛ ድድ ማለት ከጥርስ ጋር በደንብ የተጣበቀ ነው፤ ሲነካም በቀላሉ አይደማም:: ሆኖም የአፋችን ጤንነት በአግባቡ የማይጠበቅ ከሆነ፣ የላሙ ምግቦች በጥርሳችን መካከል ተከማችተው ቆይተው ሲደርቁ የድድ ቁስለት (ኢንፌክሽን) ይፈጠራል:: በዚህ ጊዜ የድዳችን መልክ ደማቅ ቀይ ይሆናል:: ሲነካም በቀላሉ ይደማል:: 50 በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብም ይህ ሁኔታ ያጋጥመዋል::

 

ሰዎች በዓመት ሁለት ጊዜ የጥርስ እጥበት ማከናወን እንዳለባቸው የተናገሩት ዶ/ር ፍሰሃ ጥርስ ማሳጠብ ሻህላ የሚባለውን ጥርስ ላይ የሚለጠፍ ቆሻሻ እንደሚያነሳ ነው የጠቆሙት:: ጥርስ ማሳጠብ የጥርስን መስታዎትን (ሽፋን) ይጎዳል የሚባለውም የተዛባ አመለካከት እንደሆነ ነው  የገለጹት::

ባለሙያው አያይዘው እንደገለጹት በቀን ሦስት ጊዜ ጥርስ መቦረሽ እንዳለበት ነው:: ይሁንና ከሥራ ባህርይ ጋር ስለማይስማማ ቢያንስ በቀን ሁለት ጊዜ መቦረሽ ጥሩ እንደሆነ፣ ከምግብ በኋላ እና ከመኝታ በፊት መቦረሽ እንደሚገባም መክረዋል::

 

ሕጻናት ሙሉ ጥርስ እስከሚያበቅሉ ድረስ በወላጆች እገዛ በለስላሳ ጨርቅ በጨው እና በውኃ እየነከሩ የላመ ምግብ ጥርሳቸውን እንዳይጎዳው ማጽዳት (አስገዳጅ ባይሆንም) ተገቢ ስለመሆኑም ነው ያስገነዘቡት:: ከሦስት ዓመታቸው  በኋላ ግን ለራሳቸው በተዘጋጀላቸው የጥርስ ሳሙና እና ቡርሽ በአዋቂዎች ድጋፍ ጥርሳቸውን ማጽዳት አለባቸው:: ጥርሳቸው እንዳይቦረቦር ደግሞ ጣፋጭ ምግቦችን ማዘውተር እንደሌለባቸው መክረዋል::

ዶ/ር ፍሰሃ አያይዘው ባስተላለፉት መልዕክት በተለምዶ ለጥርስ ማጽጃ በሚል የወይራ እንጨትና ልምጪን የመሳሰሉ መፋቂያዎች  ጥናት እስካልተደረገባቸው ድረስ ለጤና ጎጂ ወይም ጠቃሚ ናቸው ማለት እንደማይቻል ነው የተናገሩት::

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሐምሌ 14  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here