ለሰላም ግንባታ ከቤት ጀምሮ መሥራት ይፈልጋል ተባለ

0
130

የሰላም ግንባታ ሁሉም ሰው ከቤቱ፣ ከየእምነት ተቋሙ ሠርቶ ወደ ሀገር የሚያሳድገው ነው፤ በመሆኑም የእምነት ተቋማት ይህን መሠረት በማድረግ ለሰላም መሥፈን በትኩረት መሥራታቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል::

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከል ላይ ያተኮረ ውይይት ከሚለከታቸው አካላት ጋር አካሂዷል፤ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ጥሩወርቅ ገና ከተለያየ ቤተ ዕምነት የተሰባሰቡ ተወካዮች ሰላምን በማስፈን የዘመኑ ባለ አደራ እንደሆኑ ነው የገለፁት::

ሰላም እንዲሰፍን መፍትሔው እና ውጤቱ ከኃይማኖት አባቶች ይገኛል ያሉት ወ/ሮ ጥሩወርቅ ለሰላም ግንባታ ከቤት ጀምሮ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፤ ሰላም ከቤት ሲሰፍን ወደ ጎረቤት፣ ወደ አካባቢ እየተሸጋገረ ሰላም ይጸናል ብለዋል:: ለዚህ ሁሉ መፍትሔው እና ውጤት ደግሞ ከዕምነት ተቋማት እንደሚመጣ ነው ያነሱት::

በኢትዮጵያ ኦርዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር እና አካባቢው ሃገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መላከ ሰላም ፍሰሃ ጥላሁን የኃይማኖት አባቶች የመጀመሪያ ድርሻ ለአምላካቸው ሰላም እንዲመጣ መፀለይ መሆኑን በመጠቆም ቀጥሎ ደግሞ ከመንግሥትም ይሁን ከሌላው ባለድርሻ ጋር ሰላም እንዲመጣ ማስተማር እና የማቀራረብ ሥራ ይሠራል ብለዋል::

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የትምህርት እና ዳዕዋ ዘርፍ ኃላፊ ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም ሰላም ከቤት ጀምሮ ሲወራ ሰው ሰላም ወደ ማሰብ ይመጣል ነው ያሉት፤ ሕብረተሰቡም የኃይማኖት አባቶቹን ማዳመጥ እንደሚገባው ነው የተናገሩት::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here