እሳተ ገሞራ

0
158

የዓየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው ሙቀት ግግር በረዶ እየቀለጠ መጠኑ ሲቀንስ መሬት ውስጥ የተዳፈነ ቅላጭ አለት እንቅስቃሴ ፈጥሮ እየተስፋፋ የእሳተገሞራ ፍንዳታን ሊያባባስ እንደሚችል ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶታል::

የአውሮፓ ጂኦ ኬሚስትሪ ማህበር በመረጃ ምንጭነት ለንባብ እንዳበቃው ግግር በረዶ ከሥር የሚገኙ የእሳተ ገሞራ  ቅላጭ እንቅስቃሴን ይገድባል:: ሆኖም የበረዶ ክምሩ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሲቀልጥ የተዳፈነው ተነቃቅቶ ፍንዳታው ሊጨምር እንደሚችል አረጋግጧል::

 

የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ መጨመር ተመልሶ  በዓየር ንብረት ላይ ተፅእኖ እንደሚያሳድር ማለትም የሙቀት መጨመርን አባባሽ መሆኑ ነው የተጠቆመው- በጥናቱ::

ተመራማሪዎች አንታርክቲክን በመሳሰሉ ግግር በረዶ ባለባቸው ቀጣናዎች በርካታ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተዳፈኑ እሳተ ገሞራዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ነው ያረጋገጡት:: የተዳፈኑት ንቁ ሆነው ሲፈነዱ በጥቅሉ በዓየር ንብረት ላይ እጅግ አሳሳቢ ጫና እንደሚያሳድሩም ነው ያሳሰቡት::

ተመራማሪዎቹ የተዳፈኑ እሳተ ገሞራዎች አሉ ተብለው በሚገመቱበት ቀጣናዎች ክትትል ጀምረዋል- ለአብነት በቺሊ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ ኒውዝላንድ እና ሩሲያ በመሳሰሉትም ላይ ትኩረት አድርገዋል::

 

የተጠቀሰውን የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ስጋት በምርምር እና ውጤት ትንበያ ላይ የተመሠረተ ለማድረግ ከአሜሪካ የዊስኮንስ ማዲሰን ተመራማሪዎች በቺሊ ስድስት ያንቀላፉ ወይም የተዳፈኑ እሳተ ገሞራዎችን በቅርበት መርምረዋል፤ ገምግመዋል:: በውጤቱም እሳተ ገሞራዎቹ ከላይኛው የመሬት ገጽ ከ10 እስከ 15 ኪሎ ሜትር ጥልቀት የቀለጠ ዓለት ታምቆ የተዳፈኑ መሆናቸውን አረጋግጠዋል::በቅድመ ልደት በበረዶ ዘመን ከበርካታ ሺህ ዓመታት በፊት ይህን መሰል ሁነት ሳይከሰት እንዳልቀረም ነው መላምታቸውን ያስቀመጡት::

በማጠቃለያነት አሁን ላይ ያለው የግግር በረዶ መቅለጥ የተዳፈኑ እሳተ ገሞራዎችን በየቀጣናው አንቅቶ የሚፈነዱ ከሆነ ተፅእኖዋቸው ተባብሶ አሁን ያለው የዓየር ንብረት ለውጥ   ወደ  ከፋ ደረጃ ሊሸጋገር እንደሚችል ነው  ያሳሰቡት – ተመራማሪዎቹ::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here