ካታቪ ብሔራዊ ፓርክ በታንዛኒያ በምእራብ አቅጣጫ በካታቪ ክልል ነው የሚገኘው፡፡
ካታቪ በ1974 እ.አ.አ የዱር እንስሳት ጥብቅ ስፍራ ሆኖ 22 ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ በ1996 በብሔራዊ ፓርክነት እውቅና አግኝቷል፡፡
የፓርኩ ስፋትም 4500 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል፡፡
የዓየር ንብረቱ ሞቃታማ ሲሆን ርጥበት የሚበዛባቸው ዝናባማ ወራት ከህዳር እስከ ሚያዚያ ያሉት ናቸው፡፡ ደረቅ ዝናብ የሌለባቸው ደግሞ ከግንቦት እስከ ጥቅምት ሙቀቱ የሚያይልባቸው ሆነው ነው የተለዩት፡፡
ለጐብኚዎች የምሽቱ ዓየር ፀባይ ቀዝቀዝ ስለሚል የዱር እንስሳቱን ለመመልከት በበርካቶች ተመራጭ ነው፡፡ ከወራቱ ደግሞ ከግንቦት እስከ ጥቅምት ያሉት ጭቃ የማይበዛባቸው ተመራጭ መሆ ናቸውን ልብ ይሏል፡፡
ፓርኩ ደን፣ የሳር ምድር፣ ውኃ የሚተኛበት ደልደላ ሜዳ ይበዛዋል እንዲሁም የካታቪ እና ቻዳ ኃይቆችን ይዟል፡፡
ከዱር እንስሳት የጐሽ መንጋ በበጋ በወንዞች ዳር ይታያል- በፓርኩ ቀጣና ጉማሬ እና አዞ በረግረጋማ ቀጣናዎች፣ በኃይቆች እና ወንዞች ዳር መመልከት ለጐብኚዎች የደስታ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል፡፡ አቦሸማኔ፣ የዱር ውሻ እና አንበሳም የትእይንቱ አካል ናቸው- በካታቪ ፓርክ፡፡
ከአእዋፍ 400 ዝርያዎች እንደሚገኙ ተመዝግቧል፡፡ አእዋፉን በሚገባ ለመመልከት በክረምቱ ማየል ከቀጣናው የተሰደዱት ሲመለሱ ከህዳር እስከ ሚያዚያ ያሉት የበጋ ወራት ተመራጭ ናቸው፡፡
ካታቪ ብሔራዊ ፓርክ መገኛው ራቅ ያለ ነው፡፡ በመሆኑም ለጐብኚዎች ቀደም ብሎ ከጉዞ ወኪሎች ጋር መገናኘት እና አስፈላጊ ሁኔታዎችን ማመቻቸትን ግድ ይላል፡፡ ለዚህም ቻዳ ካታቪ ካምኘ፣ ካታቪዋይልድ ካምኘ እና ሙዋምባዚ ሳፋሪ ካምኘ ዝግጁ ሆነው ይጠበቃሉ፡፡
በመጨረሻም ወደ ፓርኩ ለመድረስ የአየርም ሆነ ለተሽከርካሪ የተመቸ ነው፡፡ በቅርበት የሚገኘው የዓየር ማረፊያ ማፓንዳ ከተማ የተገነባው ሲሆን በግል በማንኛውም ሰዓት በኪራይ ከዳሬ ስላምም ሆነ ከአሩሻ መነሳት ይችላሉ – ጐብኚዎች፡፡
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ታንዛኒያ ካታቪ ናሽናል ፓርክ፣ አፍሪካ ጂኦግራፊክ እና ታንዛኒያ ቱሪዝም ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም