የብሪክስ ጉዞ

0
115
Indian Prime Minister Narendra Modi, China's President Xi Jinping, South Africa's President Cyril Ramaphosa, Russia's President Vladimir Putin and Brazil's President Michel Temer pose for a group picture at the BRICS summit meeting in Johannesburg, South Africa, July 26, 2018. REUTERS/Mike Hutchings

ብሪክስ የተፈጠረው በመስራች ሀገራት  ፖለቲካዊ ተነሳሽነት ነው። የመጀመሪያ ግቡ በዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ውስጥ ስላሉት ዋና ዋና መሪ ሃሳቦች ውይይት ማድረግ እና የጋራ አቋማቸውን በፖለቲካዊ መልኩ በማጠናከር የዓለምን ስርዓት ዴሞክራሲያዊ፣ ሕጋዊ እና ሚዛናዊ ለማድረግ ነው።

እንደ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ ሀገራት ስብስብ ምህፃረ ቃል የሆነው ብሪክስ ዓላማው ሰላምን፣ ደኅንነትን፣ ልማትን እና ትብብርን ማበረታታት ነው። የመጀመሪያው የብሪክስ ስብሰባ የተካሄደው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ እ.አ.አ. በ2006 በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ነው። እ.አ.አ. በ 2008 የፋይናንስ ቀውስ ተፈጥሮ በነበረበት ጊዜ በወቅቱ አራቱ ሀገራት (ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና) ከቡድን ሃያ (G20)፣ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ፈንድ (አይኤምኤፍ) እና ከዓለም ባንክ አንፃር የተቀናጀ አካሄድ በመከተል የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ እና የፋይናንስ አስተዳደርን ለማሻሻል ሀሳቦችን በማቅረብ ታዳጊ ሀገራት በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸውን አንፃራዊ ክብደት ለማንፀባረቅ ሞክረዋል። ሀገራቱ የመጀመሪያውን የብሪክስ መሪዎች ጉባኤን ያካሄዱት እ.አ.አ 2009 ሲሆን አስተናጋጇም  ሩሲያ ነበረች::

 

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የብሪክስ አባል ሀገራት በአፍሪካ ያላቸውን ተሳትፎ አስፋፍተዋል። በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ገቢ እና በንግድ መጠን ያላቸው ድርሻም በፍጥነት ከፍ ብሏል። አብዛኛዎቹ አባል ሀገራቱ በተለያዩ አህጉራት ላይ ጉልህ ተዋናዮች ናቸው። ለዓለም ኢኮኖሚ ጠቃሚ የሆኑ ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት እና ሌሎች ወደ ውጭ የሚላኩ ጥሬ እቃዎች አሏቸው።

ግሎባል ታይምስ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ብሪክስ በዓለም አቀፉ ስርዓት ለውጥ እና በዓለም አቀፍ የኃይል ሚዛን ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር ወሳኝ መድረክ ሆኗል። የብሪክስ አባል ሀገራት ዛሬ 31 በመቶውን የዓለም የመሬት ስፋት፣ 46 በመቶውን የዓለም ሕዝብ እና 20 በመቶውን የዓለም ንግድ ይሸፍናሉ። የዘይት ምርታቸው እና የመጠባበቂያ ክምችቱም ከዓለም አቀፍ የኃይል ገጽታ 40 በመቶውን ይይዛል።

 

ስታርት አፕ ኢንዲያ (tartupindia) የተባለ ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ደግሞ እንደሚያመላክተው የብሪክስ  ሀገራት ኢኮኖሚያቸውን በምናይበት ጊዜ 37 ነጥብ ሦስት በመቶ የሚሆነውን ከዓለም አቀፉ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ያዋጣሉ:: ይህም ጉልህ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ክብደታቸውን ያሳያል።

//ipea.gov.br// ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው “ጎልድ ማን ሳችስ” የተባለ የኢንቨስትመንት ባንክ እ.አ.አ በ2032 የብሪክስ ሀገራት አጠቃይ ኢኮኖሚ ከቡድን ሰባት (G7) እኩል ይሆናል ብሎ አስቀምጧል::

