ጣሊያናዊው መካኒክ በ1993 እ.አ.አ የተሰራች ፊያት የቤት መኪናን ቆራርጦ መልሶ በመገጣጠም አንድ ሰው ብቻ የምትይዝ ጠባብ መኪና መስራቱን ኦዲቲ ሴትንራል ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት አስነብቧል፡፡
አንድ ሰው ብቻ የምትይዘውን ጠባቧን ተሽከርካሪ የተመለከቱ በሰው ሰራሽ ኪሂሎት ወይም /አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ /የተሰራች ብትመስላቸውም በጐዳና ላይ ስትሽከረከር በመመልከታቸው የዓለማችን ጠባቧ ተሽከርካሪ መሆኗን ማረጋገጥ መቻላቸውን ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡
ጣሊያናዊው መካኒክ አንድሬ ማራዚ የ1990ዎቹ ስሪት የሆነችውን ፊያት የቤት መኪና አዲስ ቁስ ሳይጨምር ሙሉ በሙሉ ከቀድመ ስሪቷ መጠኗን ቀንሶ የዓለማችንን ቀጭኗን ተሽከርካሪ ለመስራት 12 ወራት እንዳፈጀበት ነው ድረ ገጹ ያስነበበው፡፡
ጠባቧ ተሽከርካሪ ስፋቷ 50 ሴንቲ ሜትር ሲሆን በምሽት ለማሽከርከር የሚረዳ አንድ የፊት መብራት ብቻ ነው ያላት፡፡
የተሽከርካሪዋ ጠቅላላ ክብደት 264 ኪሎ ግራም ፣ከፍታዋ ወይም ቁመቷ 145 ሴንቲ ሜትር ርዝመቷ ደግሞ 340 ሴንቲ ሜትር፣ ስፋቷ 50 ሴንቲሜትር ተለክቷል፡፡ ተሽከርካሪዋ በኤሌክትሪክ የምትሰራ ሲሆን በአንድ ጊዜ ሙሊት 25 ኪሎ ሜትር መጓዝ እንደምትችል ነው የተገለፀው- በድረ ገጹ፡፡
ተሽከርካሪዋ ቀጭን ናት ወይም ስፋት የላትም – በመሆኑም ለአደጋ ተጋላጭ ትሆናለች- በመሆኑም የመጨረሻ ፍጥነቷ በሰዓት 15 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው፡፡ ተሽከርካሪዋ እስከ አሁን በሚመለከተው አካል በጐዳና ላይ ለመሽከርከር ፈቃድ አላገኘችም- የሰራትን ባለሙያ ችሎታ ማሳያ ብቻ እንጂ፡፡
በዚህም ተባለ በዚያ ቀጭኗን 50 ሴንቲ ሜትር ብቻ ስፋት ያላትን ተሽከርካሪ የሰራት ባለሙያ በዓለም አቀፍ የድንቃ ድንቅ መዝጋቢ ድርጅት ለማስመዝገብ ጥረት እያደረገ መሆኑ ነው የተብራራው፡፡
ከሁሉም በላይ የጣሊያናዊው መካኒክ የፈጠራ ሀሳቡ፣ ትእግስቱ እና የአንድ ዓመት የፈጀ ጥረቱ ይበል የሚያሰኝ መሆኑ ነው በማደማደሚያነት ለንባብ የበቃው፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም