“ዛፉ ዛፉ እስትንፋሴ፣
ልጠብቅህ እንደራሴ!
ዛፉ ዛፉ አረንጓዴ፣
አንተ ባትኖር እኛስ አለን እንዴ?”
እንደ መንደርደሪያ የተነሱት ስንኞች የዕጽዋትን እና ሌሎች ፍጥረታትን (በተለይ የሰው ልጅ) የማይነጣጠል መስተጋብር፣ አንዱ ለሌላው የመኖር ምክንያት እንደሆኑ ለማሳየት የተጠቀሱ ናቸው:: ይህን በመረዳትም ነው ታዋቂው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በስንኞቹ የተቀኜው::
በኢትዮጵያ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሀገሪቱ የመሬት ቆዳ ስፋት ውስጥ 60 በመቶው የሚሆነው በደን የተሸፈነ እንደነበር ድርሳናት ያስነብባሉ። በተለይም በዐፄ ዳዊት፣ በንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ፣ አፄ ምኒልክ፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴ እና በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዘመነ መንግሥታት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።
እነዚህ የየዘመኑ መንግሥታት የደን ጭፍጨፋን ለመከላከል የሚያስችሉ ጥብቅ የሕግ ማዕቀፎችን ከማውጣት ጀምረው በተለያዩ መንግሥታት የነበሩ ተሞክሮዎችን አስቀጥለዋል:: ለአብነትም አፄ ምኒልክ ችግኝ የዜጎች ጉዳይ እንዲሆን የመሬት ግብር ምሕረት እስከማድረግ የሚደርስ ማበረታቻ ማድረጋቸው ይጠቀሳል:: ከዚህ ባለፈ በደን ጭፍጨፋ የሚሳተፉ አካላት ንብረታቸው እንዲወረስ እና የማያዳግም ቅጣትን የሚያበረታታ የሕግ ማዕቀፍ ማውጣታቸው ለዘርፉ የሰጡት ትኩረት ማሳያ ነው::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለዓመታት ትኩረት በመነፈጉ፣ የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ፣ የእርሻ ሥራ በመስፋፋቱ፣ የባለቤትነት ስሜት በማጣቱ እና መሰል ምክንያቶች የሀገራችን የደን ሽፋን እየተመናመነ ወደ ሦስት በመቶ አሽቆልቁሎ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። ይህም ለበረሃማነት መስፋፋት፣ ለዱር እንስሳት መሰደድ፣ ለዝናብ እጥረት እና መሰል ችግሮች ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።
ይህን ለመቀልበስ በተሠሩ ሥራዎች ታዲያ የደን ሽፋኑን ከመመናመን መታደግ ተችሏል፤ ለዚህ ደግሞ በተለይ በቅርብ ዓመታት የተጀመረው ዓመታዊው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ማሳያ ነው። ኢትዮጵያ የተራቆተ መሬቷን ለማከም፣ ዓለምን እየፈተነ ያለውን እና ለብዙ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ በብርቱ እየሠራች መሆኑን ከግብርና ሚኒስቴር የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ::
ባለፋት ስድስት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል በከፍተኛ ደረጃ ተጎድቶ የነበረ መሬት እንዲያገግም እና በአካባቢ ጥበቃ ሥራውም ላይ ለውጥ እንዲያመጡ መደረጉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያክላል:: አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የምትፈተንበትን እንደ ድርቅ፣ የመሬት መንሸራተት፣ ቅፅበታዊ ጎርፍ እና አሲዳማነትን ለመቀነስ አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑንም ባለሙያዎች ይናገራሉ::
በመሆኑም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ለአረንጓዴ አሻራ በተሰጠው ልዩ ትኩረት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ ስድስት በመቶ መድረሱን ከኢትዮጵያ ደን ልማት ድረ ገፅ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በ2030 ዓ.ም የደን ሽፋኗን ወደ 30 በመቶ ከፍ ለማድረግ በትጋት እየሠራች እንደምትገኝ መረጃው አክሏል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተለይ ባለፉት ስድስት ዓመታት በተሻለ መነቃቃት እየተከናወነ የሚገኝ ተግባር ነው። በዚህም የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ ሳይጨምር ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ከኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር ማሕበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል::