በብሪክስ ውስጥ ቻይና ለታዳጊ ሀገራት እና ለታዳጊ ገበያዎች እውነተኛ እና ተዓማኒ ድምጽ እንደምትወክል ይታመናል።  ከብሪክስ ሀገራት ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላት እንደመሆኗ መጠን ቻይና የብሪክስ ትብብርን በማጠናከር፣ በመምራት እና በማስተዋወቅ ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውታለች።

 

ብሪክስ በመጀመሪያ አቅዶት የነበረው በ2050 የዓለምን ኢኮኖሚ ሊቆጣጠሩ የሚችሉ በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉ ኢኮኖሚዎችን ማሰባሰብ ነበር። እንደ አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ ያሉ የምዕራባዊያን የበላይነት ያላቸውን ዓለምአቀፍ ተቋማት ሚዛን ለመጠበቅ ጂኦፖለቲካዊ ቡድን ለመፍጠር አልሞ ነበር። በመሆኑም ብሪክስ እስያን፣ አፍሪካን፣ አውሮፓን እና ላቲን አሜሪካን በማካተቱ የበለጸገ የስልጣኔ ስብጥርን ያመጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል::

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ግን ብሪክስ እርስ በርስ የተራራቁ  የሀገሮች ስብስብ ብቻ በመሆኑ ፖለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ውህደታቸው ተስፋ የለውም ብለው ያስባሉ። ለዚህ ሀሳባቸው በምክንያት የጠቀሱት አብዛኛዎቹ የብሪክስ አባል ሀገራት እርስ በርስ ፉክክር ውስጥ ስለሚገኙ እና አንዳንዶችም የአሜሪካ አጋሮች በመሆናቸው ነው:: ተንታኞች በህንድንና በቻይና የኢኮኖሚ፣ የግብጽ እና የኢትዩጵያን በሕዳሴው ግድብ ያለውን ፉክክር እንዲሁም ሳዑዲ አረቢያ እና ዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች አሜሪካ  ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ግምት ውስጥ በማስገባት አላማቸው ላይሳካ ይችላል ይላሉ::  የአሜሪካን ዶላር ላለመጠቀም የወሰኑት ውሳኔም እስካሁን  ይህ ነው የሚባል ፍሬ አንዳላፈራ ነው የሚናገሩት:: ትራምፕም ይህንን ካደረጉ በአባል ሀገራቱ ላይ ተጨማሪ  ታሪፍ እጥላለሁ የሚል ከዛቻ ያልተናነሰ አቋም ይዘዋል:: ሩሲያ እና ቻይና በጂኦፖለቲካዊ አላማቸው ምክንያት ዶላርን ላለመጠቀም ቀዳሚ ሆነዋል። እ.አ.አ. በ 2023 ሩሲያ እና ቻይና የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥን ከአሜሪካ ዶላር ውጭ ለማሳደግ ማቀዳቸውን አሳውቀው ነበር::

 

ከሰሞኑ በሪዮ በተካሄደው የብሪክስ ጉባኤ አባላቱ  በፋይናንስ፣ ጤና፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሰላምን፣ ደኅንነትን እንዲሁም ዓለም አቀፍ መረጋጋትን ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል። አስራአንድ አባላትን የያዘው የብሪክስ ውህድ እንደ ቤላሩስ፣ ቦሊቪያ፣ ኩባ ፣ካዛኪስታን፣ ማሌዥያ፣ ናይጄሪያ፣ ታይላንድ፣ ኡጋንዳ እና ኡዝቤኪስታን የመሳሰሉ አጋር ሀገራትም አሉት:: ከሰሞኑም የብራዚል መንግሥት በጊዜያዊነት የብሪክስ ሊቀ መንበር ሆኖ ሲሾም ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ያላትን ቬትናም የቡድኑ አጋር ሀገር አድርጎ መቀበሉን አስታውቋል:: ቬትናምም አሥረኛዋ የብሪክስ አጋር ሀገር ሆናለች።

