አጋቹ እባብ

0
165

በአውስትራሊያ የሀገር ውስጥ መጓጓዣ አውሮኘላን ተሳፋሪዎች በመግባት ላይ እያሉ በእቃ መጫኛው ክፍል እባብ ተለጥፎ በመታየቱ በረራው ለአንድ ሰዓት መዘግየቱን ዩፒአይ ድረገጽ ከሳምንት በፊት ለንባብ አብቅቶታል፡፡

ቨርጂን አውስትራሊያ ቪኤ 337 አውሮኘላን ከሜልቦርን ወደ ብሪስቤን ለመጓዝ በዝግጅት ላይ እያለ የአውሮኘላኑ ሰራተኞች በጭነት ክፍሉ እባብ በመመልከታቸው በረራው ሊዘገይ ችሏል፡፡

እባቡ እንደታየ ማርክ ፔሊ ለተሰኘ እባብ አዳኝ ባለሙያ ተነግሮት በቦታው ይደርሳል፤ እናም በእቃ መጫኛው ክፍል 60 ሴንቲ ሜትር ወይም ሁለት ጫማ የሚረዝም እባብ ማየቱን አረጋግጧል፡፡

 

እባብ አዳኙ ማርክ ፔሊ በአውስትራሊያ የሚገኙ አብዛኛዎቹ የእባብ አይነቶች መርዛማ መሆናቸውን ገልፆ  እባቡ ባለበት ሁኔታ ካልተያዘ ወይም ወደ ድብቅ ቦታ ከተሰወረ  ተጓዦች ከአውሮኘላኑ ፈጥነው መውጣት እንደሚኖርባቸው አሳስቧል፡፡

ባለሙያው እባቡን ለመያዝ ሲሞክር ግማሽ አካሉ ማእዘን ላይ በሚገኝ ክፍተት በመሰወሩ ተጓዦች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የዓየር መንገዱ ሰራተኞችም ይህንኑ እንዲፈጸሙ ምክሩን ለግሶ ጥረቱን ይያያዘዋል፡፡ እባቡን ለመያዝ ሲቃረብ ግን ዓይነቱን ለይቶ መርዛማ ይሁን አይሁን በውል ለመገንዘብ ባደረገው ጥረት እባቡ አረንጓዴ ቀለም ያለው የዛፍ ላይ መርዛማ ያልሆነ እባብ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

ለሁሉም ተጓዦች እና ለአውሮኘላኑ ሰራተኞች አብስሮ እባቡን ለመያዝ በገባበት የአውሮኘላኑ የውስጥ ግድግዳ መገናኛ ማእዘን የመጀመሪያ ሙከራውን አድርጐ ካልተሳካ ቀጣዩ ርምጃ ተጓዦችን እና እቃዎቹን አውርዶ አውሮኘላኑን መፍታት ሊሆን እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል- እባብ አዳኙ ባለሙያ፡፡

 

በመጨረሻም እባብ አዳኙ ባለሙያ ባደረገው የመጀመሪያ ጥረት እባቡን የመያዝ ጥረቱ ሊሳካለት ችሏል፡፡ የተያዘው የእባብ ዝርያ በአውስትራሊያ ጥበቃ የሚደረግለት በመሆኑም የእባብ ጥበቃ ፈቃድ ላለው የእንስሳት ሀኪም መሰጠቱ ነው በማደማደሚያነት ለንባብ የበቃው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here