እንደ ሀገር በ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከሰባት ነጥብ አምስት በላይ ችግኝ ይተከላል ተብሎ ይጠበቃል።
በአማራ ክልልም በ2017 ዓ.ም በክረምት ወራት በሚከናወነው የችግኝ ተከላ በክልሉ አሁን ያለውን 16 ነጥብ ሦስት በመቶ የደን ሽፋን ወደ 17 ነጥብ ሦስት በመቶ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል። በአማራ ክልል ባለፉት ስድስት ተከታታይ ዓመታት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከዘጠኝ ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን የፅድቀት ምጣኔም በየዓመቱ ዕድገት እያሳየ ነው። ለዚህም የኅብረተሰቡ እና የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር መዳበር፣ ኅብረተሰቡ የተሻለ ግንዛቤ መኖሩ እና የፅድቀት መጠን የሚጨምሩ የተሻሻሉ ሥራዎች በመሠራታቸው ስለመሆኑ ነው የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ያስታወቀው።
አረንጓዴ አሻራ የአፈር ለምነትን ለመጨመርና ለመጠበቅ፣ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የቱሪስት ሀብቱን ለማሳደግ፣ የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል፣ ለአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ፣ የውኃ አካላትን ለማጎልበት (የውኃ ምንጮች እንዲበራከቱ)፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ፣ ለአካባቢ ውበት፣ ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ፣ ለሥነ ምህዳር ጥበቃ፣ ለመድኃኒት መቀመሚያ፣ ለዱር እንስሳት መጠለያ፣ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል፣ ለማገዶ፣ ለከሰል፣ ለቤት መገንቢያ፣ ለውጭ ምንዛሬ ማስገኛ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ጉልህ ሚናን እንደሚጫወት በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የደን ምርምር ዳይሬክተር ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ምናለ ወንዴ አስረድተዋል።
በአማራ ክልል በ2017/18 የክረምት ወቅት አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። እስካሁን አንድ ነጥብ 55 ቢሊዮን ችግኞች እና አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን የተከላ ጉድጓድ ተዘጋጅቷል። ከ205 ሺህ ሄክታር በላይ የተከላ ቦታ የተለየ ሲሆን ከ53 ሺህ በላይ ሄክታር የተከላ ቦታ ላይ የካርታ ሥራም ተሠርቷል።
ይህን ሁሉ ዝግጅት በማድረግ ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሐምሌ 01 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ መጀመሩ የሚታወስ ነው። “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘንድሮ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ይተከላሉ ተብሎ ይጠበቃል። አሁን ላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለተከላ ዝግጁ መደረጋቸውም ተገልጿል። ከተዘጋጁ ችግኞች ውስጥ የፍራፍሬ፣ ሀገር በቀል የደን ችግኞች፣ የእንስሳት መኖ እና ሌሎች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ናቸው። በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንደ ክልል 278 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ከቢሮዉ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል::