 

አልጀዚራ እንደዘገበው ብሪክስ በዓለም ፖለቲካ ውስጥ፣ በዓለም አቀፍ ብዝሃነት እና በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ዴሞክራሲያዊ አሰራር ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል:: በመሆኑም የብሪክስ ህብረት መሪዎች ከአንድ ወር በፊት አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ያደረሱትን የቦምብ ድብደባ “የዓለም አቀፍ ህግን በግልጽ የጣሰ” በሚል መተቸታቸው አንዱ ማሳያ ነው::

ከብሪክስ መግለጫ እጅግ አስደናቂ ከሆኑት አንዱ በ1967 ለተመሰረተው ለፍልስጤም ሀገርነት ያለው የማያሻማ ድጋፍ ሲሆን ምሥራቃዊ እየሩሳሌም ዋና ከተማቸው እንድትሆን ወስነዋል:: እንዲሁም ህብረቱ በጋዛ ላይ አፋጣኝ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ እንዲወጡ፣ ታጋቾች እንዲፈቱ እና ሰብአዊ ርዳታዎችን ያለምንም እንቅፋት እንዲደርሱ መጠየቁ ነው። ምንም እንኳን አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ሕብረቱ በምዕራቡ ዓለም የሚመራውን ዓለም አቀፍ ሥርዓት ሊያደናቅፍ እንደሚችል ቢያስቡም  ነገር ግን የራሱን ገንዘብ ለመፍጠር እና አሁን ካሉ ተቋማት ጋር ሊሠራ የሚችል አማራጭ የማዘጋጀት ፍላጎቱ የማይታለፉ ፈተናዎች እንዳሉበት ያመላክታሉ።

 

የጥምረቱ ራዕይ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን በጋራ ግብ ዙሪያ የሚያቀናጅ ልቅ ከሆነው የምዕራባዊያን ኢኮኖሚ ተፅዕኖ ስብስብ ነፃ መውጣት ነው። የብሪክስ ሀገሮች የምዕራቡ ዓለም የበላይነት ከሚንጸባረቅበት የዓለም ባንክ፣ የቡድን ሰባት (G7) እና የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ባሉ ዋና ዋና የባለብዙ ወገን ቡድኖች ትይዩ ሌላ አማራጭ መገንባት ይፈልጋሉ።

ብሪክስ ከዓለም ባንክ ትይዩ የሚቆም አማራጭ የፋይናንስ ሥርዓት መፍጠር አላማው በመሆኑ  የቡድኑ አዲስ ልማት ባንክ (ኤንዲቢ) እና የተጠባባቂ ሪዘርቭ አደረጃጀት (ሲአርኤ) እንደየቅደም ተከተላቸው የዓለም ባንክን እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ፈንድ (አይኤምኤፍን) ለመገዳደር የሚያስችሉ ናቸው።

የብሪክስ ቡድን በዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ የምዕራባውያን ተጽዕኖን ለመከላከል ካለው ፍላጎት በመነሳት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ትልቅ የፖለቲካ ኃይል ሆኗል::

እ.አ.አ. ሐምሌ 6 እና 7 በ2025 በሪዮ ዴጄኔሮ ብራዚል የተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ በዓለም አቀፍ የአስተዳደር ማሻሻያዎች እና በዓለምአቀፍ ደቡብ ማህበረሰብ ትብብር ላይ ያተኮረ ነበር። ነገር ግን በዚህ ጉባኤ የቻይና እና የሩስያ መሪዎች ለዓመታዊው ስብሰባ ወደ ሪዮ አለመሄዳቸው የሕብረቱን ዘላቂነት ላይ ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱን ካውንስል ኦፍ ፎሬን አፌርስ ላይ ያገኘነው መረጃ ያትታል::

 

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here