የክልሉ የደን ምርምር ዳይሬክተር ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ምናለ ወንዴ እንዳሉት በኢትዮጵያ የደን ልማትን ለማፋጠን የደን ፖሊሲ እና የደን ጥበቃ አዋጅ ተቀርፆ ወደ ሥራ ተገብቷል። የደን ዘርፉ በሀገር አቀፍ ደረጃ 12 ነጥብ 9 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ድርሻ እንዳለውም አመላክተዋል። አረንጓዴ አሻራ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማሕበራዊ እና አካባቢያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል። ለአብነትም የተለያዩ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ተግባራት የሚከናወኑት በደን ውስጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዳይሬክተሩ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሲከናወን ሳይንሳዊ ዘዴን እና በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል። የአማራ ክልል ለደን ልማት የሚውል የተለያዩ ሥነ – ምህዳሮች፣ ምቹ የአየር ንብረት እና ተስማሚ አፈር እንዳለው ገልፀዋል።
የተመናመነን የደን ሽፋን መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል። ከመትከል በላይ የጽድቀት ምጣኔን ማሳደግ ዋናው ጉዳይ ሊሆን ይገባልም ብለዋል:: የጽድቀት ምጣኔ ሊያድግ የሚችለው ደግሞ የተተከሉት ችግኞች ባለቤት ሲኖራቸው መሆኑን ጠቅሰዋል::
እንደ ክልል የደን ሽፋንን ለማሳደግ እየገጠሙ ያሉ ዋና ዋና ተግዳሮቶችን ዳይሬክተሩ ዘርዝረዋል። እነዚህም ተፈጥሯዊ፣ ቴክኒካዊ፣ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓሊሲያዊ መሆናቸውን ነው ያስረዱት። ተፈጥሯዊ ተግዳሮቶች ደን ምርት ለመስጠት ከአምስት እስከ 15 ዓመት ጊዜ የሚወስድ እና የግብርና ሥራ በሰብል ልማት ላይ ያተኮረ መሆኑን አንስተዋል። ነገር ግን ብዙ ሀገሮች በሰብል ምርት ብቻ ለውጥ እንደማያመጡ ተረድተው በደን ልማት ላይ ማተኮራቸውን ገልፀዋል።
ቴክኒካዊ ችግር ሌላው ተግዳሮት ሲሆን የተከላ ቦታ እና የችግኝ ዝርያ አለመጣጣም፣ የሚተከሉ ችግኞች ለምን ዓላማ እንደሚተከሉ አለመረዳት፣ ተገቢውን እንክብካቤ አለማድረግ እና ሌሎችን ጠቅሰዋል። ማሕበራዊ የሚባው ተግዳሮትም የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የሰደድ እሳት፣ ሕገ ወጥ የደን ጭፍጨፋ እና መሰል ችግሮች ናቸው። ኢኮኖሚያዊ፦ በታዳሽ ኃይል አለመተካት (የኃይል ምንጫችን በደን ውጤቶች ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ) የደን መጨፍጨፍ መንስኤ ሆኗል ብለዋል።
ሌላው ፖሊሲያዊ ተግዳሮት ሲሆን፤ የሚወጡ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በታቀደው መሠረት አለመፈፀም እየታዩ ያሉ ተግዳሮቶች ናቸው ብለዋል።
የሚተከሉ ችግኞች እንዳይፀድቁ የሚያደርጉ ዋና ዋና ምክንያቶችንም ከፍተኛ ተመራማሪው ገልፀዋል። እነዚህም የቅድመ ዝግጅት ማነስ፣ ያለ ፕላስቲክ ማፍላትና መትከል፣ የተከላ ቦታ አለመለየት፣ ቀድሞ ጉድጓድ አለማዘጋጀት (ወዲያው ቆፍሮ መትከል)፣ ከአረም ነፃ አለማድረግ፣ የችግኝ ፍል ዕድገቱን አለመከታተል፣ ጥራት ያለው ችግኝ አለመትከል፣ በወቅቱ አለመትከል፣ በቂ የአፈር እርጥበት በሚኖርበት ሰዓት አለመትከል እና መሰል ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ችግኝ ከንፁህ ዘር መረጣ ጀምሮ የዘር ጥራቱን ፍተሻ ማድረግ፣ የእያንዳንዱን የችግኝ ዘር ዓይነት ማወቅ፣ የበቀለው ችግኝ በችግኝ ጣቢያው ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ መረዳት፣ ተገቢውን እንክብካቤ አድርጎ ጠንካራና ጤናማ ችግኝ ወደ ተከላ ቦታ መውሰድ፣ የተከላ ቦታን ማፅዳት፣ ደረጃውን የጠበቀ የችግኝ ጉድጓድ ማዘጋጀት፣ ሳይንሳዊ ዘዴን በመከተል ርቀቱን እና ስፋቱን መለካት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከተከላ በኋላም ወቅቱን ጠብቆ መኮትኮት፣ ማረም፣ ውኃ ማጠጣት፣ ማጠር፣ ከእንስሳት ንክኪ ነፃ ማድረግ፣ ልክ እንደ ሰብል ልማቱ ተገቢውን ግብዓት መጨመር (የአፈር ማዳበሪያ እና ኮምፖስት)፣ ካደጉ በኋላም መመልመል፣ ተገቢውን ጥበቃ እና እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።
መረጃ
በኢትዮጵያ የተለያዩ የደን ዓይነቶች ይገኛሉ። ከነዚህ መካከልም፦ የተፈጥሮ ደን፣ ሰው ሠራሽ ደን፣ ዘርዛራ ደን፣ የጣንና ሙጫ፣ የቅርቀሀ እና ቁጥቋጦ ደኖች ተጠቃሽ ናቸው።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም